Tuesday, April 10, 2012

‹‹ማኔ ቴቄል ፋሬስ›› ብሎ የሚፅፈው ጣት ቀርቧል

(አንድ አድርገን ሚያዚያ 2 2004 ዓ.ም)፡
የመቅደሱንም ዕቃዎች በፊትህ አመጡ፥ አንተም መኳንንትህም ሚስቶችህም ቁባቶችህም የወይን ጠጅ ጠጣችሁባቸው ከብርና ከወርቅም ከናስና ከብረትም ከእንጨትና ከድንጋይም የተሠሩትን የማያዩትንም የማይሰሙትንም የማያውቁትንም አማልክት አመሰገንህ ትንፋሽህንና መንገድህን ሁሉ በእጁ የያዘውን አምላክ አላከበርኸውም።  ስለዚህም እነዚህ የእጅ ጣቶች ከእርሱ ዘንድ ተልከዋል ይህም ጽሕፈት ተጽፎአል። የተጻፈውም ጽሕፈት። ማኔ ቴቄል ፋሬስ ይላል። የነገሩም ፍቺ ይህ ነው ማኔ ማለት፥ እግዚአብሔር መንግሥትህን ቈጠረው ፈጸመውም ማለት ነው። ቴቄል ማለት፥ በሚዛን ተመዘንህ፥ ቀልለህም ተገኘህ ማለት ነው። ፋሬስ ማለት፥ መንግሥትህ ተከፈለ፥ ለሜዶንና ለፋርስ ሰዎችም ተሰጠ ማለት ነው። የዚያን ጊዜም ብልጣሶር ለዳንኤል ሐምራዊ ግምጃ እንዲያለብሱት፥ የወርቅ ማርዳም በአንገቱ ዙሪያ እንዲያደርጉለት አዘዘ በመንግሥትም ላይ ሦስተኛ ገዥ እንዲሆን አዋጅ አስነገረ። በዚያ ሌሊት የከለዳውያን ንጉሥ ብልጣሶር ተገደለ። ሜዶናዊውም ዳርዮስ መንግሥቱን ወሰደ ዕድሜውም ስድሳ ሁለት ዓመት ነበረ። ትንቢተ ዳንኤል 5 23-31


