Sunday, March 24, 2013

የፓትርያርኩ አስመራጭ ከምርጫ በፊትና ከምርጫ በኋላ… … . ምን ይላሉ ?

  • ነፃ መሆናችንን የሚያረጋግጠው እግዚአብሔርና ሕሊናችን ነው፡፡ በሙሉ ህሊናዬ በመተማመን የምናገረው አንዳች የሚፀፅተኝ ነገር አለማድረጌ ነው፡
  • ማኅበረ ቅዱሳን አቡነ ጳውሎስ ሹመት ከቀኖና ውጪ ነው በማለት ተቃውሞ አያውቅም፡
  • ማኅበረ ቅዱሳን ለምርጫው አመራር ላክ ተብሎ ቢነገረው እንኳ እኔን ይልከኝ እንደነበር በእርግጠኘነት መናገር እችላለሁ፡
  • መንግሥት ጣልቃ አልገባም ፤ “የማይተማመኑ ባልንጀሮች በየወንዙ ይማማላሉ” ይባላል፡፡ ከአሁን በኋላ ይህን ጥያቄ እንድትጠይቀኝ አልፈልግም፡፡(ከምርጫ በፊት
  • ጫናዎች አልነበሩም ማለት አልችልም…(ከምርጫ በኋላ
  • ሕጉ ተጣሰ ከተባለም ሕጉን የጣሰው አስመራጭ ኮሚቴው ሳይሆን መርሀ ግብሩ እንዲጸድቅ ያደረገው ሲኖዶሱ ነው፡
  • እኛ አቡነ ማትያስ ኢትዮጰያዊ ዜጋ መሆናቸውን ደብዳቤም በለው ምንም እስከተመለከትን ድረስ አምነንበታል፡፡
(አንድ አድርን መጋቢት 16 2005 ዓ.ም)፡- ከሳምንታት በፊት ስድስተኛ ፓትርያርክ አድርጎ አቡነ ማትያስን በመምረጥ የተጠናቀቀው የምርጫ ሂደት ውስጥ ሲኖዶሱ ምርጫውን እንዲያከናውኑ አስመራጭ ኮሚቴ አድርጎ ከሾማቸው ሰዎች ውስጥ ባያብል ሙላቴ አንዱ ነው፡፡ ባያብል ከአስመራ ዩኒቨርሲቲ በአካውንቲንግ የመጀመሪያ ድግሪ እና በማኔጅመንት ኢንፎርሜሽን ሲስተም ሌላ ድግሪ እንዳለው የትምህርት ፕሮፋይሉ ይናገራል፡፡ በአሁኑ ሰዓት በኮንስትራክሽን ባንክ የመምሪያ ኃላፊ እና በማኅበረ ቅዱሳን ስራ አመራር ደረጃ እየሰራ ይገኛል፡፡

ባያብል ከምርጫው በፊት ከአዲስ ጉዳይ መጽሔት ጋር ፤ ከምርጫ በኋላ ደግሞ ከላይፍ መጽሔት ጋር ቃለ መጠይቅ አድርጎ ነበር ፡፡ ከምርጫው በፊት የተከናወነው ቃለ መጠይቅ ከምርጫው በኋላ ጋር ሲተያይ አንዳንድ የሚጣረሱ ነገሮችን ማስተዋል ችለናል፡፡ ባያብል ለአንዳንድ ጥያቄዎች የሰጠው መልስ ከሲኖዶስ ሳይሆን ከቤተመንግሥት የተወከለም ይመስል ነበር ፤ ለአንዳንዱ ደግሞ ለፖሊስ እንጂ ለጋዜጠኛ ቃል የሚሰጥ አይመስልም ፡፡ ምርጫው ፍትሀዊ መሆኑን ለመግለፅ ድምጽ መስጫ ሳጥኑን መስታወት መደረጉን እንደ ምክንያት ያስቀምጣል፡፡ አቡነ ሳሙኤል ግማሽ ሚሊየን ብር መድበው ቅስቀሳ አድርገዋል የተባለውን ፤ ጋዜጦች ተቀባብለው ሲዘግቡት የነበረውን ፤ አቡነ ሳሙኤልም መልስ የሰጡበትን ጉዳይ የሕዝብ ግንኙነትና የምርጫ አስፈጻሚ ሳለ ወሬውን አልሰማሁም ብሏል፡፡ ትንሽ ቆይቶም “መረጃ የተባለውን ሁላ እንሰማለን እንከታተላለን” ሲል ይስተዋላል፡፡  የተለያዩ ብሎጎች ሁኔታውን በወቅቱ በመመልከት ስድስተኛው ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ እንደሚሆኑ አስረግጠው የተናገሩትን መሠረተ ቢስ በማለት አጣጥሏል፡፡ በመጀመሪያው ቃለ ምልልስ ላይ አስመራጭ ኮሚቴው ምንም አይነት ተጽህኖ እንደሌለበት ገለጾ ነበር ፤ ከምርጫ በኋላ ባደረገው ቃለ ምልልስ ግን ‹‹ጫናዎች አልነበሩም ማለት አልችልም፡፡ ነገር ግን ይህ ጫና ከመስፈርቱ ውጪ እንድንሰራ አላደረገንም›› ብሏል፡፡  3.66 ሚሊየን ብር የተመደበለት ምርጫ 1.7 ሚሊየን ብር በመጠቀም ሁለት ሚሊየን ብር ለስኖዶሱ እንደመለሱም ገልጿል ፤ ይህንም በቤተክህነት አካባቢ ያልተለመደ ነገር በማለት ገልጿታል፡፡ ይህ እውነት ነው ከቤተክህነት የሚወጣ ብር እንጂ የሚመለስ ብር መመልከት ያልተለመደ ነገር ነው፡፡ ችግሮቹ እንዳሉ ሆነው ባያብል ለመጽሔቶች ቃለ መጠይቅ መስጠቱ ያስመሰግነዋል፡፡ቃለ መጠይቁን እንደሚከተለው አቅርበነዋል…


