Tuesday, May 16, 2017

የፓትርያርክ ቴዎፍሎስ የመጨረሻዋቹ ሰዓታት


ሐምሌ 7 ቀን 1971 ዓ.ም ዕለተ ቅዳሜ ከታላቁ ቤተ መንግሥት ምድር ቤት እስረኞች መካከል የክርስትና እምነት ተከታዮች የሆኑት በጠዋት ተነስተው በአባቶች መሪነት ጸሎት አድርሰዋል፡፡ የቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ደውል ድምፅ ሲያስተጋባ ሰምተዋል፡፡ ፈጣሪያቸውን አውቀው በድፍረት ሳያውቁ በስህተት የፈፀሙትን በደል ይቅር እንዲላቸው ተማጽነዋል፡፡ ከጸሎት በኋላ እስረኞቹ ጧት ጸሐይ ለመሞቅና አየር ለመቀበል የተፈቀደላቸው ለ45 ደቂቃ ጊዜ አጠናቀው ወደየክፍሎቻው ተመልሰው ተቆልፎባቸዋል፡፡ የሐምሌ ጸሐይ በቀዝቃዛው በታላቁ ቤተ መንግሥት ምድር ቤት ውስጥ የታጎሩትን ታላላቅ ኢትዮጵያውያን ለማጽናናት የተላከች ይመስላል ፤ ሰማዩን በጋረደው ደመና መካከል ብልጭ ድርግም ትላለቸው፡፡


ከቀኑ 6፡00 ሰዓት ላይ ከእስረኛ ክፍል ቁጥር 2 የሚፈለጉት ሰዎች ሥም ዝርዝር በመጥራት ‹‹ራቅ ወዳለ ቦታ ስለምትሄዱ ብርድ ልብስ እና ሶፍት ያዙ›› ተብሎ ተነገራቸው… በመቀጠልም ወደ ክፍል 1 በእስረኞች አለቃ አማካኝነት የሚፈልጉትን የእስረኛ ስም መጥራት ጀመሩ …
‹‹ልጅ ካሳ ወ/ማርያም ፤ ብ/ጀ ሳሙኤል አበበ !›› ከዚያም ‹‹ ወደ ውጭ ትፈለጋላችሁ ፤ የምትሄዱበት ራቅ ወደአለ ቦታ ስለሆነ የብርድ ልብስና የሽንት ቤት ወረቀት ያዙ ተብሏል›› አሉ፡፡
 
በዚህ ጊዜ ልጅ ካሳ ወ/ማርያም ወደ ፓትርያርክ ቴዎፍሎስ ቀርበው ፤
‹‹ አባታችን ሊገሉን ነው ፤ ይፍቱኝ ›› አሏቸው ፡፡ እሳቸውም ‹‹እግዚአብሔር ይፍታ ፤ አይዞህ አትፍራ ሥጋህን እንጂ ነፍስህን አይገድሏትም›› አሏቸው፡፡ ልጅ ካሳ ወ/ማርያም መስቀል ተሳልመው ከወጡ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ፓትርያርክ ቴዎፍሎስ ስማቸው ተጠራ፡፡ ፓትያርኩ ስማቸው ሲጠራ ከደረጃው ሥር ወዳለው መኝታቸው በመሔድ የሚፈልጉትን ልብስ መርጠው ከለበሱ በኋላ ጸሎት ማድረስ ጀመሩ ፤ በዚህ ሁኔታ በርካታ ደቂቃዎች አለፉ ፤ የመንፈስ አባታቸው አቡነ ዮሐንስ ከዓመታት በፊት ‹‹.. ፍጻሜአቸው መከራ የበዛበት ይሆናል›› ብለው የተናገሩት ትንቢት ቀኑ ደረሰ፡፡ 