ይህን ታሪክ አታውቁትም ብዬ አይደለም ለመጻፍ የወደድኩት የናቡከደነጾር ልጅ ብልጣሶር ለእግዚአብሔር መስዋት የሚቀርብበት የመቅደሱን እቃ አውጥቶ እንዴት እንዳቃለለ እግዚአብሔርም ተቆጥቶት ምን እንዳደረገው ለማስመልከት  ያህል ነው ፤  የናቡከደነጾር ልጅ ብልጣሶር  ይህን ተግባር ከማድረጉ በፊት እግዚአብሄር ሁሉን ነገር ማድረግ ይችላል ፤ አሁንም በዋልድባ እየሆነ ያለው ነገር ማኔ ቴቄል ፋሬስ የሚጻፍበት ጊዜ የደረሰ ይመስላል ፤ በኦሪት ዘመን ስራውን ሲሰራ የነበረው እግዚአብሔር አሁንም ከእኛ ከሀጥያተኞቹ ጋር አለ ፤ ከነብያትና ከሀዋርያት ጋር የነበረው አምላክ አሁንም በመካከላችንን አለ ፤ ማቴዎስ 28 ፤ 20 ላይ ‹‹ እኔ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ። ብሎ ቃል ገብቶልናል ፡፡ የዛሬ 20 ዓመት በፊት ገዳሙን የጦር ካምፕ ለማድረግ ስትነሱ ለናንተ ባልተገለጸ መንገድ 80 ሰዎች በአንድ ቀን ሞተው መገኝታቸውን  ሰማን ፤ ይህ የሆነው በእኛ ዘመን በእኛ እድሜ ነው ፤ ‹‹እግዚአብሔር አምላክም ሰውን ከምድር አፈር አበጀው በአፍንጫውም የሕይወት እስትንፋስን እፍ አለበት ሰውም ሕያው ነፍስ ያለው ሆነ።›› ኦሪት ዘፍጥረት 27  ተብሎ ተፅፏል ፤ የእኛም ይሁን የእናንተ ነፍስ ይህች ናት እኛ ግን አላስተዋልንም ፤ በሰው አፍንጫ የህይወት እስትንፋስ የሰጠን አምላክ ለመውሰድም ይህን ያህል ለእርሱ ቀላል ነው፡፡ ሟች መሆናችሁን አውቃችሁ የገዳሙን ህልውና የሚያሳጣ ስራ አትስሩ ፤ የሚበቅለው ሸንኮራ ጣፋጭ ስለመሆኑ እርግጠኛ አትሁኑ ፤ ባለቤቱ ለቤቱ ቀናተኛ መሆኑንም አትርሱ ፤ አሁን እየተገዳደራችሁ ያላችሁት ከእግዚአብሔር ጋር ነው ፤ እሱ ደግሞ አይተኛም ተብሎ ተጽፏል ፤ ምንም መንፈሳዊነት የማይገባችሁ ሰዎች ብትሆኑም የእግዚአብሔር መኖር ትጠራጠራላችሁ የሚል ግምት የለንም ፤ ናቡከደነጾር ሲበድል አምላክ ዝም ያለበት ምክንያት ‹‹እግዚአብሔር መሐሪ፥ ሞገስ ያለው፥ ታጋሽም፥ ባለ ብዙ ቸርነትና እውነት፥ እስከ ሺህ ትውልድም ቸርነትን የሚጠብቅ፥ አበሳንና መተላለፍን ኃጢአትንም ይቅር የሚል፥ በደለኛውንም ከቶ የማያነጻ፥ የአባቶችንም ኃጢአት በልጆች እስከ ሦስትና እስከ አራት ትውልድም በልጅ ልጆች የሚያመጣ አምላክ›› ስለሆነ ነው  ኦሪት ዘጸአት 346 የምትሰሩት ስራ ከእርሱ የተደበቀ ሆኖ አይደለም ፤ ትንቢተ ኤርምያስ 17፤10 ላይ ‹‹እግዚአብሔር ለሰው ሁሉ እንደ መንገዱ፥ እንደ ሥራው ፍሬ እሰጥ ዘንድ ልብን እመረምራለሁ ኵላሊትንም እፈትናለሁ።›› ተብሎ ተጽፏል አንዳች ከእርሱ የሚደበቅ ስራ የላችሁም ፤ በተጨማሪ የዮሐንስ ራእይ 2፤23 ላይ ‹‹ኵላሊትንና ልብን የምመረምር እኔ እንደ ሆንሁ ያውቃሉ፥ ለእያንዳንዳችሁም እንደ ሥራችሁ እሰጣችኋለሁ።›› ይላል ፡፡ ስለዚህ ከእርሱ የተደበቀ ከእርሱ የተሰወረ አንዳች ነገር የለም ዛሬ ላይ ልባችሁ አብጦ ጉልበትን መከታ በማድረግ የሚሰራ ስራ  ነገ ከተጠያቂነት ነጻ አያደርግም ፤ ከታሪክ ተወቃሽነትም ወደ የትም አያሸሽም ፤ በሰራችሁት ስራ ይመዝናችኋል ዋጋችሁንም ይሰጣችኋል  ‹‹እግዚአብሔር ፈራጅ ነውና።›› መዝሙረ ዳዊት 506 ፡፡ የራሄል እንባ 420 ዓመታት በግብጽ ሲማቅቁ የነበሩትን እስራኤላውያን ለመውጣታቸው መንስኤ ሆኗል ፡፡ ‹‹የዋይታና የመራራ ልቅሶ ድምፅ በራማ ተሰማ ራሔል ስለ ልጆችዋ አለቀሰች የሉምና ስለ ልጆችዋ መጽናናትን እንቢ አለች። ትንቢተ ኤርምያስ 31 ፤15 ፤ አሁንም አባቶች ስለምታደርጉት ነገር እያለቀሱባችሁ መሆኑን እወቁ ፤ እንባቸው ጎርፍ ሆኖም እንዳይጠራርጋችሁ ለራሳችሁ ስጉ ፤ አምላካችን የራሄልን እንባ ከአይኗ የዳበሰ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር ነው ፡፡‹‹ የሠራዊት ጌታ ከእኛ ጋር ነው የያዕቆብ አምላክ መጠጊያችን ነው። ›› መዝሙረ ዳዊት 46 ፤7 ተብሎ ተጽፏል፡፡ በተጨማሪ በትንቢተ ኢሳያስ 1፤24 ላይ ‹‹የሠራዊት ጌታ የእግዚአብሔር ቀን በትዕቢተኛውና በኵራተኛው ሁሉ ላይ ከፍ ባለውም ላይ ይሆናል፥ እርሱም ይዋረዳል›› ይላል ሀይል የእግዚአብሔር መሆኑን እናምናለን ፤ ነገር ግን ስጋውያን ትላንት ታይተው ከደቂቃዎች በኋላ እንደ ጤዛ ለሚደርቁ ጉልበተኞች በዘመናችን ቢያጋጥሙን ለሰው ልጅ ጉልበት የሚሆን ጉልበትንም የሚሰብር እርሱ አምላካችን  እግዚአብሔር መሆኑን ይወቁት፡፡ የክርስትያኖች  ጉልበታችን ጾማችን ፤ጸሎታችን ፤ምህላችን ፤ ስግደታችንና ወደ አምላክ የምናፈሰው እንባችን ብቻ ነው፡፡