ከምርጫ በፊት የነበረው ቃለ መጠይቅ 
አዲስ ጉዳይ፡- በአስመራጭ ኮሚቴ ውስጥ እንዴት ልትገባ ቻልክ ?
          ወደዚህ ዝርዝር ውስጥ ባልገባ ጥሩ ነው፡፡
አዲስ ጉዳይ፡- እያወራን ያለነው ስለ አስመራጭ ኮሚቴ ስለሆነ እንዴት ልትገባ ቻልክ ተብሎ ቢጠየቅስ?
          ሲኖዶሱ መረጠኝ፡፡
አዲስ ጉዳይ፡- በምን መስፈርት?
          እኔ ምንም የማውቀው ነገር የለም ብቻ ተመርጠሀል የሚል  ደብዳቤ ደርሶኝ ነው ማገልገል የጀመርኩት፡፡
አዲስ ጉዳይ፡- ማንን ወክለህ ?
          ወጣቶችን ወክዬ ነው ተመረጥኩት፡፡
አዲስ ጉዳይ፡- የአስመራጭ ኮሚቴ እንዴት ነው የሚመረጠው?
ከተለያዩ አካላት ሲኖዶስ በግልጽ ባስቀመጠው ሕግ መሰረት ነው የተመረጥነው፡፡ ያ ማለት ሁሉንም የቤተክርስቲያን አካላት የወከለ መሆን አለበት፡፡ በዚህ መሰረት ከሲኖዶስና ከሊቃነ ጳጳሳት አራት ፤ ከምዕመናን ሶስት ፤ ከታዋቂ አድባራትና ገዳማት  ሁለት ፤ ከማኅበረ ቅዱሳን አንድ ፤ ከሰንበት ት/ቤቶች አንድ እነዚህ ሲደመሩ አስራ ሶስት አባላት  መሆን እንዳለበት በሕጉ ላይ ተቀምጧል፡፡ በዚሁ መንገድ ነው የተመረጥነው፡፡
አዲስ ጉዳይ፡- ከዚህ አኳያ አንተ ማንን ነው የወከልከው?
          ማኅበረ ቅዱሳንን ነው የወከልኩት፡፡
አዲስ ጉዳይ፡- መጀመሪያ ላይ እጩ የነበሩት ስንት ናቸው?

በዕጣው የተጠቆሙት ሰላሳ ስድስት ነበሩ፡፡ ከሰላሳ ስድስቱ በጤናና በእድሜ ወይንም በምርጫ ሕጉ ላይ በተቀመጠው መሥፈርት መሰረት አስራ ዘጠኙ ነው የገቡት ፡፡ ከአስራ ዘጠኙ እንደገና ወደ ስምንት አውርደናቸዋል፡፡ይህ የሆነው የእያንዳንዱ ታሪክ ተነቦ ነው፡፡
 
አዲስ ጉዳይ፡- ለምሳሌ ስምንቱ እነማን ነበሩ?
          አምስቱ ተገልጸዋል ሶስቱን መናገር አስፈላጊ አይደለም፡፡

አዲስ ጉዳይ፡- የሚያመጣው ችግር አለ?
እስካልተመረጡ ድረስ የሰዎችን ልብ መስቀል አስፈላጊ አይደለም፡፡ በጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ይህ ተጠይቆ ነበር፡፡ ነገር ግን አስፈላጊ ሆኖ ባለመገኝቱ ምላሽ አልሰጠንበትም፡፡

አዲስ ጉዳይ፡- በዓለማዊ ምርጫ ሰዎች በሰጡት ድምጽ ነው መሪዎች የሚመረጡት ቤተክርስቲያኗን የሚያስተዳድራትስ?

          ሕጉ ላይ በተቀመጠው መስፈርት መሰረት ነው፡፡
አዲስ ጉዳይ፡- የመጭበርበር ሁኔታዎች ሊፈጠሩ አይችሉ ?     

