By
በሔኖክ ያሬድ
‹‹የያሬድ ስም ገናና የሆነው በዝማሬው ብቻ አይደለም፡፡ የቃላቱ ጣዕም፣ የቅኔዎቹ ረቂቅነትና የሐሳቡ ምጥቀት እኩያም የለው፤ እንዲያው ቀረብ ብለን ብናጠናው ለመላ የባህል ታሪካችን ዋና ምንጭ መሆኑ አይጠረጠርም፡፡ ግን ሊቃውንቶቻችን በጸሎትነት ሲዘምሩት፣ በተመስጦ ሲደጋግሙትና በረቀቀ ውዝዋዜ ሲያሸበሽቡት ነው የኖሩት እንጂ፣ ታሪካዊ ይዘቱንና ማኅበራዊ መልእክቱን ተንትነው በጽሑፍ አላቆዩንም፡፡ አሁን እኛ፤ ይህንን ለማድረግ መጀመር አለብን፡፡››
ይህ ከሠላሳ ዓመታት በፊት በታተመ አንድ የጥናት መጽሔት (ጆርናል) ላይ የታሪክ ምሁሩ ታደሰ ታምራት (ፕሮፌሰር) ስለ ስድስተኛው ምታመት ሊቅ ቅዱስ ያሬድ ሥራዎች በምልዐት አለመጠናቱ ያሳሰቡት ኃይለ ቃል ነበር፡፡ የቅዱስ ያሬድ ልሂቅነት ከዜማ ከማኅሌት ባለፈ ያለመተንተኑ ታሪካዊው ጥንተ ነገሩ ዘመኑና ትውልዱ እንዲያውቁት መጣና እንደሚገባም ያስተጋቡት የጥናት ደወል ነበር፡፡
ከ1504 ዓመታት በፊት የኖረው ቅዱስ ያሬድ ሚያዝያ 5 ቀን ልደቱ፣ ግንቦት 11 ቀን ደግሞ ዕረፍቱ (መስወሩ) የሚዘከርበት ነው፡፡ በተለያዩ ዘመናት በልደቱም ሆነ በመሰወሪያው ዕለት በተለያዩ ተቋማት የመታሰቢያ ዝግጅቶች ይብዛም ይነስም ሲቀርቡ ነበር፡፡ ኢትዮጵያ ሦስተኛውን ሺሕ ዓመት (ሚሌኒየሟን) በተቀበለችበት 2001 ዓ.ም. ዋዜማ፣ በጳጉሜን 2000 ዓ.ም. በሚሌኒየም አዳራሽ፣ በ1500 ዓመተ ልደቱ በባህል ማዕከል ከዜማና ቅኔ ጋር በተያያዘ ዝክረ ያሬድ ተከናውኖም ነበር፡፡
ጎልቶ ከሚነገረው ከዜማው በተጨማሪ ሊዘከሩ ከሚገባቸው የቅዱስ ያሬድ ትሩፋቶች አንዱ ከሥነ ጽሑፍ ጋር የተያያዘው ነው፡፡ ከጽሑፈ እብን (የድንጊያ ላይ ጽሑፍ) ወደ ጽሑፈ ብራና (የብራና ላይ ጽሑፍ) ሽግግር በተደረገበት ዘመነ አክሱም የሥነ ጽሑፍ መነሻው የቅዱሳት መጻሕፍት ከግሪክና ዕብራይስጥ፣ ከሱርስጥና ከዐረቢ ወደ ግእዝ መተርጐማቸው ነበር፡፡ የግእዝ ሥነ ጽሑፍ የልደት ዘመን ከትርጉም ጋር ቢያያዝም፣ ያሬድ ከተነሣ በኋላ ከአሥራው መጻሕፍት ላይ በመነሣት ያዘጋጃቸውና የደረሳቸው አምስቱ ዐበይት መጻሕፍት (ድጓ፣ ጾመ ድጓ፣ መዋሥእት፣ ዝማሬ፣ ምዕራፍ) የመጀመሪያ ሀገራዊ ሥራዎች መሆናቸው ይታወቃል፡፡