 እንደ እኔ ሀሳብ  የናቡከደነጾር ልጅ ብልጣሶር  የደረሰበት ነገር አሁንም የማይደርስበት ምንም ምክንያት ያለ አይመስለኝም ፤ የያኔው እግዚአብሔር አሁንም ከእኛ ጋር ነው ያለው ፤ የዛኔ የጻፉ የእጅ ጣቶች አሁንም ለመስራት ባሰባችሁት 138 ሜትር ግድብ ላይ የማይጽፉበት አንዳች ነገር የለም ፤ አሁንም ተመዝናችሁ ቀላችሁ እንዳትገኙ ለራሳችሁ አስተውሉ ፤ መንግስታችሁንም እንዳይቆርጠው እንደዚያው ፤ ‹እውነተኛ ሚዛንና መመዘኛ የእግዚአብሔር ናቸው›› መጽሐፈ ምሳሌ 16፤11 በእርሱ ሚዛን ተመዝናችሁ እንደ  ብልጣሶር  እንዳትቀሉ ለራሳችሁ ብላችሁ ተጠንቀቁ ‹‹እርሱ ታላቅ አምላክ ኃያልም የሚያስፈራም፥ በፍርድ የማያደላ፥ መማለጃም የማይቀበል ነውና››   ኦሪት ዘዳግም 10 ፤ 16 ነውና፡፡እኛ ግን እንደ ክርስትያን ለመሪዎቻችን ማስተዋሉን እና ጥበቡን ስጣቸው እያልን ዘወትር እንጸልያለን ፤ ማንም የሚመጣው ማንም የሚሄደው በእርሱ ፍቃድ ነው ብለንም እናምናለን ፤
በኦሪት ዘመን እግዚአብሔር እንደ ልቤ ያለው ንጉስ ዳዊት ፤ ካንተ በኋላ ሌላ ጠቢብ አይነሳም የተባለው ጠቢቡ ሰለሞን ፤ እና አያሌ ነገስታት ህዝብን ለማስተዳደር እግዚአብሔር ሾሟቸዋል ፤ ጊዜውም ሲደርስ የሾማቸውን ሽሯቸዋል ፤ አሁንም ይህ የመንግስት ወንበር ከዘመናት በፊት ያለፉት ነገስታት ተቀምጠውበታል ፤ ህዝብንም በህግና ከህግ ውጪ አስተዳድረውበታል ፤ እግዚአብሔር በዘመናቸው ሾሞ ፤ ቀብቶ አስቀምቷቸዋል ፤ ዘመናቸው ሲያበቃ አውርዷቸዋል ፤ በእነዚህ ሁሉ ጊዜያት ይህች አሁን ያለችው ቤተክርስትያን እንዳለች አለች ፤ ዛሬ የምናያቸው ባለስልጣናት ዛሬ መጥተዋል ነገ ደግሞ ወደ ማይቀርበት ሞት ይነጉዳሉ  ይህች ንፅህት አንዲት ቤተክርስትያ ግን ጌታችን መድሀኒታን እየሱስ ክርስቶስ በዳግም እስኪመጣ ድረስ ከነፈተናዋ ሳትጠፋ ትጠብቀዋለች ፤ ትቆያለች፡፡   ስለያዛችሁት ስልጣን ደግሞ እንዲህ ተብሏል ‹‹ከእግዚአብሔር ካልተገኘ በቀር ሥልጣን የለምና፤ ያሉትም ባለ ሥልጣኖች በእግዚአብሔር የተሾሙ ናቸው።›› ወደ ሮሜ ሰዎች 9፤21 ታዲያ ሰጪ እግዚአብሔር የሚነሳም እሱ ሆኖ ሳለ ለምን በቤቱ ላይ አመጻን ታካሂዳላችሁ ? ለእናንተ መመሪያችሁ ሰው የጻፈው ህግ ነው ፤ ለእኛ ለክርስያኖች መመሪያችን ደግሞ የአምላካችን ቃል ነው ፤ የእሱ ቃል ደግሞ ‹‹የእግዚአብሔር ቃል ሕያው ነውና፥›› ወደ ዕብራውያን 4፤12 ተናገረውን የማያስቀር አምላክ ነው ፤ የተናገረውንም የሚፈጽም ፤  ቃሉን ደግሞ እንዲህ ብሎ ገልጾ አስቀምጦታል  ‹‹ሰማይና ምድር ያልፋሉ፥ ቃሌ ግን አያልፍም።›› የማቴዎስ ወንጌል 518 ቤተክርስትያናችን የምታምነው በዚህ ‹‹ቃል›› ነው፡፡
