Wednesday, May 23, 2018

የወይንዬ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን ተመረቀ



(አንድ አድርገን ግንቦት 15 2010 ዓ.ም)፡- በኢትዮጵያ በረሃዎችና አውራጃዎች እየተዘዋወሩ በልዩ ልዩ አምልኮ የነበረውን ሕዝብ የክርስቶስ ወንጌለ መንግሥትን አስተምረውና አጥምቀው የክርስቶስን መንግሥት እንዲወርሱ ያደረጉት  ቅዱስ አባታችን አቡነ ተክለ ሃይማኖት እግዚአብሔር በመራቸው መሠረት የሐዋርያ አሠረ ፍኖት በመከተል ዘር ልዝራ ፣ ትዳር ልያዝ ሳይሉ ታላላቅ ተዓምራትን ካከናወኑባቸው ቦታዎች  ውስጥ በሰሜን ሸዋ ሀገረ ስብከት ከደብረ ብርሃን አካባቢ የሚገኝው ወይንዬ ተክለ ሃይማኖት ስፍራ አንዱ ነው፡፡ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ወይን ተክለው ለ12 ዓመታት በቦታው በመቀመጥ ሲጸልዩበት የነበሩበትና በርካታ ተዓምራትን ያከናወኑበት  ፤ ጸበል አፍልቀው አህዛብን ሲያጠምቁበት የነበረውን ቦታ ያዩበታል፡፡ (በገድለ ተክለሃይማኖት ላይ ምድረ ደርደሬ ይለዋል)፡፡

ይህ ቦታ የሚገኝው ከደብረ ብርሃን ከተማ  በስተሰሜን ምዕራብ አቅጣጫ በግምት 5 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ቀጥ ባለ ገደል ተከቦ ሲሆን እዚህ ቦታ ላይ ጻድቁ አቡነ ህጻኑ ሞአ የተወለዱበትና እንደ በሬ ተጠምደው በማረስ ገድላቸውን የፈጸሙበት ታላቅ ስፍራ ይገኛል፡፡ በዚሁ ስፍራ ላይ ‹‹እስትንፋስ›› የሚባል ቦታ ከመሬት ሳያቋርጥ በሚወጣው እስትንፋስ አማካኝነት በርካቶች ከተለያዩ በሽታዎች የዳኑበትና እየዳኑ የሚገኙበት ልዩ ስፍራ ይገኛል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በቦታው ቀድሞ  ከኢትዮጵያ ውስጥ ከሚገኙ ትላልቅ ገዳማት የመጡ አባቶች የሚያገለግሉበትና የሚገለገሉበት ታላቅ ቦታ  ፡፡


እዚህ ቦታ ላይ ከተጀመረ አስራ አራት ዓመት ያለፈው የጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ቤተክርስቲያን ግንቦት 12 2010 ዓ.ም ተመርቋል ፤ እጅግ ብዙ ፈተናዎችን ያለፈውና በመጨረሻ እንደ እግዚአብሔር መልካም ፍቃድና እንደ ወንድሞች ብርታት ሕንጻ ቤተክርስቲያኑ የአባታችን ዓመታዊ በአል ቀን በእለተ ሰንበት በብዙ ካህናት ፤ ዲያቆናት ፤ ሕዝበ ምዕመን እና ከአገረ ስብከቱ የተወከሉ ቆሞሳት ባሉበት ግንቦት 11 አመሻሹ ላይ ከቀድሞ ቤተክርስቲያኑ የአባታችን የአቡነ ተክለሃይማት እና የእናታችን የኪዳነ ምህረት  ታቦታትን በማውጣት ፣ አዲሱን ቤተ ክርስቲያን በመባረክ አባቶች ያስገቡ ሲሆን ሙሉ ሌሊት ምስጋና በማቅረብ በቀጣይ ቀን እጅግ ብዙ ምዕመን በተገኝበት ቅዳሴ ቤቱ ከብሮ አገልግሎት መስጠት ችሏል፡፡



ቤተ ክርስቲያኑ ለምርቃት እንዲበቃ ያላሰለሰ ጥረት ያደረጉ ሰዎች ከሀገር ውስጥ ሆነ ከውጭ ክርስቲያናዊ ግዴታቸውን የተወጡ ምዕመናን ላደረጉት ጉልህ አስተዋጽኦ ከቤተክርስቲያኗ የምስጋና ምስክር ወረቀት ተቀብለዋል፡፡

የአካባቢው ምዕመን በአሉን ለማክበር የሚመጣውን ምዕመን ከንግስ በኋላ ለማስተናገድ ከ10 በላይ በሬ በማረድ በተለያዩ አዳራሾች ለ5 ሰዓታት ያህል ምዕመኑን እና በዓሉን ሊያከብር የመጣውን ሕዝበ ክርስቲያን ሲያስተናግን አምሽቷል፡፡   

በአሁኑ ሰዓት የተሰራውን ቤተክርስቲያን የሚመጥን ቤተልሔም ፤ የግቢ ሥራ ፤ የውስጥ ስዕላት ፤ ንበር መጋረዣ እና ለአገልግሎት የሚያስፈልጉ አንዳንድ ነገሮች የሚጎሉት ሲሆን ከዚህ በተጨማሪም ከ3 ዓመታት በፊት በበጎ አድራጊ ወንድሞች የተጀመረው የአብነት ትምህርት ቤት በአሁኑ ሰዓት ከ30 በላይ ተማሪዎች በአንድ መምህር ትምህርት እያገኙ ቢሆንም ወደፊት ይህን አገልግሎት በሰፊው ከአራት በላይ መምህራን እና ከ100 በላይ ተማሪዎችን ለማስተማር ስለታቀደ እርስዎም በዚህ የቤተክርስቲያንን አገልግሎት የማስቀጠል እና በረከት የማግኝት ጉዞ ላይ የራስዎትን ግዴታ በመወጣት ከጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት በረከትን ያገኙ  ዘንድ ተጋብዘዋል፡፡

ለበለጠ መረጃ  ፡- 0911-616317 (የሕንጻ አሰሪ ኮሚቴ ሰብሳቢ)ይደውሉ



No comments:

Post a Comment