ዘንድሮ የማኅሌታይ ያሬድ የትውልድ ቦታ በሆነችው አክሱም ከተማ፣ የአክሱም ዩኒቨርሲቲ ግንቦት 11 ቀን የሚውለውን በዓሉን ምክንያት አድርጎ የጥናት ጉባኤ ለሁለት ቀናት አካሂዷል፡፡ በዐውደ ጉባኤው ከ31 ዓመት በፊት በፕሮፌሰር ታደሰ ታምራት ለተነሣው ጥያቄ ዓይነተኛ ምላሽ የሚሰጥ፣ ባንዳንዶች አገላለጽ የቅዱስ ያሬድን ልዕልና የሚያሳዩ ጥናቶች ታይተውበታል፡፡
የዕውቀት ጎዳና
ግንቦት 9 እና 10 በረምሃይ ሆቴል በተዘጋጀው ዐውደ ምርምር ከቀረቡት 11 ጥናቶች አንዱ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህር አቶ ይኩኖ አምላክ መዝገቡ ነው፡፡
አቶ ይኩኖአምላክ ‹‹ነገረ አእምሮ፡- ምን፣ እንዴት እንወቅ?›› በማለት በመጽሐፈ ድጓ ላይ የተመሠረተውን ጥናታቸውን አቅርበዋል፡፡
መንደርደሪያው፣ ‹‹አንተስ፣ አንተ ግን፣ አንተንኳ፣ አንተንማ ለማወቅ ብትሻ የምድርን (አፈር÷ ጠፊ የኾነውን) ሐሳብ ተው፡፡ ከዋክብትን ተሻገራቸው፡፡ የሕብረታቸውን - የአኳኋናቸውን ውበት ተመልከት፡፡ ከዚኽ ኸሉ እይታኽ ተነስተኽ በልቡናኽ የማይጨፈለቅ ሥሉስን ዐስብ›› የሚል ነው፡፡ የድጓውን የግእዝ ንባብ በዜማ ጭምር እያጀቡ፣ ትርጓሜውንም እያፍታቱ ዘልቀውበታል፡፡
አንድ ከባድ፣ የሚቻል የማይመስል ኃላፊነት ነው ሊቁ የጣለብኽ፡፡ ‹‹ከዋክብትን ተሻገራቸው፣ ዙራቸው፣ አገላብጠኽ እያቸው›› ነው ቃል በቃል ያለኽ፡፡ ይኽ እንዴት ነው እሚቻል? ሌላም ሥራ ጥሎብኻል፡ ‹‹ከዚኽ ተነስተኽ ዐስብ››፡፡ ኹለት ታላላቅ የነገረ አእምሮ ሐሳቦች ናቸው በዚኽች የድጓ ንባብ የተነገሩ፡፡
ሰው አንድን ነገር ከማወቅ ተነስቶ ሌላን ነገር ሊያውቅ ይችላል፡፡ የአእምሮ - የዕውቀት ተሸጋጋሪነትን ነው ይኽ የሚያስረዳን፡፡ ‹‹የከዋክብትን ሥን፣ ስንኝ፣ ሕብረት ተመልክተኽ ዐስብ›› ይላል፡፡ ማየት፣ መመልከት ለሐሳብ መነሻነት እንዲውል እንጂ ቆሞ እንዳይቀር ዐደራ ሰጠ፡፡ ያሬድ ኢትዮጵያዊ ካህን ነውና የቤተ ክርስቲያኑን አስተምህሮ ምን ጊዜም ከመናገር - ከመስበክ አልቦዘነም፡፡ በዚኽችም ዐጭር ድጓ ‹‹የማይጠቀለል ሥሉስ›› የኾነውን አምላክ ታውቅ ዘንድ መጻሕፍቱ ብቻ ሳይኾኑ ልቡናኽም ሊነግርኽ ይችላል - ይገባል›› አለ፡፡ ምናልባት ‹‹ኁባሬ - አብሮነት፣ አንድነት ከ‹‹ኑባሬ›› - መኗኗር ይልቅ መመረጡ ለዚኸ ትርጓሜ ሲባል ይመስላል፡፡