‹‹በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ትጠብቁአት ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እናንተን ጳጳሳት አድርጎ ለሾመባት ለመንጋው ሁሉና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ።›› የሀዋርያት ስራ 20 ፤28 ይህን መልእክት በመጽሀፍ ቅዱስ ሰፍሮ እናገኝዋለን ፤ አሁንም ብጹአን አባቶቻችን ለመንጋውና ለቤተክርስተያን ግድ ሊላቸው ይገባል ፡፡ ለምን ይህ ፈተና መጣ አንልም ‹‹ከሚቻላችሁ መጠን ይልቅ ትፈተኑ ዘንድ የማይፈቅድ እግዚአብሔር የታመነ ነው፥ ትታገሡም ዘንድ እንድትችሉ ከፈተናው ጋር መውጫውን ደግሞ ያደርግላችኋል።›› 1ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 10 ፤13 ላይ ሰፍሯል ፤ ነገር ግን ፈተና ሲመጣ ብቻውን እንደመጣ ብቻውን አያልፍም ፤ ፈተናው አብሮ ይዞ የሚያልፋቸው ነገሮች ይኖራሉ ፤ እኛም ስለ ፈተናችን ልንታገስ በጾም በጸሎት ልንበረታ ያስፈልጋል  ፤ ይህ ፈተና የሚያልፈው አባቶች የአባትነታቸው ተግባር ሲፈጽሙ ምዕመናኑም ሀላፊነታቸውን አውቀው ስራቸውን በአግባቡ ሲፈጽሙ ብቻ ነው ፡፡ ይህ ፈተና ሰዎችን ከስልጣናቸው ሊያፈናቅል ይችላል ፤ እስር ቤት ሊያስገባቸውም ይችላል ፤ አካላዊ ጉዳትም ሊያደርስባቸው ይችላል ፤ አባቶችን ከበአታቸው በረው እንዲጠፉ መንገድ ሊከፍት ይችላል ፤ በስተመጨረሻ የህይወት መስዋእትነትንም ሊጠይቅ ይችላል ፤ ይህን አውቀን ነው ፈተናን በእግዚአብሔር ኃይል ለመጋፈጥ መዘጋጀት ያለብን ፤ ስለዚህ ይህ ፈተና የመጣው ለዋልድባ መነኮሳት ብቻ አይደለም ፤ ይህ ፈተና የሁላችንም ነው ፤ ቅዱስ ፓትርያርኩ በጉዳዩ ላይ እስካሁን ያሉት ነገር ባይኖርም ሰልፋቸው ከወዴት እንደሆነ ለመገመት ግን ነጋሪ የሚያሻ አይመስለንም ፤  ነገሩን መቃወምም አለመቃወምም ሁለቱም አቋም ነው ፤ ነገር ግን ሁኔታው እያዩ ዝም ማለት ግን እንደ አባት መልካም አይደለም ፤ ብጹአን አባቶቻችን  ዝም ማለታቸው ለምን ይሆን? የሚል ነገር ውስጣችን ፈጥሯል ፤ እነርሱ በዚህ ጉዳይ ላይ አንድ እርምጃ ተራምደው ቢያሳዩን መልካም ነው ፤ ታላቁ አባት ብጹእ አቡነ ሺኖዳ ሳልሳዊ ፓትርያርክ ከሆኑ ከጥቂት ዓመታት በኋላ ‹‹የግብጽ መንግስት በተናጠል ከእስራኤል ጋር ያደረገውን ስምምነት እኛ ክርስትያኖችን ያማከለ አይደለም ፤ እኛ ክርስትያኖች እንደ ሀገር ስትወስኑ አልሰማንም አልተጠራንም ፤ በቦታው ላይም አልነበርንም ፤ ከ8ሚሊየን በላይ ቁጥር እያለን እኛን አግልላችሁ በራሳችሁ የተስማማችሁበት ነገር እንደ እምነት አባት እውቅና አንሰጥም ፤ ግብጽ የክርስትያኑም የሙስሊሙም ነች ፤ ሀገሪቷ የሁላችን ናት ›› በማለታቸው ቀጥታ በግዞት ለ3 ዓመት ያህል ወደ ገዳም ነበር ያወረዷቸው ፡፡ እሳቸው በሀገር ጉዳይ ልታማክሩን ይገባችሁ ነበር ብለው ነው የተቃወሙት ፤ እኛ ግን ገዳማችንን የስኳር ልማት ለማድረግ ሲነሱ እኛን አላማከራችሁም የሚል አባት አልተሰጠንም ፤ ሁኔታው ገና ሲጠነሰስ የጉዳዩ ባለቤት መሆን የሚገባን እኛ ነበርን ፤ ሀገር እኮ የሁሉም ናት ፤ አይደለም ይህን ፕሮጀክት እንደ ሀገር የሚሰራ ስራን ማወቅ እና ለመንግስት ጥያቄ መጠየቅ መብታችን ነው ፡፡ በአሁኑ ሰዓት ለቤተክርስትያን እንደ አቡነ ጴጥሮስ ከጠላት ፊት ለፊት የሚቆምም አባት ያስፈልጋታል ፤ ይህን ተግባር መጀመሪያ ማውገዝ ያለባቸው ዝም ብለዋል ፤ ምንም እንዳልተፈጠረ በኢቲቪ ድራማ ሲሰራ እያዩ እንዳላዩ ተመልክተዋል ፤ ይህ ግን ከምንም አያድንም ፤ ትውልድም ይወቅሰናል ፡፡  በ16ተኛው ክፍለ ዘመን እምነታችንን አንቀይርም ብለው በጎንደር 8ሺህ ምዕመናን ስለ አንዲት እምነታቸው መስዋእትነትን ተቀብለዋል ፤ አሁንም በጎንደር ይህን ስራችሁን የሚቃወሙ ፊት ለፊትም የሚጋፈጧሁ በርካታ የቤተክርሰትያን ልጆች አሉ ፤ ባለፉት 15 ዓመታት በጎንደር ያሰባችሁትን ነገር ምዕመኑ እንዴት እንደተቃወመ ማስታወስ ያለብን አይመስለንም ዛሬ ያገኝናት ቤተክርስያን ብዙ መስዋእትነት የተከፈለባት መሆኑን አንርሳ ፤
‹እግዚአብሔር ስለ እናንተ ይዋጋል፥ እናንተም ዝም ትላላችሁ›› ኦሪት ዘጸአት 1414 ፤ ይህን ተግባር መቃወም እና ከእኩይ አላማቸው መግታት ቢያቅተን መጽሀፍ ቅዱስ ‹‹ተሰለፉ፥ ዝም ብላችሁ ቁሙ፥ የሚሆነውንም የእግዚአብሔርን መድኃኒት እዩ እግዚአብሔርም ከእናንተ ጋር ነውና አትፍሩ፥ አትደንግጡም፥›› መጽሐፈ ዜና መዋዕል ካልዕ 20 ፤17 ይላል ፤ እስኪ ጊዜው ሰሞነ ህማማት ነው ፤ ስንሰግድ ስንጸልይ ስንወድቅ ስንነሳ የዋልድባ ነገር አደራ እያልን ፤ በአሁኑ ሰዓት የገዳሙ አባቶች እያሳለፉት ያለውን ፈተና አምላክ እንዲያቀለው እያሳሰብን እንበርታ ፡፡