እንዴት? መጀመሪያውኑ መጭበርበር የሚባለውን ሀሳብ ምን አመጣው? ይህ እንዳይሆን እኮ ነው በግልጽ እንዲታይ ብለን መስታወት ያደረግነው፡፡ በተጨማሪም ታዛቢዎችና አስመራጮች ባሉበት በግልጽ ይቆጠርና አሸናፊው ወዲያው ይገለጻል፡፡

አዲስ ጉዳይ፡- ፍሕታዊ የሆነ ምርጫ እናካሂዳለን ብላችሁ ታምናላችሁ?
በትክክል በትክክል.. ፍሕታዊ የሆነ ምርጫ እናካሂዳለን፡፡ ታምናላችሁ ብቻ ሳይሆን ሕጉ የተዘጋጀው ለዚህ ብቻ ነው፡፡
አዲስ ጉዳይ፡- ሕጉ ይተገበራል ?
ይተገበራል

አዲስ ጉዳይ፡- አምስቱ እጩ ተመራጮች መካከል የሚመረጠው እየታወቀ አራቱን ምርጫ ውስጥ የሚከቷቸው ሆን ብለው ነው፡፡ የሚሉ ቅሬታዎች እየተሰሙ ነው፡፡
ይሄ የብሎጎች ወሬ ነው፡፡ አስመራጭ ኮሚቴው የሚሰራው ሥራ 99 በመቶ ውሸት ነው ብለው ያወራሉ፡፡ ይህ ደግሞ በእኛ ላይ የሚፈጥረው አንዳችም ተጽህኖ የለም፡፡

አዲስ ጉዳይ፡- ወሬው ምንም ጫፍ ሳይኖረው ነው እየተወራ ያለው?
ምንም መሠረት የላቸውም ፡፡ ይህንን የሚያጠናክር ጥቆማ በምንቀበልበት ጊዜ 2791 ድምጽ ያገኝን ሲሆን ብሎጎች (ሐራ ብሎግ) ግን 9ሺህ ብለው ጽፈዋል፡፡ እንደውም 9ሺህ ብለን የነበረው ተሳስተናል ብሎ በጋዜጣዊው መግለጫ መሰረት አስተካክሏል፡፡ 

አዲስ ጉዳይ፡- ይህንን አባት ምረጡ የሚል ትዕዛዞች አይተላለፉም ?
በፍጹም እንዲህ ሊደደረግ አይችልም፡፡

 አዲስ ጉዳይ፡- ለምሳሌ ብጹዕ አቡነ ሳሙኤል ሰሞኑን በሰጡት ቃለምልልስ “ይህንን ሰው ምረጡ እየተባልን ቤታችን ይንኳኳ ነበር” የሚል ነገር ተናግረዋል፡፡

እንግዲህ እኔ መራጭ ሳልሆን አስመራጭ ነኝ፡፡ ይህንን ምረጡ ተብለው ከሆነ እሳቸው በመረጃ ማቅረብ ይችላሉ፡፡ እንደ አስመራጭ ኮሚቴ ግን እኛ የቀረበልን አቤቱታ የለም፡፡

አዲስ ጉዳይ፡- ተመራጮች እኔን ምረጡ ብለው የምርጫ ቅስቀሳ ማካሄድ ይችላሉ ?
ቅስቀሳ ያድርጉ አያድርጉ የሚል ሕግ አልተቀመጠም፡፡

አዲስ ጉዳይ፡- ሕጉ ምንድነው የሚለው ?
          ሕጉ ያደርጋሉ አያደርጉም አይልም ፡፡

አዲስ ጉዳይ፡- አንዳንድ እየወጡ ያሉት ወሬዎች ለምረጡኝ ቅስቀሳ ከግማሽ ሚሊየን ብር በላይ የሰጡ አሉ ይባላል ?
          እኔ አልሰማሁም፡፡

አዲስ ጉዳይ፡- እንደ ሕዝብ ግንኙነትና የምርጫ አስፈጻሚነትህ የሚወጡትን መረጃዎች ማወቅ የለብህም ?
          አልተከታተልኩም ፤ መረጃ አልደረሰኝም፡፡

አዲስ ጉዳይ፡- አስመራጭ ኮሚቴ እስከመሆናችሁ መጠን የሚወጡትን መረጃዎች ማወቅ ግድ ይላል?
መረጃ የተባለውን ሁላ እንሰማለን እንከታተላለን ፤ በየዕለቱ በድረ-ገጾች የሚወጡትን እናነባለን፡፡ ግን የሰማህው ሁሉ መረጃ ነው ማለት አይቻልም፡፡ በማስረጃ እስካልተደገፈ ድረስ ማለቴ ነው፡፡

አዲስ ጉዳይ፡- የሚወጡትን መረጃዎች ትክክል ካልሆኑ ለምን መግለጫ አትሰጡባቸውም ?
እኛ ልናስተባብል የምንችለው የምንሰራውን ስራ በተመለከተ ተቃውሞ ከደረሰብን ትክክለኛውን መረጃ ይሄ ነው በማለት በመግለጫ እናሳውቃለን፡፡

አዲስ ጉዳይ፡- ለምሳሌ አስመራጭ ኮሚቴዎች ነጻ አይደሉም ብለው የጻፉ አሉ፡፡ ለዚህ ምንድነው ምላሽ የምትሰጠው?
          አሉባልታ ……. አሉባልታ ነው::

አዲስ ጉዳይ፡- ግን ነፃ ናችሁ ?
          በትክክለ ነፃ ነን::

