Sunday, March 11, 2018

ድንጋይ በድንጋይ ላይ



በዲ/ን ብርሃኑ አድማስ አንለይ


ሐዋርያት ከጌታችን ጋር በደቀ መዝሙርነት በነበሩበት ዘመን ምንም ያህል ኃይልና ተአምራት የማድረግ ነገር ቢሰጣቸውም ከሌላው ሕዝብ ጋር ሲኖሩ ቀድመው የወሰዱት ጠባይ ገና አልለቀቃቸውም ነበር፡፡ ለዚህ ምሳሌ ሊሆኑን ከሚችሉት ብዙ ማስረጃዎች አንዱ ዛሬ ደብረ ዘይት እያልን በምናከብረው በዓል ላይ በሚነበብልን ወንጌል የተገለጸው ምስክር ሊሆን ይችላል፡፡ ምንም እንኳ አምላክነቱን አምነውና አውቀው ቢከተሉትም ብዙ ጊዜ ግን እነርሱን የሚያስደንቃቸው ነገር እርሱንም የሚያስደንቀው፣ ለእነርሱ የተለየ የሚመስላቸው ነገርም ለእርሱም የተለየ የሚሆን ይመስላቸው ነበር፡፡ ለዚህም ነበር ቤተ መቅደሱን እያደነቁ እርሱም የሚደነቅ መስሏቸው የነገሩት፡፡

ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ቤተ መቅደስ ከተናገራቸው መካከል ድንጋይ በድንጋይ ላይ ሳይፈርስ አይቀርም የሚለውና በበዓለ ደብረ ዘይት የሚነገረው ይህ አስደናቂ ትምህርት አንዱና ዋነኛው ነው፡፡ ይህም ማለት ለቤተ መቅደስ መሥሪያነት በመደራረብ ከታነጹትና ድንጋይ ከመባል ቤተ መቅደስ ወደ መባል ከደረሱት ውሰጥ እንደገና ተመልሰው አንዱም ሳይቀር ይነሡና ቤቱም ቤተ መቅደስ ከመባል ወጥቶ ቦታው ሜዳ ምድረ በዳ፣ ድንጋዮቹም ተመልሰው ድንጋይ ከመባል አይተርፉም ማለት ነው፡፡በርግጥ ቤተ መቅደሱ ቤተ መቅደስ መሆኑ የሚቀረው እግዚአብሔር የተለየው ጊዜ ነው፡፡ እርሱም በትምህርቱ ወቅት ራሱን ቤተ መቅደስ ብሎ ከመጥራቱ በቀር ይህን እነርሱ የሚመኩበትን ቤተ መቅደስ ቤተ መቅደስ ብሎ አልጠራውም፤ ምክንያቱም አይሁድ ቤተ መቅደስ ከመባል በግብር እያስወጡት ነበርና፡፡


ይህ ታሪክ ራሱ በወንጌል የተመዘገበው ደግሞ እኛ ራሳችን ይህንኑ ስሕተት ደጋግመን እንዳንፈጽመው ለማስተማር ነው፡፡ ምክንያቱም አንድን ነገር ከሚያስደንቅበት፤ ከሚያስወድድበት፣ ከሚያሳስብበት አውጥተን በሌላ መንገድ ልናደንቀውና ልንወድደው ወይም ልናከብረው ስንፈልግ እግዚአብሔር ደስ አይሰኝም፡፡ ለምሳሌ ቤተ መቅደሱ ሊደነቅ የሚገባው እግዚአብሔር በዚያ በማደሩ ኃይልና ተአምራት በማድረጉ ሆኖ ሳለ እነርሱ ግን ያንን ትተው በቁሳዊ ውበቱ ተደነቁ፡፡ ሌላው ቀርቶ እግዚአብሔር በፈጠረው ፍጥረት ሕብርና ውበት ሳይደነቁ በዚያ ሰዎች በሠሩት፣ በሚመኩበትና ከተለበጠበት ወርቅና ጌጥ የተነሣ መደነቃቸው ሳያነስ ሁሉንም ለፈጠረው ፈጣሪ እርሱም በዚያ የሚደነቅ መስሏቸው ማመላከታቸው አስደናቂ ነው፡፡ ጌታችንም ይህ መቅደስ ይፈርሳል ከማለት ይልቅ ድንጋይ በድንጋይ ሳይፈርስ አይቀርም ያላቸውም አይሁድ በቤተ መቅደሳቸው አንጻራዊ ውበት ተመስጠው መቅደሱን ገንዘብ አድርጎ ሲመለከበት የነበረውን አምላክ በልቡናቸው ገፍተው ስላስወጡትና እርሱም የይስሙላ እና የትምክህት አምልኮታቸውን መቀበል ስለተወ ነበር፡፡ ምክንያቱም እርሱ አምልኮትን የማይቀበልበትና የማይድርበት ቤት ሁሉ የፈለገውን ያህል ቢሽቆጠቆጥና ቢያምር፣ ጎብኝዎችንም ቢያማልል ድንጋይ በድንጋይ ላይ ከመባል ያለፈ ስያሜን ሊያገኝ አይችልም፡፡ እንኳን የእርሱ መመስገኛ ይሆን ዘንድ የተዘጋጀው ቀርቶ ለእኛም መኖሪያት የተሠራው ሕንጻ ሁሉ ቤት ሊባል የሚችለው እኛ እግዚአብሔርን ሳንረሳ ስንቀር ብቻ ነው፡፡ ካልሆነ ኤልሣዕ ማድጋዎችን ከሜዳም ሰብስቢ /2 ነገ 4 3/ ሲል የንዝህላሎቹን ቤት እንደጠራው የእኛም ሜዳ ከመባል አይተርፍም፡፡

