(አንድ አድርገን ሚያዚያ 7 2005 ዓ.ም)፡- በአዲስ አበባ ባለፉት አስርት አመታት ውስጥ ከተቆረቆሩት አብያተ ክርስቲያናት አንዷ አጉስታ ደብረ ጽዮን ቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያን አንዷ ነች፡፡ ይች ቤተ ክርስቲያን በምዕራብ አዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ውስጥ በጦር ኃይሎች ወይራ ቤተል መንገድ አውጉስታ ልብስ ስፌት ፋብሪካ አካባቢ ትገኛለች፡፡ ቀደም ሲል ከንጉሠ ነገሥቱ ዘመን ጀምሮ ቤተ ክርስቲያኒቱ ያረፈችበት ቦታ ‹‹የቢስ ግቢ›› እየተባለ ይጠራ ነበር፡፡ ከዚያም ጊዜ በኋላ ለቀድሞ መንግሥት ደርግ ለከፍተኛ ሹማምንቱ እና ባለሥልጣናቱ ለመኖሪያ ቤት መስሪያነት ቦታውን ቢሰጥም ‹‹ግቢው ከብዶናል እዚህ ግቢ ውስጥ ቤት አንሰራም››በማለት ቦታው የተመሩት ሰዎች በአንድም ይሁን በሌላ ምክንያት ቤት ሳይሰሩበት ቦታውን ትተው ሊሄዱ ችለዋል፡፡ ከዚህ በኋላ መንግሥት ለአካባቢው ልጆች እንዲማሩበት ለትምህርት ቤት ቦታውን ቢፈቅድም የአካባቢው ማኅበረሰብ ልጆቻቸውን እዚህ ቦታ ማስተማር ባለመፍቀዳቸውና ለመንግስትም አቤቱታ በማሰማታቸው ትምህርት ቤትም ሊሰራበት አልቻለም ፡፡ ይህም አቤቱታ የተመለከተው መንግሥት በአካባቢው ላይ ሌላ ቦታ ላይ ‹‹ትንቢተ ኤርሚያስ›› በመባል የሚታወቀው ትምህርት ቤት ሊመሰርትላቸው ችሏል፡፡ ቦታው ወጣቶችና ህጻናት የኳስ መጫወቻ አድርገውት እንደነበር ለተወሰነ ጊዜም ባዕድ አምልኮ ይፈጽሙበት እንደነበር ቦታውን የሚያውቁት አረጋውያን አባቶች ይናገራሉ፡፡ ይሁን እንጂ የመማጸኛ ከተማ ተብሎ በመጽሐፍ ቅዱስ እንደተጻፈ ሁሉ ከብዙ ቦታዎች ይልቅ ይህ ቦታ ለህሙማን መፈወሻ ፤ ሀዘን ለገባቸው ማረጋጊያና የመንፈስ ቅዱስ ማደሪያ አድርጎ በእግዚአብሔር ስለተመረጠ ለዘመናት በመጠበቅ አሁን ላይ በመድረስ የተዓምራት መገለጫና መታያ ቦታ ሊያደርጋት ችሏል፡፡
ይህ እንዲህ እንዳለ የአካባቢው ምዕመናን ሥርዓተ አምልኮ የሚፈጽሙበትና እግዚአብሔርን የሚያመልኩበት ሥፍራ በመራቁ ምክንያት ፤ ህጻናት የሥላሴን ልጅነት የሚያገኙበት ፤ ወጣቶች ስርዓተ ቤተክርስቲያንን የሚማሩበት ፤ ስብከተ ወንጌልን የሚያገኙበት ፤ አረጋውያን አባቶች በቦታ ርቀት ምክንያት ስጋወ ወደሙ የሚቀበሉበት ቤተክርስቲያን በመራቁ ምክንያት ለበርካታ ጊዜያት ሲጨነቁ ይኖሩ ነበር፡፡ ‹‹ጊዜ ሲደርስ አምባ ይፍረስ›› እንዲሉ ከዚህ ሁሉ ነገር በኋላ በእመቤታችን ፍቃድ እዚህ ቦታ ላይ ከአስራ አንድ ዓመት በፊት ጥቅምት 24 1994 ዓ.ም ደብረ ጽዮን ቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያን ልትመሰረተ ችላለች፡፡