አዲስ ጉዳይ፡- ነጻ መሆናችሁን የሚያረጋግጠው ምንድነው?
          ነፃ መሆናችንን የሚያረጋግጠው እግዚአብሔርና ሕሊናችን ነው፡፡

አዲስ ጉዳይ፡- መንግሥት በምርጫው ላይ እጁን አስገብቷል ይባላል?
እስከ አሁን አስመራጭ ኮሚቴው ራሱን እየገመገመ እየሰራ ነው ያለው፡፡ የመንግሥት ጣልቃ ገብነት በውጤትና በስራ ነው የሚታየው፡፡ በዚህ ደረጃ በሙሉ ሕሊና ባለው መልኩ ነው እየተጓዝን ያለነው፡፡ የመንግሥት ጣልቃ ገብነት አለው ተብሎ የሚወራው ነገር ውሸት ነው፡፡

አዲስ ጉዳይ፡- የመንግሥት ጣልቃ ገብነት ቢገጥማችሁ ምን ታደርጋላችሁ ?
መንግሥት እጁን የሚከት ከሆነ አስመራጭ ኮሚቴው ስራውን ያቆማል፡፡

አዲስ ጉዳይ፡- እስከ አሁን ምንም የመንግሥት ጣልቃ ገብነት የለም በሚለው አቋምህ ጸንተሀል ማለት ነው?
አልገባብንም፡፡ የማይተማመኑ ባልንጀሮች በየወንዙ ይማማላ” አይነት ነው፡፡ ከአሁን በኋላ ይህን ጥያቄ እንድትጠይቀኝ አልፈልግም፡፡

ከምርጫው በኋላ የተደረገ ቃለ መጠይቅ
ላይፍ፡- ስድስተኛውን ፓትርያርክ ለማስመረጥ የአስመራጭ ኮሚቴ ውስጥ ስለገቡበት ሁኔታ እንነጋገር፡፡ ማኅበረ ቅዱሳን ማኅበሩን በመወከል በኮሚቴው ውስጥ ተሳተፍ ብሎ ነው የላከህ ? ወይስ በቀጥታ ሲኖዶስ ባያብልን ወክላችሁ ላኩልን የሚል ትዕዛዝ በማስተላለፍ ነው?
ባያብል፡- ሲኖዶሱ የሄደበት አካሄድ አለ፡፡ አስመራጭ ኮሚቴውን ያቋቋመው ከተለያዩ አካላት ነው፡፡ እነዚህ አካላቶች ሰው እንዲልኩ ሳይሆን ቀጥታ የሚልኩትን ሰዎች በመግለጽ እከሌን ላኩ ያለው፡፡ ስለዚህ ከማኅበረ ቅዱሳን እኔ የተመረጥኩት ሲኖዶሱ በላከው ደብዳቤ ባያብልን ላኩልኝ በማለቱ ነው፡፡ የእኔ ውክልና ሙሉ በሙሉ ማኅበሩ በመቀበል አጽድቆልኛል፡፡

ላይፍ፡- ነገር ግን በማኅበራችሁ ውስጥ በዚህ ጉዳይ ከፍተኛ ጭቅጭቅ መስነሳቱንና እኛ የፈለግነውን መርጠን እንልካለን እንጂ እንዲህ አይነት አስገዳጅ ትዕዛዝ መቀበል የለብንም ተብሎ እንደነበር ሰምተናል፡፡
ባያብል፡-  በማኅበሩ አመራር ደረጃ እንዲህ አይነት ነገር አልተካሄደም፡፡ አመራር ላክ ተብሎ ቢነገረው እንኳ እኔን ይልከኝ እንደነበር በእርግጠኘነት መናገር እችላለሁ፡፡ ሲኖዶሱን እኔን የመረጠው ዝም ብሎ አይደለም፡፡ ከዚያ በፊት የምርጫ ሕጉ ውይይት ሲደረግበት ከእኛ ማኅበር ሶስት ሰዎች ተወክለን ነበር፡፡ በዚያ የውይይት መድረክ ላይ ተገኝቼ ይጠቅማሉ ያልኳቸውን ሃሳቦች ስገልጽ  ሊቃነ ጳጳሳቱ ተመልክተውኛል፡፡ ከዚህ በመነሳት እኔ እንድመረጥ ጠይቀዋል፡፡

ላይፍ፡- ማኅበሩ ግን ባያብል ሳይሆን ሌላ ሰው ነውእኔን የሚወክለኝ  በማለት የሲኖዶሱን ውሳኔ የመለወጥ አቅም ነበረው?
ባያብል፡- በሲኖዶስና  በማኅበራችን አመራር መካከል ጥሩ የሚያሰኝ መግባባት አሉ፡፡ የተሰራው በዚሁ መናበብ ነው፡፡ ሲኖዶስ በእርግጥ ማዘዝ ይችላል፡፡ ነገር ግን በታዛዥነትና በአዛዥነት መንፈስ ሳይሆን ነገሩን የተቀበልነው በመግባባት ነው፡፡ 

