Thursday, April 11, 2013

እንጦጦ ማርያም ቤተክርስቲያን በኢትዮጵያ ቅርስ ባለአደራ ማኅበር ላይ የመሰረተችውን ክስ ረታች

(ሰንደቅ ጋዜጣ መጋቢት 25 2005 ዓ.ም ፡-) ርዕሰ አድባራት የመንበረ ጸሐይ እንጦጦ ማርያም ቤተክርስቲያን በይዞታዋ ስር የሚገኝውን የባሕር ዛፍ በሕገወጥ መንገድ ጨረታ በማውጣት ለመሸጥ ሲንቀሳቀስ የኢትዮጵያ ቅርስ ባለአደራ ማኅበር የተባለ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ላይ የመሰረተችው ይወገድልኝ ክስ ረታች፡፡
ቤተክርስቲያኗ በጥር 23 2003 ዓ.ም በመሰረተችው ክስ ላይ እንደሰፈረው የኢትዮጵያ ቅርስ ባለአደራ ማኅበር ወደ ቤተክርስቲ  ይዞታ በመግባት ዛፎችን ቆርጦ  ለመሸጥ ጨረታ ያወጣ በመሆኑ እና ዛፎቹም የቤተክርስቲያኗ ንብረት ናቸው ብንልም ሊቀበሉ ባለመቻላቸው ፤ እንዲሁም በጥር 12 2003 ዓ.ም ሁከት የፈጠሩባቸው  መሆኑን በመጥቀስ ዛፍ እንዳይቆረጥ በሕግ ይወገድልን በማለት በልደታ ምድብ 7ኛ ፍትሐ ብሔር ችሎት ክስ መስርታ ነበር፡፡

ተከሳሽ በበኩሉ በ14/06/2003 ዓ.ም በሰጠው ምላሽ ከሳሽ በዛፎቹ ላይ መብት የለውም፡፡ በ1988 ዓ.ም ጀምሮ የተከሳሽ መብት ሆኗል፡፡ አሁን ከሳሽ ይዞታ ነው ያለው ቦታ እና ዛፍ ከ1988 ዓ.ም ጀምሮ የተከሳሽ ሆኗል፡፡ ከመስተዳድሩ በመረከብ ያሉትን ዛፎች በጨረታ በመሸጥ በአገር በቀል ዛፎች በመተካት ወደ ብሔራዊ ፓርክነት የመለወጥ ስራ በመስራት ላይ ይገኛል፡፡ ሕጋዊነት በተላበሰ መልኩ ያወጣነው ጨረታ በመሆኑ የሚያደናቅፍ ምክንያት የለም ፤ ቤተክርስቲያኗ ምንም መብት ሳይኖራት ባለመብት በመምሰል ያቀረበችው ክስ በመሆኑ ልንከሰስ አይገባም በማለት መከላከያ አቅርቦ ነበር፡፡
ጣልቃ የገባውም የአዲስ አበባ መስተዳድር አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን በበኩሉ በ26/12/03 ዓ.ም ባቀረበው አቤቱታ ከሳሽ መብት የለውም ጉዳዩን ማየት የሚችለው የከተማ ፍርድ ቤት ነው፡፡ በተሰጠኝ ካርታ መሰረት ዛፎቹን ለመቁረጥ ጨረታ ማውጣቱ ሁከት አይደለም፡፡ የከሳሽ ይዞታ ስላልሆነ ሁከት የለም በማለት መልስ ሰጥቷል፡፡
የከሳሽና የተከሳሽን ክርክር ማስረጃ በማቅረብ የተመለከተው የልደታው ፍርድ ቤት በሰጠው ብይን ላይ እንደሰፈረው  ፤ ጣልቃ ገብም ሆነ ተከሳሽ እንዲሁ በወረቀት ላይ የሰፈረው ካርታ  ይዘው የከሳሽ ይዞታ ራሱ ተጠቃሎ ባለበት ሁኔታ  ዛፍ እንቆርጣለን በሚል ጨረታ  ማውጣታቸውን ተገቢ ነው መባሉ የሚደርጉት ነገር ኃላፊነት የጎደለው በመሆኑ ያቀረቡት መቃወሚያ ሆነ ክርክር በማይታበል ሁኔታ ለመብታቸው ለመብታቸው የሚናገርላቸው ባለመሆኑ ተቀባይት የለውም ብሏል፡፡
የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በቁር 184150 መዝገብ በሰጠው የፍርድ ውሳኔ መሠረት
1ኛ. ተከሳሽም ሆነ ጣልቃ ገቡ በያዙት ካርታ ብቻ ተመርተው የከሳሽ ይዞታ በሆነው በተከሳሽ በአግባቡ ተለይቶ ባልተሰጠው ይዞታ ላይ ያለውን ዛፍ በመቁረጥ ያወጣውን ጨረታ እንዲቆም እና በጥር 12 ቀን 2003 ዓ.ም ያደረገውን ይህንኑ ሁከት እንዲያስወግድ አዟል፡፡