እኛም በዘመናችን ተመሳሳይ ድርጊትን የምንፈጽም መሆኑ የታወቀ ነው፡፡ ለምሳሌ ያህል የሰውን ኅሊና ከገቢረ ኃጢአት ሰውነቱንም ከርኩሰት ለመጠበቅ የተሰጡ ቅዱሳት መጻሕፍትን በጽሑፋቸው ከመጠቀም ይልቅ በንብረትነታቸው በቅርስነታቸው ብቻ ለመጠቀም በእነርሱም ለመኩራትና ለመጓደድ እንጣደፋለን፡፡ እንደ ሀገርና ሕዝብ በእነርሱ መጠቀም በታሪካቸውም መታወቅ ኃጢአት ባይሆንም የተሰጡበትን ዓላማና ግብር ያስወጣ፣ ባለቤታቸውን እግዚአብሔርንና የሰጠውን ትዕዛዝ የዘነጋና ከይዘታቸው ይልቅ በንብረትነታቸው መቆጨት ሐዋርያት በደብረ ዘይት እንዳደረጉት መቅደሱን ለቀዳሴ መቅደሱ ማድነቅ ይሆናል፤ የዚህ ደግሞ ፍጻሜው ጥፋት ነው፡፡

ከዚያ በላይ ዋናው ቤተ መቅደሱ ደግሞ ሰውነታችን ነበረ፡፡ ሰውነታችንንም ከእግዚአብሔር ቃልና ከንስሐ ካራቅነው በጌታ ዘንድ ለዚያ ለኢየሩሳሌሙ ቤተ መቅደስ ድንጋይ በድንጋይ ላይ እንዳለው ለእኛም ሥጋ በሥጋ ላይ ጡንቻ በጡንቻ ላይ ብቻ ይሆናል፡፡ በርግጥም ጌታችን አንዱ ያለን ሰውነታችንን መቅደስ የሚያሰኘው ሥጋውና ጡንቻው ሳይሆን መንፈሳችን ወይም ምግባራችን ነውና እግዚአብሔር በተለየን ጊዜ ለሰውነታችንም ድንጋይ በድንጋይ ላይ ሳይፈርስ አይቀርም የሚለው የሚሠራ ይሆናል፡፡ ይህም ማለት እግዚአብሔር የተለየው ሰው በእርሱ ዘንድ ሰውነቱን መቅደስ ሲያሰኙ የነበሩትን አንዱ በአንዱ ላይ ሆነው የተሠሩት ቀስ በቀስ እየተነሡ ይፈርሳሉ፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ በመልእክቱ "ስለዚህም ምክንያት ትጋትን ሁሉ እያሳያችሁ በእምነታችሁ በጎነትን ጨምሩ፥ በበጎነትም እውቀትን፥ በእውቀትም ራስን መግዛት፥ ራስንም በመግዛት መጽናትን፥ በመጽናትም እግዚአብሔርን መምሰል፥ እግዚአብሔርንም በመምሰል የወንድማማችን መዋደድ፥ በወንድማማችም መዋደድ ፍቅርን ጨምሩ። እነዚህ ነገሮች ለእናንተ ሆነው ቢበዙ፥ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ እውቀት ሥራ ፈቶችና ፍሬ ቢሶች እንዳትሆኑ ያደርጉአችኋልና፤ እነዚህ ነገሮች የሌሉት ዕውር ነውና፥ በቅርብም ያለውን ብቻ ያያል፥ የቀደመውንም ኃጢአቱን መንጻት ረስቶአል። ስለዚህ፥ ወንድሞች ሆይ፥ መጠራታችሁንና መመረጣችሁን ታጸኑ ዘንድ ከፊት ይልቅ ትጉ፤ እነዚህን ብታደርጉ ከቶ አትሰናከሉምና" /2 ጴጥ 1 5 – 10/ ሲል እንደገለጸው እነዚህ በደረጃ የሚገነቡት አንድ በአንድ እየተኘሱ ይፈርሳሉ ማለት ነው።