ከቁጥር 1 የተጠሩት ሌሎች እስረኞችና ከቁጥር 2 የተጠሩት አውቶማቲክ መሳሪያ ታጥቀው በተጠንቀቅ በቆሙ ወታደሮች እየተጠበቁ ቁጥር 1 በር አጠገብ ቆመዋል፡፡ የመቶ አለቃ ሚካኤል አመዴ ደጋግመው ፓትርያርክ ቴዎፍሎስን ይጣራሉ ፤ ‹‹ አባታችን እየተጠበቁ እኮ ነው !›› አሏቸው ፡፡ ፓትርያርኩ ጸሎታውን ካደረሱ በኋላ በእጃቸው የእንጨት መስቀል ጨብጠው 3 ዓመት ከ3 ወር ከ7 ቀን የቆዩባትን የደረጃ ስር ማረፊያቸውን ለቀው በዚያ ቁመታቸው አየሩን እየቀዘፉ ፤ በራሳቸው ላይ የመነኩሴ ቆብ አጥልቀው ፤ ከሀር የተሰራ ጥቁት የመነኩሴ ልብስ ለብሰው ፤ ከላይ ካባ ደርበው ፤ የቆዳ ነጠላ ጫማ ተጫምተውና በግርማ ሞገስ ቀና ብለው ወደፊት እያዩ ከማረፊያቸው ወጡ ፤ ዶ/ር አበራ ጀምበሬ እንደጻፉት መስቀላቸውን እያማተቡ ግርማ ባለው አረማመድ ወጡ - የሚያስቸኩል ምክንያትም አልነበራቸውም፡ 

በዚህ ጊዜ ፓትርያርኩ ላይ በፊታቸው ላይ የሚነበብ አንዳች ፍርሀት ፤ ጭንቀት ምልክት አልነበረም፡፡ ይልቁንም የሚታይባቸው የመረጋጋት ስሜት ነበር፡፡ በክፍሉ ውስጥ የነበሩት ቀሪ  ታሳሪዎች ፊታቸውን ቅጭም አድርገው ዓይኖቻቸውን ተክለው ይመለከቷቸው ነበር፡፡ የእሳቸው አይን ግን በማንም ላይ አላተኮሩም ነበር፡፡ አቶ ንጉሤ ሀብተወልድ ፓትርያርኩ ተጠርተው ሲወጡ  የነበራቸውን ሁኔታ ሲገልጹ ‹‹ ሠዓሊ ሆኜ በዚየ ቁመታቸው አየሩን እየቀዘፉ በመካከላችን አልፈው ሲሔዱ በስዕል ማስቀረት ብችል እንዴት ደስ ባለኝ ነበር›› በማለት ነበር፡፡ 

የቁጥር 1 እስረኞች እንግዳ እንደሚቀበል ወይም እንደሚሸኝ ሰልፈኛ በሁለት ረድፍ ቆመዋል፡፡ ቴዎፍሎስ በመካከላቸው ሲያልፉ የሚመለከቷቸው ለመጨረሻ ጊዜ እንደሆነ አልተጠራጠሩም፡፡ እሳቸውም የነገ ጠዋቱን 45 ደቂቃ ጸሐይ አብረዋቸው እንደማይሞቁ ተረድተዋል፡፡ ከአራት ቀን በፊት ሐምሌ 3 ጸሐፌ ትዕዛዝ ተፈራ ወርቅ ኪዳነ ማርያም ፤አቶ ሰይፉ ማኅተመ ሥላሴ ፤ ሐምሌ 5 ቀን ደግሞ አቶ አበበ ከበደ እና አቶ አሰፉ ድፋዬ በዚሁ ሁኔታ ተጠርተው ወጥተው ሳይመለሱ ቀርተዋል ፡፡ ዛሬ ደግሞ ሐምሌ 7 ነው፡፡

ፓትርያርኩ መደዳውን በቆሙት እስረኞች መካከል ሲያልፉ ‹‹ አይዟችሁ የሥጋ ሞት አትፍሩ ፤ የሚያስፈራ ዳግም ሞት ነው ፤ እግዚአብሔር ከዳግም ሞት ያድናችሁ›› ብለው እያጽናኑ መንገዳቸውን ቀጠሉ፡፡ ሞት ከእያንዳንዱ እስረኛ ከጥቂት ጫማዎች ርቀት ላይ ሆኖ ቢለዋውን እየሳለ ነበር፡፡ የማይታወቀው ቅደም ተከተሉ እንጂ ሁሉም ሞት ተደግሶላቸው ነበር፡፡