ላይፍ፡- የማኅበረ ቅዱሳን መመሪያ ደንብ የማኅበሩ አመራር አባል የፖለቲካ ፓርቲ አባል መሆን እንደማይገባው ይደነግጋል፡፡ ነገር ግን እርስዎ የማኅበሩ አመራር ሆነው እያለ የኢህአዴግ ብአዴን አባል መሆንዎ ይነገራል፡፡ ይህ በማኅበሩ ጥያቄ ማስነሳቱንና ብዙ ጭቅጭቅ እንደፈጠረ መረጃዎች አሉ፡፡
ባያብል፡- የገዥው ፓርቲ አባል አይደለሁም፡፡ የብአዴን አባል ብሆን ኖሮ ዛሬ ቀን ድርጅቱ ጠቅላላ ጉባኤውን እያካሄደ በመሆኑ እዚህ አንገናኝም ነበር፡፡እኔ ያለሁት አራት ኪሎ የብአዴን አባላት ግን ባህር ዳር ነው ያሉት ፡፡ ስለዚህ የፓርቲው አባል አይደለሁም፡፡ ማኅበረ ቅዱሳን እንደ አቋም የያዘው አላማ ፖለቲካ ውስጥ አይገባም፡፡ ነገር ግን ማኅበሩ ሁሉ አባላቶቹ በፖለቲካ አይሳተፉም አላለም፡፡ እንደሚታወቀው የማኅበራችን አባላት ከዩኒቨርሲቲ የተመረቁ ወጣቶች ናቸው፡፡ እነዚህን ሁሉ ፖለቲካ ውስጥ አትግቡ ማለት አይቻልም፡፡ ለምሳሌ በእኛ አገር የሚገኙ የሚበዙ ፓርቲዎች የተዋቀሩት በብሔር ነው፡፡ የእኛ ማኅበር አባላት በበኩላቸው በአገሪቱ ከሚገኙ ሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች የተወጣጡ ናቸው፡፡ እኔን በሚመለከት ከኢህአዴግ በፊት ማኅበረ ቅዱሳን ነበርኩኝ፡፡

ላይፍ፡- ከ40 ሚሊየን የሚበልጥ የቤተክርስቲያኒቱ አማኝ በ2791 ጥቆማ ብቻ እንዲወከል የማድረጋችሁ መነሻ ምንድነው?
ባያብል፡-  በስምንት ቀናት ሁሉእንዲጠቁም በሩን ክፍት አድርገናል ፡፡ እኛ ሁለት ሺህ ሰው ነው የሚጠቁመው አላልንም ፤ ከዚህ በፊት በነበረው ምርጫ የሚጠቁሙት ጳጳሳት ብቻ ነበሩ፡፡ አሁን ግን ካህናትና ምዕመናን እንዲጠቁሙ መደረጉን እኛ እንደ እድገት ነው የምንመለከተው፡፡

ላይፍ፡- የጠቋሚዎች ድምጽ 36 ጳጳሳትን በእጩነት እንድትይዙ ከማድረግ ውጪ ምን ፋይዳ ነበረው ? ለምሳሌ አቡነ ሳሙኤል የጠቋሚዎቹን ከፍተኛ ድምጽ አግኝተው ነበር ፡፡ ነገር ግን አምስቱ ውስጥ እንኳን እንዳይገቡ ተደርጓል፡፡
ባያብል፡-  ይህ የጥቆማን ምንነት ካለማወቅ የመነጨ ነው፡፡ አንድ አባት በአንድ ሺህ ሌላው ደግሞ በአንድ ድምጽ ቢጠቆም ብዛቱና ማነሱ ምንም ለውጥ አያመጣም፡፡ 36ቱን ጳጳሳት ካወቅን በኋላ እነዚህን አባቶች በወንፊት ውሰጥ በማሳለፍ ለማጥራት የተለያዩ መለኪያዎችን ተጠቅመናል፡፡ ለምሳሌ እድሜ አቃቢ መንበር በምርጫ አይገባል ፤ ሙሉ አካል ያለው መሆን አለበት ፤ በሚሉት መስፈርቶች መሰረት 19 እንዲቀሩ አድርገናል፡፡ ከ19 ወደ 8 ያወረድንበት ሁለተኛ ማጣሪያ የትምህርት ዝግጅት ፤ የአገልግሎት ልምድ ፤ ፤ የቋንቋ ችሎታና ለቤተክርስቲያን ያለው ቅድስና የሚሉ መስፈርቶች መሠረት ወደ ስምንት ገባን፡፡ ከዚህ በኋላ የስምንቱን መዝገብ በመያዝ ሦስቱን በመነጠል አምስት ምርጥ የሚባሉትን ለይተን አወጣን፡፡ 

ላይፍ፡- አምስቱን በማውጣት ሂደት ውስጥ በአስመራጭ ኮሚቴው መካከል የአቡነ ሳሙኤል ጉዳይ ውዝግብ መፍጠሩ ተሰምቷል፡፡ አቡኑ ብዙ ድምጽ ከማግኝታቸው ባሻገር እርሳቸውን በፓትርያርክነት ማየት የሚፈልጉ ሰዎች ጫና ውዝግብ ውስጥ መቆታችሁ ተነግሯል፡፡
ባያብል፡-  እኛ የሰራነው በተቀመጠው መስፈርት መሰረት ነው፡፡ ጫናዎች አልነበሩም ማለት አልችልም፡፡ ነገር ግን ይህ ጫና ከመስፈርቱ ውጪ እንድንሰራ አላደረገንም፡፡ እኛ ከጠቋሚዎቹ ብዙ ቁጥር ማን አገኝ የሚለውን ለማወቅ እንኳን አልፈለግንም፡፡ ያየነው ቁጥሩን ሳይሆን መጠቆማቸውን ብቻ ነው፡፡