በዚኽች ድጓ የተነገረ ሌላው ቊም ነገር ‹‹አንተ ግን ለማወቅ ብትሻ›› በምትለው ሐረግ የተሰጠው ሐሳብ ነው፡፡ የትሕትና ውጤት ነው፡፡ በጥበብ፣ በከፍተኛ ሐሳቦች የታሸ ሊቅ ደረቅ ትእዛዛትን ከማውረድ ይልቅ ማስፈቀድ፣ ማስወደድ ይቀናዋል፡፡ ውስጡ ‹‹እባክኽ ማወቅን ውደድ›› የሚል አባታዊ ምክር አለ፡፡ እርሱን ተከትሎም የአስተዋወቅን ስልት የተለመው ‹‹በልቡናኽ ዐስብ፤ ከዋከብትን አልፈኽ ዙር፤ ይኸንም ለማድረግ ተራ ዐሳብን ተው›› የሚለው ትምህርት ተሰጠን፡፡ ያውና፡-
ይኽ ስልተ ድርሰቱ፣ አግባብቶ ማስተማሩ ከአውጋዦች፣ ከመራር ሰባኪዎች ይለየዋል፡፡ አስፈራርቶ አይነግርም፡፡
‹‹እነሆ ለሚያምኑ ታላቅ የምሥራች እንናገራለን›› አለ እንጂ ‹‹ይኽን የምሥራች ያልተቀበሉ ወዮላቸው›› አላለም፡፡ ይኸም ታላቅ የትምህርት አሰጣጥ ፍልስፍና ነው፡፡ ‹‹አእምሮ (ዕውቀት) በመውደድ እንጂ በመገደድ አይመጣም›› ብሎ የሚያምን ታላቅ መምህር ነው፡፡ ለዚያውም ሊያስገድድባቸው የተቈረጡለት ድንቅ አርጩሜዎች እያሉለት - እነ ገሃነመ እሳት፡፡
‹‹ሊታወቅ የሚችል ምንድነው?›› የሚለውን ጥያቄ ለቅዱስ ያሬድ ብናቀርብለት ሊሰጠን የሚችለውን መልስ ከዚኽች የድጓ ንባብ መገንዘብ እንችላለን፡፡ መልሱ ዐርበ ሰፊ ነው፡፡ ‹‹ሰው ነኽ፣ አፈር ነኽ፣ ደካማ ነኽ፣ ዐርፈኽ የታዘዝከውን ፈጽም›› ከሚለው ቃለ ሰባኪያን የሚለይ ይመስላል፡፡ በሕዋሳተ ሥጋ ሊቃኙ ሊዳሰሱ በሚችሉ ነገሮች መነሻነት በሕዋሳተ ሥጋ ሊቃኙ የማይችሉ ነገሮችንም ለማወቅ እንደሚቻል ነው እሚያስረዳን፡፡ በዚኽም ምክንያት ያሬድ ‹‹ኹሉንም ማወቅ አይቻልም›› ከሚሉት ይልቅ ‹‹ኹሉንም ማወቅ ይቻላል›› ወደሚሉት ይቀርባል፡፡ የአምላክን ባሕርየ መለኮት ዐስቦ ለማመን እንደሚቻል መንገሩ ለዚኸ ማስረጃ ነው፡፡
አኹን ‹‹እንዴት እንወቅ?›› እና ‹‹ሊታወቅ የሚቻል ምንድን ነው?›› ለሚሉት ጥያቄዎች ያሬዳዊ መልስ አግኝተናል - የሚበዛውንም ገና ወደፊት እንገኛለን፡፡ እንዴት እንወቅ? በመምረጥ (እማይረባውን በመተው)፣ ሩቅ መስለው የሚታዩንን ከዋክብት በመቅረብ፣ በመዞር - በመዟዟር፣ በመሻገር፣ በማሰብ፡፡ እኒኽን ካዋለድን የስንትና ስንት አዝማን ስንቅ ይኾኑናል፡፡ ምንስ ነው እኛ ልናውቅ የምንችል? ሥነ ፍጥረትን፣ ሥነ ፈጣሪን፡፡ ይኽ እጅግ በጣም ሰፊ ቢጋር ነው- ንድፍ፡፡