2ኛ. ተከሳሽ በራሱ ይዞታ ለመጠቀም ከፈለገ በመጀመሪያ በካርታው በሰረት የራሱን ይዞታ በመሬት ላይ በማስፈር  የወሰን ድንጋይ እንዲለይ ታዟል፡፡

3ኛ. ከሳሹ ወጪ እና ኪሳራውን ማቅረብ ይችላል፡፡
ይህን የልደታ ፍርድ ቤት ውሳኔ በመቃወም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር  አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ለፌደራል ከፍተኛው ፍርድ ቤት በመዝገብ ቁጥር 118925 ሰኔ 2004 ዓ.ም አቤት ቢልም ፤ ከፍተኛ ፍርድ ቤቱ ሐምሌ 5 2004 ዓ.ም በሰጠው ብይን የሥር ፍርድ ቤቱ የሰጠውን ውሳኔ የሚነቀፍበት ምክንያት ስለለሌ በፍ/ሥ/ ሕ//ቁ 337 መሰረት ተዘግቷል ሲል  ፋይሉን ወደ መዝገብ ቤት እንዲመለስ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡
በመቀጠልም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አካባቢ ጥበቃ እና የኢትዮጵያ ቅርስ ባለአደራ ማኅበር በጣምራ በሰበር ችሎት በመዝገብ ቁጥር 83743 የካቲት 25 ቀን 2005 ዓ.ም አቤቱታ አቅርበዋል፡፡ ሰበር ችሎትም በሰጠው ውሳኔ የፌደራል መጀመሪያ ፍርድ ቤት  በመዝገብ ቁጥር 184150 መጋቢት 13 ቀን 2004 ዓ.ም ተሰጥቶ በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመ/ቁጥር 118925 ሰኔ 05 2004 ዓ.ም የፀናው ውሳኔ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ ቁጥር 348 (1) መሰረት ጸንቷል ብሏል፡፡ እንዲሁም የአመልካች የሰበር አቤቱታ የመሰረታዊ ሕግ ስህተት መመዘኛን የሚያሟላ ባለመሆኑ ተቀባይነት የለውም  ብለናል ሲል መዝገቡን ዘግቶ ወደ መዝገብ ቤት መልሶታል፡፡
ርዕሰ አድባራት የመንበረ ጸሐይ እንጦጦ ማርያም ቤተክርስቲያን የተመሰረተችው ከ135 ዓመታት በፊት ሲሆን ኅብረተሰቡን በማስተባበር እስከ አሁን ድረስ አካባቢዋን በባህር ዛፍ በመሸፈን የአካባውን አየር ንብረት በመጠበቅ ላይ ትገኛለች፡፡

1 comment:

  1. ብላቴናዋ ከጀርመንApril 12, 2013 at 2:37 AM

    እግዚአብሔር ይመስገን! ለነሱ ግን ይሄጠጋጠጋ እቃለማንሳት ነው የሚለውነ ተረት ማስታወስ ሳያስፈልጋቸው አይቀርም ላላጡት ቦታ ቤተክርስቲያንን መጋፋት ምነው አበዙ

    ReplyDelete