አሁን በቦታው ላይ የሚደረገውን ነገር ተመልክታችሁ ስለ ምትሰሩት ስራ ትምህርት ካልሆናች  ‹‹ማኔ ቴቄል ፋሬስ›› ብሎ የሚፅፈው ጣት ይቀርብባችኋል

9 comments:

  1. <> ቃለ ህይወት ያሰማልን እንደ ዲወቅሊጢያኖስ እግዚአብሔር የሚሰራው ተአምር የማይሰማቸው ልባቸው የደነደነ መማር ያቃታቸው እቤታቸው አንኳኩቶ እስኪገባ ድረስ የሚጠብቁ ናቸውና እግዚአብሔር የጃቸውን ይስጣቸው አሜን::

    ReplyDelete
  2. ለገባው ይሄ ትልቅ መልዕክት ነው፤ ዳንኤል ለመተርጎም መጠራት የለበትም ፡፡ እምቢኝ አሻፈረኝ ካሉና ጊዜው ከደረሰ ግን ምንም ማድረግ አይቻልም የንጉስ ብልጣሶርን ዕጣ መጠበቅ ነው፡፡ ምን አለ በሉኝ ደግሞ አይቀርላቸውም!!!!!

    ReplyDelete
  3. melekame eyetanewe egiziabehere zemenachehune yebarekilachehu

    ReplyDelete
  4. የይሁዳ ግብር ልጆች ክርስቶስን አሳልፎ እንደሰጠው ይሁዳ አሳልፎ እንደሰጠው ቤ/ክንን አሳልፋችሁ ሰጣችሁ፡፤ ክርስቶስን ለይዙት የመጡት ሊይዙት ሲሉ ፍግም ብለው ወድቀው ነበር፡፡ በፈቃዱ ተያዘ እንጂ፤ አሁንም ዋልድባን የደፈሩ ፍግም ማለት ተጀመረ ተጠንቀቁ ፤ ሰሞኑን ሆሳዕና ላይ የተፈጠረውን እንዳትረሱ በዋልድባ ላይ የተፈራረማችሁ ሁሉ ቤታችሁን አስተካክሉ በተለይ ተሐድሶ መናፍቃን ኢአማንያን ስልጣን በእጃችን ብላችሁ በሃይል ያስወሰናችሁት ሁሉ አስቡበት የተፈራረማችሁ ሁሉ

    ReplyDelete
  5. FOR SURE THE LIFE OF THE PROJECT IS TOO SHORT!!!!

    But I wonder for future GOVERNMENT - BETEKHNET unity against EOTC. Do they believe SECULARISM IS ABOLISHING OUR TRUE MOTHER. Wow,,,,,,
    This is threat to our spiritual sovereignty and national order as well.

    Sew Yemiqawomewun ena yemidegefewun meleyet kalchale . . . . . .

    ReplyDelete
  6. ‹‹በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ትጠብቁአት ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እናንተን ጳጳሳት አድርጎ ለሾመባት ለመንጋው ሁሉና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ።››
    የሐ ስራ 20፡28
    እውነት አሁን ሀገራችን ትክክለኛ አባት አላት? አይመስለኝም ብቻ እግዚአብሔር አምላክ የራሔልን እንባ እንደሰማ የእኛንም እንባ ይስማ፡፡

    ReplyDelete
  7. አሁን በቦታው ላይ የሚደረገውን ነገር ተመልክታችሁ ስለ ምትሰሩት ስራ ትምህርት ካልሆናች ‹‹ማኔ ቴቄል ፋሬስ›› ብሎ የሚፅፈው ጣት ይቀርብባችኋል::

    ReplyDelete
  8. pleas, stand up!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!

    ReplyDelete
  9. ‹ከሚቻላችሁ መጠን ይልቅ ትፈተኑ ዘንድ የማይፈቅድ እግዚአብሔር የታመነ ነው፥ ትታገሡም ዘንድ እንድትችሉ ከፈተናው ጋር መውጫውን ደግሞ ያደርግላችኋል።›› 1ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 10 ፤13

    ReplyDelete