ሥነ ፍጥረትን ማወቅ እንዲቻል ከያሬድ በላይ የሰበከልን፣ ያሳየን ወገን የለንም፡፡ ከዝናብ ኮቴ እስከ ዕፀዋት ዝማሬ በያሬድ የተብራራ ሥነ ፍጥረት ነው፡፡ ነገረ መለኮትንም የተናገረበት አንደበት ልናውቅ፣ ልናደንቅ ስለሚቻለን ነገሮች ብዛትና ክብደት እጅግ በጣም ተስፋ ሰጪ ነው፡፡ ብዙ ልናውቅ፣ ብዙ ታላላቅ ነገሮችን ልንገነዘብ እንደምችል ትልሙ ተተልሟል - የኛ መዝራት - መሥራት ብቻ ይጠበቃል፤ ያሬድ ይጠብቃል በልቶ ዝም እንዳንኾንበት ልጆቹ፡፡
ባሕረ ሐሳብ
ስለ ኢትዮጵያ የዘመን አቆጣጠር (ባሕረ ሐሳብ) ጥንታዊ ማስረጃ ስለሚገኝበት መጽሐፈ ድጓ የቀረበ የጥናት ሐተታ የጉባኤው አካል የሆነው ‹‹ጽብራቆት በቅዱስ ያሬድ ሥራዎች›› በሚል በወልደ ያሬድ የቀረበው ነው፡፡
የድጓው ድርሰት በአራቱ ወቅቶች (ክረምትና መፀው፣ በጋና ፀደይ) ተመሥርቶ የተዘጋጀ ነው፡፡ በወቅቶቹ ባሕርያት ላይ ተመሥርቶ ያሬድ ከደረሳቸው መካከል ለአብነት ያህል የክረምትና የመፀው ድርሰቶቹን እነሆ፡፡
በየዓመቱ መስከረም 26 ቀን የሚብተውን (የሚጀምረውን) ከክረምት በኋላ የሚመጣውን መፀው (የአበባ ወቅት) እንዲህ ገልጾታል፡፡
‹‹በጊዜሁ ኅለፈ ክረምት ቆመ በረከት ናሁ ጸገዩ ጽጌያት››
- በጊዜው አለፈ አሁን የበረከት ጊዜ ይሆናል አበቦችም ያብባሉ፡፡
ሰኔ 26 ቀን የሚብተውን የኢትዮጵያ ክረምትንም
‹‹ደምፀ እገሪሁ ለዝናብ፣ ሶበ ይዘንብ ዝናብ ይትፌስሑ ነዳያን፤
ደምፀ እገሪሁ ለዝናብ፣ ሶበ ይዘንብ ዝናብ ይፀግቡ ርሁባን›› - የዝናብ ኮቴ ተሰማ፤ ዝናብ በዘነበ ጊዜ ነዳያን ይደሰታሉ፤ ርሁባንም ይጠግባሉ፡፡
ክረምት በሚወጣበት መስከረም 25 ቀን በአክሱም ታላቅ ሥነ በዓል ‹‹ተቀጸል ጽጌ›› (አበባን ተቀዳጅ) ይከበር ነበር፡፡ በዓፄ ገብረመስቀል ዘመን ሲከበር የተገኘው ቅዱስ ያሬድ ‹‹ተቀጸል ጽጌ፣ ገብረ መስቀል ዓፀጌ›› ብሎ ዘምሮ ንጉሡን እንዳስደሰታቸው ይወሳል፡፡ ይህ የአበባ በዓል እስከ 15ኛው ምእት ዓመት