ታቦተ ጽዮን በአጉስታ አካባቢ ከገባችበት ጊዜ ጀምሮ አካባቢው ከእመቤታችን ፈውስና በረከት እየተጎበኝ ይገኛል፡፡ ቀደም ሲል አቃቂ ተብሎ የሚጠራው ወንዝ ውስጥ ብዙ ሰዎች እየገቡ ይሞቱ የነበሩበት ሁኔታ በእመቤታችን ጠባቂነት በአሁኑ ሰዓት ሙሉ ለሙሉ ሊወገድ ችሏል፡፡ ለአስርት አመታት መድሃኒት ካልተገኝለት ከኤች.አይ.ቪ በሽታና በተጨማሪ ተላላፊ ካልሆኑ በሽታዎች መካከል ከስኳር ፤ ከአስም ፤ ከልብ ህመምና ከካንሰር በሽታ የእመቤታችንን ጸበል በመጠመቅና በመጠጣት ብዙ ህመምተኞች እንደዳኑም አስተዳዳሪው መልአከ መዊዕ ስብሀት ባይህ ይገልጻሉ፡፡ የደብሩ ስታስቲክስ ክፍል መረጃ እንደሚያመለክተውም በጸበሏም ተጠምቀው ከዳኑት ሰዎች መካከል እስከ አሁን 15 የሚሆኑ ሙስሊሞች አምነው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን እምነት አባል ለመሆን በቅተዋል፡፡
የዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ 6፥54-56 ላይ ‹‹ሥጋዬን የሚበላ ደሜንም የሚጠጣ የዘላለም ሕይወት አለው ፤ ሥጋዬን የሚበላ ደሜንም የሚጠጣ በእኔ ይኖራል እኔም በእርሱ እኖራለሁ።›› የሚለውን በወንጌል ቃል መሠረት በማድረግ በአሁኑ ወቅት ደብረ ጽዮን ቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያን የበርካታ ምዕመናን ስጋወ ደሙ መቀበያ ቤተክርስቲያን ልትሆን ችላለች ፡፡ በወትሮ ቀን የተቀባዩን ምዕመን ሰልፍ ከቤተ ክርስቲያኒቱ በራፍ መውጫ ላይ ሲሰለፉ ማየት ያልተለመደ ቢሆንም ፤ ባለንበት የአብይ ጾም ግማሽ በደብረ ዘይት ዕለት ግን ምዕመኑ እጅጉን ስለበዛ ከቤተክርስቲያኗ የውስጥ መውጫ በር እስከ ዋናው የቤተክርስቲያን መግቢያ የውጭ በር ድረስ ስጋው ደሙ ለመቀበል ተሰልፈው መመልከት ችለናል ፡፡ በሁኔታውም እጅጉን ተገርመናል ፤ ይህን ያህል ሰልፍ ስጋወ ደሙ ለመቀበል የምንመለከተው በነሃሴ 24 በደብረ ሊባኖስ አቡነ ተክለሃይማኖት ገዳም ነበር፡፡
ከሦስት ወር በፊት በወርሀ ጥር በአስራ አራተኛው ቀን 2005 ዓ.