Wednesday, March 20, 2013

የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ተማሪዎች ኮሌጁን በመቃወም ለፓትርያርኩ ደብዳቤ ጻፉ



-    አሥር ችግር ናቸው ያሏቸውን ጥያቄዎች አቅርበዋል
   (Reporter March 20 ):- አራት ኪሎ የሚገኘው የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ተማሪዎች ኮሌጁ እያደረሰባቸው ያለውን ችግር በመዘርዘርና በመቃወም፣ 15 ቀናት በፊት በዓለ ሲመታቸውን ለፈጸሙት ስድስተኛው ፓትርያርክ ለብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ደብዳቤ ጻፉ፡፡
ደብዳቤያቸውን ለቋሚ ሲኖዶስ ጽሕፈት ቤት፣ ለጠቅላይ ቤተ ክህነት፣ ለኮሌጁ፣ ለሰብዓዊ መብት ኮሚሽን፣ ለፌዴራል ፖሊስ፣ ለአዲስ አበባ ወጣቶች ቢሮና ለአራዳ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ግልባጭ ያደረጉት ተማሪዎቹ፣ በኮሌጁ ውስጥ ከዕለት ወደ ዕለት እየተባባሰ መጥቷል ያሉትን አስተዳደራዊና የመማር ማስተማር ሒደት ችግሮች አስታውቀዋል፡፡


ቁጥራቸው 200 በላይ የሚሆኑትና ፔቲሺን ተፈራርመው ቅሬታቸውን ያቀረቡት ተማሪዎቹ፣ ኮሌጁ ለሚጠይቁት ማንኛውም ጥያቄ አፋጣኝ ምላሽ እንደማይሰጣቸው፣ ኮሌጁ ከትምህርት ማዕከልነት ይልቅ የንግድ ማዕከል መምሰሉን፣ የትምህርት ጥራትና የመምህራን ብቃት መፍትሔ ማጣቱን፣ የውኃ መቋረጥ ችግር፣ ተማሪዎች ሲታመሙ ተከታትሎ አለመርዳት፣ ከሌሎች ኮሌጆች ጋር ሲነፃፀር ጥራቱን ያልጠበቀ የጤፍ አቅርቦት፣ የቤተ መጻሕፍት ችግርና ሌሎችንም በደብዳቤያቸው አስፍረዋል፡፡

የጠቀሷቸው ችግሮች ለማሳያ ያህል መሆኑን የገለጹት ተማሪዎቹ፣ ችግሮቹን ተሸክመውና ተቋቁመው የሚሄዱበት ትዕግስታቸው ማለቁን ጠቅሰው፣ ፓትርያርኩ አፋጣኝ መፍትሔ እንዲሰጧቸው ጠይቀዋል፡፡

ተማሪዎቹ ለፓትርያርኩ በደብዳቤ የገለጿቸውን ችግሮች በሚመለከት ማብራሪያ እንዲሰጡን በኮሌጁ ቅጥር ግቢ ተገኝተን የኮሌጁን የበላይ ጠባቂ አቡነ ጢሞቲዎስን ለማነጋገር ብንሞክርም ከተማሪዎቹ፣ ከቤተ ክህነትና ከመንግሥት አካላት ጋር ስብሰባ ላይ ስለሆኑ ሊያነጋግሩ አይችሉም በመባሉ አልተሳካልንም፡፡

1 comment:

  1. ስትፆም ሰው አይወቅብህ"

    21ተሰ 4፡1-12 1ጴጥ 1 ፡13-25 ማቴ 6፡1-23

    ፆም የሰው ልጅ ራሱን ከስጋ ምኞት ፣ከኃጥያት ተከላክሎ ከአምላኩ ጋር የሚቀራረብበትና የሚታረቅብት በቤተክርስቲያናችን ትልቁ አምልኮና ተጋድሎ ነው፡፡ጾም የሰው ልጅ የስጋ ምኞትንና ኃጥያትን ተከላክሎ ከአምላኩ ጋር እንዲታረቅ በቤተክርስቲያናችን በተለይም ምስራቃዊያን በዓመት ውስጥ አጿማት ለምእመኗ አውጃ ምእመናኑ መጾምና በተጋድሎ ከአምላካቸው ጋር እንዲታረቁ ትጋብዛለች፡፡ አሁን ያለንበት ግዜ የአብይ ፆም የመጀመሪያ ሳምንት ሲሆን ምዕመናን ለዚህ ፆምና ተጋድሎ ራሳቸውን አዘጋጅተው ከጀመሩት አንድ ሳምንት ሆኗቸዋል፡፡ታዲያ ስንፆም ምን ማድረግ አለብን?የዛሬው ወንጌላችን ይህንን የሚያሳየን ሲሆን ጌታችን መድኃኒታችን "ስትፆም በፍፁም ሰው አይወቅብህ"ይለናል፡፡ምንም እንኳን አብይ ፆም ትልቁ ፆምና ሁሉም ምዕመናን የሚፆመው በመሆኑ፤ሁሉም ጿሚ እርስ በራሱ ቢተዋወቅም፤ለሌሎች ግን ለእይታ ማድረግ እንደሌለብን መገንዘብ ይገባናል፡፡የምንፆመውም ከስጋ፣ከወተትና ከወተት ውጤቶችብቻም ሳይሆን የስጋ ምኞቶቻችንን ከሚያበዙብን ከአልኮልና ከመሳሰሉት ነገሮች ሁሉ መታቀብ ይገባናል፡፡

    ፆም ከላይ ከተጠቀሱት የምግብ አይነቶች መታቀብና መጸለይ እንዲሁም ነዳያንን መደገፍ ነው፡፡ፆም ከምግብ አይነቶችና የስጋ ምኞቶችን ከሚያበዙብን ታቅበን ካልጸለይን ፈተናዎቻችን ይበዛሉ፤በፈተናም እንዳንወድቅ በርትተን መጸለይ ይገባናል፡፡እነዲሁም በመጸለይ ከአምላካችን ጋር እንገናኛለን በተጨማሪም ለነዳያን ያለንን ስናካፍል አምላካችንን እናስደስታለን፤ለእኛም የመንፈስ እርካታ ከማግኘታችን በላይ አምላካችን ለኛ ያለውን የፍቅር ሕይወት እንቋደሳለን፡፡ታዲያ ይህንን ዕድል ለመጠቀም ፆመን ጸልየን ነዳያንን በመደገፍ ከአምላካችን የደስታ ሕይወት መካፈል ነውእንጂ ለእይታ ማድረግ አይገባንም፡፡

    ምንባቡ ስለምን ይናገራል? ስንፆም እንዴት ነው የምንፆመው? እውነተኛውን ፆም ለመፆን ምን ማድረግ አለብን?
    እዉነት ይቻላችዋል መጀመርያ ከሆደ አምላክ ወደ ክርስቶስ ተመለሱ

    ReplyDelete