ላይፍ፡- ከ800 በላይ መራጮችች የተመረጡበት መንገድ የምርጫውን ተአማኒነት ጥያቄ ውስጥ የሚከት ስለመሆኑ ይነገራል፡፡ እነዚህ ሰዎች ግልጽ ምርጫ ወይም ውይይት ተደርባቸው የመጡ ሳይሆኑ በጥቂት አመራሮች የተመረጡ ስለመሆናቸው ይነገራል፡፡
ባያብል፡- የተደረገው የውክልና ምርጫ ነው፡፡ ውክልናውን ለማድረግ ሲኖዶሱ ሂደቱ እንዴት መመራት እንዳለበት ደንብ አውጥቷል፡፡ በምርጫው የሚሳተፉ አድባራት ኃላፊዎች ፤ የሁሉም ሀገረ ስብከት ስራ አስኪያጆች ፤ በሲኖዶስ እውቅና የተሰጠው ማኅበረ ቅዱሳን ብቻ በመሆኑ ማኅበረ ቅዱሳንም ወኪሉን እንዲልክ ተደርጓል፡፡ ከካህናት 4 ፤ ከምዕመናን 4 ፤ እያለ ውክልናው በየደረጃው ሄዷል፡፡ እነዚህን ሰዎች የሚመርጠው በየደረጃ የሚገኝ ኃላፊ  ቢሆንም ምርጫውን እኛ የምንመረምርበት መንገድ ነበር፡፡ በውክልና ቅሬታ የቀረበባቸው ሰዎች ነበሩ፡፡ ይህ እንዲቀየር አድርገናል፡፡

ላይፍ ፡- ውክልና የተሰጠበት መንገድ ራሱ ሚዛኑን የሳተ እንደሆነ ይነገራል ፤ ለምሳሌ እያንዳንዱ ሀገረ ስብከት 13 ሰው እንዲወክል ተደርጓል፡፡ ነገር ግን ድሬደዋ ላይ የሚገኝ የገዳምና የምዕመናን ቁጥር አማራ ክልል  ከሚገኝ ገዳምና የምዕመናን ቁጥር ጋር መወዳደር ባይችልም ሁለቱም እኩል 13 ሰዎች እንዲልኩ ተደርገዋል፡፡
ባያብል፡- ያለምንም ልዩነት ለሁሉም ሀገረ ስብከቶች ተመሳሳይ ኮታ መስጠቱ የቅንነት ሀሳብ ነው፡፡ ሁለተኛ ነገር ስምንት መቶ አይደለም ሁለት ሺህ ውክልና ቢኖር ጥሩ ነበር፡፡ ነገር ግን የሰው ቁጥር መብዛቱ ለቤተክርስቲያኒቱ ወጪ ነው የሚሆነው፡፡ ለዚህ ምርጫ ከአሜሪካ ሁላ 6 ሰዎች እንዲመጡ ተደርጓል፡፡ የሁሉንም ወጪ የሸፈነችው ቤተክርስቲያን ናት፡፡

ላይፍ፡- በቤተክርስቲያኒቷ ውስጥ የአንድ ብሔር ተጽህኖ በዝቷል እየተባለ እሮሮ ይሰማልና መራጭ ከተባሉት 806ቱ ሰዎች መካከል የብሔር ተዋጽኦ ምን ያህል እንደሚመስል የፈተሻችሁበት ሁኔታ አለ ?
ባያብል፡- እንደሱ የለም፡፡
ላይፍ፡- ለምን ?

ባያብል፡- በእኛ እምነት ቤተክርስቲያኗ የሁሉም የእግዚአብሔር ፍጡር ቤት ናት፡፡ ቤተክርስቲያኗ ሰውን በፈጣሪ ልጅነታቸው ብቻ ነው የምታምነውና ፤ ከየትኛው ብሔር ነው የሚለውን በጭራሽ አላየንም፡፡ በነገራችን ላይ 5ቱም እጩዎች ከአንድ ብሔር ቢመጡ እንኳን ለምን ሳንል እንቀበል ነበር፡፡

ላይፍ፡- የመጨረሻዎቹ አምስት እጩዎች ሕገ ደንቡ ለሕዝብ ለማስተዋወቅ 15 ቀን መደረገግ አለበት የሚል ቢሆንም እናንተ ግን ያስተዋወቃችሁት ምርጫው ሊደረግ ቀን ሲቀረው ነው፡፡ ይህ ሕጉን መጣስ አይሆንም..
ባያብል፡- እናንተ እየጠቀሳችሁ ያላችሁት ሕገ ደንቡን ብቻ ነው ፡፡ በዚህ ውስጥ የሚፈጠር ማናቸውም አይነት ክፍተቶች እንዲሞላ ሲኖዶስ ለቋሚ ሲኖዶሱ ሥልጣን ሰጥቶታል፡፡ ስለዚህ ይህ ስራ የተሰራው በድርጊት መርሃ ግብሩ መሠረት ነው፡፡ ሕጉ ተጣሰ ከተባለም ሕጉን የጣሰው አስመራጭ ኮሚቴው ሳይሆን መርሀ ግብሩ እንዲጸድቅ ያደረገው ሲኖዶሱ ነው፡፡