ድረስ በዕለቱ ሲከበር ቆይቶ በአፄ ዳዊት ዘመን የእግዚእነ ኢየሱስ ክርስቶስ ግማደ መስቀል መስከረም 10 ቀን ኢትዮጵያ መድረሱን ተከትሎ በዓሉ ‹‹ተቀጸል ጽጌ - ዓፄ መስቀል›› በመባል ከመስከረም 25 ወደ መስከረም 10 ተዛውሮ እስካሁን በቤተ ክህነት ተወስኖ እየተከበረ ይገኛል፡፡ ተቀጸል ጽጌን እንደ ቀደመው ዘመነ አክሱም ክረምት በሚወጣበት መስከረም 25 ማክበር ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ እንደሆነ ነው አቅራቢው ያመለከቱት፡፡
ከ55 ዓመታት በፊት ‹‹የከፍተኛ ትምህርት ዘይቤ›› ደራሲ እጓለ ገብረ ዮሐንስ (ዶ/ር) ያሬድና የኢትዮጵያ ሥልጣኔ በሚለው ጽሑፋቸው እንዲህ ብለው ነበር፡፡ ‹‹በአፍሪካ ምሥራቃዊ ዳርቻ የታወቀውን ሥልጣኔ ለማስገኘት ብዙ ሊቃውንት ጥረዋል፡፡ ሰማዩ ወይም ጠፈሩ ልሙጥ ነበር፡፡ የነዚህ ሰዎች ጥረት የሚያበሩ ከዋክብት በዚህ ጠፈር ላይ አስገኝቶአል፡፡ ምን ይሆናል ብዙ ደመና ሸፍኖቸአዋል፡፡ እነሱን ለመረዳት ክንፍ፣ ብርቱ የሕሊና ክንፍ ያሻል፡፡ ከማኅበረ ሊቃውንት አብነት ወይም ምስለኔነት ያለውን እንመርጣለን፡፡ ቅዱስ ያሬድ በዘመናት መካከል ለነበሩት ሁሉ የአገራችን ሊቃውንት እንደራሴነት ያለው ትልቅ መንፈስ ነው ብለን እናምናለን፡፡››
ከዐውደ ምርምሩ በተጓዳኝ በቅዱስ ያሬድ ሕይወትና ሥራ ላይ ያተኮረ በሚካኤል ሚሊዮን የተዘጋጀ የሙዚየም ቴአትርም ለዕይታ በቅቷል፡፡
‹‹ያሬድ ለአሁኑ ትውልድ ያበረከተው ሥራ ወደር የለሽ ቢሆንም ሥራዎቹን ግን የሚፈለገውን ያህል አላስተዋወቅናቸውም፤›› ያሉት የአክሱም ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ፀሐዬ አስመላሽ (ዶ/ር) ናቸው፡፡ ፕሬዚዳንቱ አያይዘውም እንደገለጹት፣ እጅግ በጣም ሰፊ የሙዚቃ የሥነ ጥበብና የሥነ ጽሑፍ ጥልቀት ያሳየ ሊቅ፣ አይደለም በዓለም በአገራችን ብዙ አይታወቅም፡፡ አክሱም ዩኒቨርሲቲ ክፍተቱን ግምት ውስጥ በማስገባት የሊቁ ሥራዎችና ቅርሶች በሚገባ በማጥናትና በማስተዋወቅ ታሪኩን ለመጠበቅ ጥረቱን እንደሚቀጥልም ሳይገልጹ አላለፉም፡፡
Source :- EthiopianReporter
No comments:
Post a Comment