በርግጥም በእኛ ዘመን የሚታየው አብዛኛው ሰው ድንጋይ በድንጋይ ላይ ብቻ ወይም ሥጋ በሥጋ ላይ ወይም ጡንቻ በጡንቻ ላይ ብቻ ነው ማለት ይቻላል፡፡ እንደተጻፈውም ምግባራት ሠናያት እየተነሡ እየተነሡ አንድም ሳይቀሩ የፈረሱብንም ቁጥራችን ቀላል አይደለንም፡፡ አንድ አይቀርም እንዳለው ጌታ በየሕይወታቸውን ውስጥ ሰውነታችን መቅደስ ያሰኙት ሁሉ መነሣታቸውን ለማረጋገጥ በማኅበራዊ ሚዲያው ላይ ያለውን ስድድባችን ማየቱ ብቻ በቂ ሊሆን ይችላል፡፡ እነ ማስተዋል እን ትዕግሥት እነ ጥበብ እነ ትሕትና እነ አርምሞ ልቅም ብለው ተነሥተውብናል፡፡ በርግጥም መልካ ከሚያሰኘው ነገር አንድም የሌለን እየበዛን ነው፡፡ በሥራቸንን እግዚአብሔርን ከመቅደስ ሰውነታችን ካስወጣነው በኋላ ምርኮ በዝባዡ ሰይጣን አንድ በአንድ የመቅደሱ አካላት የነበሩትን በጎ ነገሮቻችንን ነቃቅሎ ጥሎ ሰውነታችን ሜዳ አእምሮአችንን ምድረ በዳ ለማድረጉ ነጋሪ አያሻንም፡፡ መራርነታችን ጥላቻውና ጭካኔው ሰውነታችን እንደ ቁጥቋቶና አረም አልብሶት "ሰውነት" የመጥፎ ምግባር ዳዋ ለብሶ አሮጌ ባድማ መስሏል፡፡ አሁን በአብዛኛው የእኛ ሕዝብ መካከል የሚታየው መልካሙን ሁሉ የማጣመም የመጠፋፋትና የመበላላት ጫካ የወረሰን እኮ አባቶቻችን በመንቀፍ በመስደብና የእነርሱን አምላክ ከመካከላችን ስላስወጣነው እነርሱ በአንድነትና በፍቅር የነበሩበትን የመቅደሱን ድንጋይ ሰይጣን አንድ ሳያስቀር አንድ በአንድ ስላፈራረስብን ይመስለኛል፡፡

እንግዲያውስ ኢየሩሳሌም ይገነባል ስለሚባለው ስለሦስተኛው ቤተ መቅደስ መራቀቃችንን አቁመን ስለመጀመሪያውና መጨረሻው ሰውነት ቤተ መቀደስ እንደገና መሠራት ልናስብ ይገባናል፡፡ በርግጥም እግዚአብሔር እንዲገነባለት የሚፈልገው የእኛን ሰውነት ነው፡፡ እስኪ እባካችሁ የልዩነት ጫካችን የመለያየት ዳዋችን መመንጠር እንጀምር፡፡ የስድድብ እሾሐችንን እንንቀል፤ ያን ጊዜ የሰውነት ቤተ መቅደስ ውኃ ልኩን እናገኘዋለን፡፡ የሕንጻውን መገንቢያወችን ታችኛውንን መደማመጠን፣ መረዳዳትንና እውነትን መቀበልን፣ ላይኞቹን ትዕግሥት፣ ትሐትናና ፍቅርን የመሳሰሉትን መገንቢያዎች ከየወዳደቁበት እናንሳና ራሳችንን ወይም የእኛነታችንን ቤተ መቅደስ እንሥራለት፤ ሀገራችንንም ከጥፋት እናድናት፡፡

እንግዲያውስ በዓለ ደብረ ዘይትን ስናከብር ጌታችን የእኛን ሰውነት ቤተ መቅደስ እያየ በጥላቻና በቂም በጥይትና በሥለት ሊፈራርስ መቅረቡን እያየ የሚያዝንብን መሆኑን በማሰብ ቢሆን የተሻለ ይሆናልና ስለ እኛው መቅደስ መፍረስ እንጨነቅ፡፡ የትሔደ ለምን አይሰማም ከማለትም ከመቅደሳችን ያባረርነው እኛው መሆናችንን አውቀን እንመለስ፡፡ ያንጊዜ እርሱን እንሰማዋለን፣ እርሱም ይሰማናል፡፡ አሁን በያዝነው መንገድ የምንሔድ ከሆነ ግን በርግጥም ይህ እግዚአብሔር የተለየው ሰውነት መቅደሳችን የሚተርፍ አይመስልም፡፡ አቤቱ ጌታ ሆይ ሀገራችን ኢትዮጵያንና ወገኖቻንን እንፈርስ ዘንድ አትለየን፣ አሜን፡፡ ምንም ቢሆን እንኳን ለበዓለ ደብረ ዘይት አደረሰን አደረሳችሁ፡፡

No comments:

Post a Comment