ላይፍ፡- አቡነ ማትያስ ምርጫውን አሸነፉ ከመሰኝታቸው አስቀድሞ የተለያዩ ብሎጎች ስድስተኛው ፓትርያርክ እሳቸው እንደሚሆኑ በስፋት ይዘግቡ ነበር፡፡ ግጥምጥሞሹን እንዴት አገኙት?
ባያብል፡-  የአስመራጭ ኮሚቴው ዋናው ፍላጎቱ  ውጤቱ ላይ አልነበረም፡፡ ውጤቱ እግዚአብሔር የፈለገውና የመረጠው እንዲሆን  ለእርሱ የተተወ ነው፡፡ ጥሩ መሪ ለቤተክርስቲያኒቱ እንዲሰጥ ብቻ ነበር የእኛ ፍላጎት፡፡ ከዚህ አንጻር ስለ አቡነ ማትያስ ወይም ስለሌሎች የሚነገረውን ነገር በእኛ ላይ ተጽህኖ እንዳይፈጥር ራሳችንን እንጠብቅ ነበር፡፡ ሂደቱ ክፍተት ኖሮት ለትችት እንዳይዳርገንና እንዳይጣስ ጠንቅቀን ሰርተናል፡፡ ውጤቱ ሰው የጠበቀውና ያልፈለገው ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን እኛ እዚህ ውስጥ አንገባም፡፡

ላይፍ፡- ነገር ግን አስመራጭ ኮሚቴው ራሱ አቡነ ማትያስን ያጎላ እንደነበር ስሞታ ይቀርብበታል፡፡ የአምስቱን እጩዎች የሕይወት ታሪክ ባወጣችሁበት ጽሁፍ ለአራቱ ጳጳሳት አንድ አንድ ገጽ ስትሰጡ ለአቡነ ማትያስ ሶስት ገጽ ሽፋን መስጠታችሁ ተስተውሏል፡፡ ይህ ሆን ተብሎ የተደረገ አይደለም ?
ባያብል፡- ህትመቱን የሚሰራው ሌላ ክፍል ነው፡፡

ላይፍ፡- ነገር ግን እርስዎ የህትመት ክፍሉ ኃላፊ ከመሆንዎ በላይም ህትመቱ ከመሰራጨቱ በፊትና በኋላ ህትመቱን እንደ አሰራጭ ኮሚቴ አባልነትዎ የመመልከት ኃላፊነት አልነበረበዎትም ?
ባያብል፡- ህትመቱ ከመሰራጨቱ በፊት እንዲሰበሰብ ያደረግነው ትክክል እንዳልነበረ በመገንዘባችን ነው፡፡

ላይፍ፡- ህትመቱ የተሰበሰበው ግን ለጋዜጠኞች ጭምር ከታደለ በኋላ ሌሎች እጩዎች ቅሬታ በማቅረባቸው ነበር፡፡
ባያብል፡- ያገድነው ከመሰራጨቱ በፊት ነበር፡፡ ማንም ሰው እጅ አልገባም ፡፡ እኔ እስከማውቀው አልተሰራጨም ፤ ከማተሚያ ቤት እንደወጣ እንዲታገድ ያደረኩትኝ እኔ ነኝ ፤ በማግስቱ በአንድ ቀን ውስጥ አዲስና ሁሉንም ሊያስማማ የሚችል ጽሁፍ እንዲወጣ አድርገናል፡፡

ላይፍ፡- ሕገ ደንቡ ኢትዮጵያዊ የሆነ ጳጳስ ለፕትርክና መወዳደር እንደሚችል በግልጽ ቋንቋ ይደነግጋል፡፡ ነገር ግን አቡነ ማትያስ አሜሪካዊ ዜግነት ያላቸው መሆኑ ይታወቃል፡፡እንዴት በዚህ መስፈርት እሳቸውን ለመስፈር ሳትችሉ ቀራችሁ?
ባያብል፡- ትክክል ሕገ ደንቡ በዕጩነት የሚቀርብ ጳጳስ ኢትዮጵያዊ መሆን እንደሚገባው ያዛል፡፡ በዚህ መነሻነትም አቡነ ማትያስን ጠይቀናል ፡፡ አቡኑ ኢትዮጵያዊ ዜጋ መሆናቸውን አሳይተውናል፡፡

ላይፍ፡- የተመለከታችሁት ግን ከደብዳቤ ውጪ ምንድነው ? በእኛ አገር ዜግነት በደብዳቤ አይመስለንም ፤ አቡኑ በትክክል የአሜሪካ ዜግነታቸውን መመለሳቸውንና ኢትዮጵያዊ ስለመሆናቸው ማረጋገጫ መታወቂያ ወይም ፓስፖርት አሳይቷዋል ?
አቶ ባያብል፡- እኛ አቡነ ማትያስ ኢትዮጰያዊ ዜጋ መሆናቸውን ደብዳቤም በለው ምንም እስከተመለከትን ድረስ አምነንበታል፡፡(ረዥም ሳቅ…)