ም መነሻው እስከ አሁን ባልታወቀ ምክንያት ቤተክርስቲያኒቱ የእሳት አደጋ ደርሶባት ነበር ፡፡ አደጋው የደረሰበት ቀን እና ሰዓት ሰዎች በስራ ምክንያት በአካባቢው የማይገኙበት በመሆኑ እሳቱ ቤተክርስቲያኒቱ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማድረስ ችሏል፡፡ መዝሙረ ዳዊት 69፤35 ‹‹እግዚአብሔር ጽዮንን ያድናታልና›› እንዲል ታቦተ ልደታ ለማርያም ፤ ታቦተ ዮሐንስ መጥምቅና የቅዱስ ኡራኤል ጽላቶች አንዳች እሳት ሳይነካቸው በተዓምር ከአደጋው ሊተርፉ ችለዋል፡፡ በተጨማሪም አባቶች ለአገልግሎት የሚጠቀሙባቸውታአምረ ማርያም ፤ መጽሐፈ ስንክሳር ፤ መጽሐፈ አርጋኖ ፤ ገድለ ዮሐንስ መጥምቅ ፤ መጽሀፈ ቅዳሴና የተለያዩ መጠን ያላቸው የእንጨት መስቀሎች በእሳቱ ብዙም ጉዳት ሳያደርስባቸው ለምልክት ያህል በመለብለብ ብቻ ሊተርፉ ችለዋል፡፡ የቤተክርስቲያቱ ምሰሶ እንጨት ሆኖ ሳለ እሱ ወደ አመድነት ሲቀየር አባቶቻችን ምዕመኑን የሚባርኩበት መስቀል የእሳት ነበልባል ብቻ አርፎበት መትረፉ ሁሉን አስገርሟል ፡፡ ከእሳት የተረፉት መስቀሎች በነሀስ በብር እና በብረት የተሰሩ ቢሆኑ ኖሮ ለመትረፋቸው በርካታ ምክንያቶች በተሰነዘሩ ነበር ግን አልሆነም ፡፡ ቤተክርስቲያኒቱ የተሰራችበትን የግድግዳ ማገር ፤ ቆርቆሮ እና እንጨቶች ላይ ወደ አመድነት የመቀየር አቅም የነበረው እሳት የእግዚአብሔር ስም የሰፈረበት የእመቤታችን ውዳሴ እና ምስጋናን ፤ የጻድቃን የሰማዕታትና የመላእክትን ምስጋና የተሸከሙ መጻህፍት ላይ ይህ ነው የሚባል ጉዳት አለማድረሳቸው ተአምር ሆኖ አልፏል፡፡ በወቅቱ አንድ አባት የደረሰውን ጉዳት በመመልከት አንገታቸውን እየነቀነቁ ‹‹እግዚአብሔር በጽዮን ታላቅ ነው›› መዝሙረ ዳዊት 76፤2 ፤ ‹‹ማደሪያውም በጽዮን ነው›› መዝሙረ ዳዊት 76፤2 የተባለው ‹‹እሳቱን እንዴት እሳት ይበላዋል?›› በማለት የሆነው ነገር አይተው ሁኔታውን አድንቀዋል፡፡
ከቃጠሎ በኋላ የተሰራችው ቤተክርስቲያን
ከእሳት የተረፉ መጻህፍት በጥቂቶቹ
ይህን የእመቤታችን ተዓምር ይገለጽ እና ምዕመኑም ያውቀው ዘንድ የደብሩ ሰበካ ጉባኤ አስተዳደር ጽ/ቤት እና የአካባቢው ምዕመን አንድ ላይ በመሆን ‹‹ተአምሯን አንቀብርም ›› በሚል አርዕስት ከነደደው እሳት ሳትቃጠል በተዓምር የወጣችው የእመቤታችንን ታቦትና ልዩ ልዩ ንዋየ ቅድሳት ምክንያት በማድረግ ታላቅ ጉባኤና የቅኔ ምሽት በቀጣይ እሁድ ሚያዚያ 13 ቀን 2004 ዓ.ም ከቀኑ 10 ሰዓት ጀምሮ አዘጋጅተዋል፡፡ በመርሐ ግብሩ ላይ ከነደደው እሳት የተረፉ ንዋየ ቅድሳትን ለምዕመኑ የማሳየት ዝግጅት እንደሚኖረው ለማወቅ ተችሏል፡፡ በመርሐ ግብሩ ላይ ብጹአን ሊቃነ ጳጳሳት ፤ የመንፈሳዊ ኮሌጅ መምህራን ፤ ታላላቅ የቅኔ ምሁራን ፤ የድጓ እና የአቋቋም መምህራንና ዘማሪዎች ይገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ እርስዎም በዚህ ጉባኤ ላይ በዕለቱ ተገኝተው በተዓምር ከእሳት የወጡ ታቦታትን እንዲሳለሙ ፤ ልዩ ልዩ ንዋየ ቅዱሳትን በአካል እንዲጎበኙና በረከት አግኝተው እንዲመለሱ በታቦተ ጽዮን ስም ተጋብዘዋል፡፡