ላይፍ፡- በምርጫ ዕለት የዕጩዎቹን ጳጳሳት ፎቶግራፍ ስትለጥፉና ስታስተዋውቁ በመጀመሪያ የስቀመጣችሁት የአቡነ ማትያስን ፎቶ መሆኑስ ?
አቶ ባያብል፡- ለመራጮች ገለጻ የሰጠሁት እኔ ነኝ ፤ በዚህ ወቅት በአንደኝነት አቡነ ማትያስ ተቀምጠው ነበር፡፡  እነዚህ ፎቶዎች የተደረደሩት በአጋጣሚ ሳይሆን በቤተክርስቲያኒቱ መመሪያ መሠረት ነው፡፡ ከቀረቡት ጳጳሳት ቀዳሚ የሆኑት አቡነ ማትያስ ናቸው ፤ ከዛ አቡነ ኤልሳ ናቸው ፤ ሌላው ቀርቶ እነዚህ ጳጳሳት በሲኖዶስ ስብሰባ ሲገናኙ የሚቀመጡት በሹመት ቅድምና ነው፡፡ ይህ ሌላ ሰውን ግራ ሊያጋባ ይችላል እንጂ ለጳጳሳቱ እንግዳ ነገር አይደለም፡፡

ላይፍ፡- በአጠቃላይ ለምርጫው የተያዘው በጀትና ወጪ ምን ያህል ነበር ?
አቶ ባያብል፡- 3.66 ሚሊየን ብር ተበጅቷል፡፡ እኔ የባንክ ባለሙያ በመሆኔ ከሌሎች ጋር በመሆን በጀቱን እንዳንቀሳቅስ ተደርጓል፡፡ በጀቱን በአግባቡ ነው የተጠቀምንበት ፡፡ የበጀቱን 47 በመቶ ብቻ ነው የተጠቀምነው፡፡ 1.7 ሚሊየን ብር ብቻ ተጠቅመናል፡፡ ሁለት ሚሊየኑን መልሰን ለሲኖዶሱ ገቢ አድርገናል፡፡ ይህ በቤተክህነቱ ብዙ ጊዜ የሚጠበቅ አልነበረም፡፡ በጀቱን የተጠቀምንበት መንገድ በቀጥታ ከምርጫ ጋር የተያያዘ  የዋለ እንጂ የአስተዳደር ተብሎ የባከነ አይደለም፡፡ 1.4 ሚሊየን ወጪ ያደረግነው ከየሀገረ ስብከቱ ለመጡ መራጮች ነው፡፡ ህትመትና ማስታወቂያ ለማሰራት ወጪ አድርገናል፡፡

ላይፍ፡- ለአምስቱ ጳጳሳት ከምርጫው ጋር በተያያዘ የበጀት ድጋፍ አድርጋችኋል ?
አቶ ባያብል፡- ለጳጳሳቱ ምንም አይነት ገንዘብ አልሰጠንም፡፡

ላይፍ ፡- ማኅበረ ቅዱሳን በፓትርያርክ ላይ ፓትርያርክ መሾሙን በመቃወም አቡነ ጳውሎስን የቤተክርስቲያኒቱን ቀኖና ጥሰው ነው መንበሩን የያዙት በማለት ላለፉት 21 ዓመታት ስትቃወም ቆይታ አሁን እርስዎን ወክሎ መላኩ ተቃውሞውን አንስቶ በዚህ ምርጫ ተስማቶ ነው ?
ባያብል፡- ማኅበረ ቅዱሳን አቡነ ጳውሎስ ሹመት ከቀኖና ውጪ ነው በማለት ተቃዎሞ አያውቅም፡፡

ላይፍ፡- እናንተ አስመራጭ ኮሚቴ ያላችሁት  በእግዚአብሔር ስም ቃለ መሃላ ፈጽማችሁ ነው ?
አቶ ባያብል፡- አዎን፡፡

ላይፍ ፡- በዚህ ምርጫ ሂደት ተሳትፍዎ ለህሊናዬና ለእግዚአብሔር ታማኝ ነበርኩ በማለት ለመናገር የሚያስደፍርዎት ስራ ሰርቻለሁ ብለው ያምናሉ ?
አቶ ባያብል፡- ቤተክርስቲያኒቱን ላለፉት 20 ዓመታት ጠቃሚ ነው የምለውን ነገር ሳበረክት ቆይቻለሁ፡፡ ከዚህ አንጻር በሙሉ ህሊናዬ በመተማመን የምናገረው አንዳች የሚፀፅተኝ ነገር አለማድረጌ ነው፡፡

ላይፍ፡- አመሰግናለሁ፡፡
አቶ ባያብል፡- እኔም አመሰግናለሁ፡፡








           

2 comments:

  1. ባያብል ጥሩ ነው::

    ReplyDelete
  2. andadirgen.you do not like facts simply praise.keep on.

    ReplyDelete