ከእሳት የተረፈ መስቀል አንዱ(መሀል ላይ ያለውን ይመልከቱ)
ከእሳት የተረፉ ጥቂት መስቀሎች
በጉባኤው ላይ መገኝት ለማትችሉ በሀገር ውስጥና ከሀገር ውጪ የምትገኙ እህቶችና ወንድሞች የደብሩ ሰበካ ጉባኤ መርሐ ግብሩን በቪዲዮ በመቅረጽ የሆነውንና የተደረገውን ተዓምራት አይተው ያደንቁ እምነትዎንም ያጸኑ ዘንድ ፤ ተዓምራቱን በመጽሄትና በጋዜጦች በወቅቱ የነበሩትን የአይን እማኞችን ተዓማኒ በማድረግ ለማሰራጨት እንዳሰበም ለማወቅ ተችሏል፡፡
አዲሱን ህንጻ ቤተክርስቲያኑን የሚመለከት
በአሁኑ ሰዓት ደብረ ጽዮን ቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያን የተጀመረ አንድ ትልቅ ቤተክርስቲያን በግቢው ውስጥ ይገኛል ለዚህ ቤተክርስቲያን የመሠረት ድንጋይ የተጣለው በአቡነ ጳውሎስ ፕትርክና ዘመን ከአራት አመት በፊት መሆኑን ቦታው ላይ የሰፈረው ጽሁፍ ያመለክታል፡፡ ይህ ቤተክርስቲያን በአሁኑ ሰዓት አዲስ አበባ ውስጥ ካሉት አስርት አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ በዲዛይንም ሆነ በውስጡ ስፋት በደረጃ ውስጥ የሚቀመጥ ነው፡፡ ከአራት አመት በፊት ሲጀመር የግንባታ ወጪው ከአስራ አንድ ሚሊየን ብር በላይ ይፈጃል ተብሎ ተገምቶ ነበር፡፡ አሁን ላይ በየሳምንቱ ምዕመኑ እጁን ባለማሳጠር የአቅሙን በየሳምንቱ ቢዘረጋም የግንባታው በኮንስትራክሽን እቃዎች ንረት ምክንያት የመዘግየት ሁኔታ ይታይበታል ፤ በአሁኑ ወቅት ትልልቅ ስራዎች ተጠናቅቀው የመጨረሻ ምህራፍ የያዘ ቢመስልም ከፍተኛ ወጪ እንደሚጠብቀው ግን ከባለሙያዎች ለማወቅ ተችሏል፡፡ ደብሩ በዜና ማሕደረ ስብሐት ጋዜጣ ላይ ጥር 21 2006 ዓ.ም እግዚአብሔር ቢፈቅድ ሥራ ተተናቅቆ ታቦተ ሕጉ ለማስገባት አስቧል ፡፡ ምዕመናን ስማችሁን በሰማያዊ መዝገብ ታጽፉ ዘንድ የህንጻ ቤተክርስቲያኗን ግንባታ ከፍጻሜ ለማድረስ ይቻል ዘንድ አቅም በፈቀደ ሁሉ ትብብራችሁ እንዳይለየን ሲል በቤተክርስቲያኒቱ ስም ጥሪውን አስተላልፏል፡፡
በመሰራት ላይ ያለው ቤተክርስቲያን
ለበለጠ መረጃ የደብሩን የስብከተ ወንጌል ኃላፊ በዚህ ስልክ ማነጋገር ይችላሉ ..0912-629177
መርዳት የሚቻልበት መንገድ ከደብሩ አስተዳደር ጋር በመነጋገር ወደፊት እንጠቁማለን
ቸር ሰንብቱ
‹‹ተዓምሯን አንቀብርም››