ፓትርያርኩ ቀደም ካሉት እስረኞች ጋር ከተቀላቀሉ በኋላ ከሚጠብቃቸው መኪና ላይ እንደተሳፈሩ አይኖቻቸውን በጥቁር ጨርቅ ሸፈኗቸው፡፡ መኪናው የታላቁን ቤተመንግሥት ግቢ ለቆ ወደ አራት ኪሎ አመራ ፤ አውቶማቲክ መሳሪያ የታጠቁ ወታደሮች በቅርብ ርቀት ላይ እስረኞችን መከተል ያዘች ፡፡ እስረኞቹ የተገኙበት መኪና ውስጥ ጸጥታ ሰፍኗል፡፡ እንዳያዩ አይኖቻቸው ተሸፍነዋል ፤ ጆሯቸው ግን በመንገድ ላይ የሚተላለፉ የመኪና ድምጾችን ይሰሙ ነበር ፤ መኪናዋ ፓርላማውን በቀኝ ፤ የነጻነት ሃውልትን በግራ ፤ የዳግማዊ ምንሊክ ት/ቤትን በቀኝ ፤ ፓትርያርኩ መንበረ ፓትርያርክ ቀድሰው ያቆረቡበት ፤ ቆመው ያስተማሩበት ፤ የፕትርክና ማዕረግን ያገኙበትን  በግራ አድርጋ ፤ አንበሳ ግቢን በቀኝ ፤ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን በግራ እያለች እንጦጦ ተራራን ሽቅብ ወጥታ ልዑል ራስ አስራት ካሳ ግቢ ደርሳለች ፡፡

ፓትርያርኩ የሚገኙበት መኪና ልዑል ራስ አስራት ካሳ ግቢ ዋናው በር ላይ ተጠግቶ ቆመ ፤ በሩ ላይ ቆሞ የነበረው ተረኛ ወታደር ጠጋ ብሎ የሥራ ባልደረቦቹ እንደሆኑ ካረጋገጠ በኋላ በሩን ከፈተ ፤ መኪናዋም ሰተተ ብላ ገብታ ቆመች፡፡ እስረኞቹም ከመኪኖቻቸው ከወረዱ በኋላ አይናቸው ላይ የተጋረደባቸው ጨርቅ ተፈታላቸው፡፡ ግቢው ግርማ ሞገስ የተላበሰ የተንጣለለ በአታክልት የተሸቆጠቆጠ ነበር ፤ ፍጹም ሰላም የሰፈነበት ግቢ ፤ እስረኞቹም ይህ ግቢ ከዚህ በፊት ግብዣ ተጠርተው በልተው ጠጥተው ተደስተው ወጥተውበት ነበር ፤ ዛሬ ግን ሌላ  ግብዣ አዘጋጅቶ ታዳሚያን አድርጎ ጠርቷቸዋል፡፡ የግቢው ባለቤት ሕዳር 14 ቀን 1967 በግፍ ከርቸሌ ግቢ ውስጥ የኃይለስላሴ  ባለስልጣናት ጋር ከተረሽኑት አንዱ ናቸው፡፡

በግቢው ውስጥ በእጃቸው መሣሪያ ያልያዙ ፤ አካላቸው የደነደነ ወታደሮች ውር ውር ይላሉ፡፡ ልዩ ሃይል(Special Force)  ወይም ‹ተወርዋሪ ኃይል› ጦር አንዱ ክንፍ የሚኖረው እዚህ ግቢ ውስጥ መሆኑን እስረኞቹ አያውቁም፡፡ የወታደሮቹ ብዛት 60 ነው፡፡ ይህ ግቢ መንግሥት ከወረረሰው በኋላ የኩባ ሰራዊት ይኖርበት ነበር፡፡ የኩባ ሰራዊት ወደ ሐረርጌ ከሄደ በኋላ ልዩ ሃይል(Special Force) እንዲኖሩበት ተደርጓል፡፡ የሰፈሩት የጦር አባላት አሰልጠኝ ኮ/ል ዘርይሁን አጋፋሪ ሲሆን ወታደሮቹን እንዲያሰለጥን የመደበው ደግሞ የሕዝብ ደሕንነት ሚኒስትሩ ኮ/ር ተስፋዬ ወ/ሥላሴ ነበሩ፡፡ ኮረኔሉ እናታቸው ያወጣችላቸው ስም ‹‹ዘርይሁን›› ነበር ዛሬ ግን ዘር ለማጥፋት ሰዎችን ወደ ሞት እየገፉ ነበር፡፡

ከቤተ መንግሥት የመጡ እስረኞች ዓይኖቻቸውን አፍጥጠው ቀድሞ በቦታው ከነበሩ ሰዎች ጋር ተቀላቀሉ ፤ እነርሱም ከተለያዩ ቦታ የሞት ፍርድ የተፈረደባቸው እስረኞች ነበሩ ፤ የሚያነክሱ ፤ በእጃቸው ብርድልብስ የያዙ ፤ ትናንሽ ቋጠሮዎችን ያዘሉ ፤ የተቦጫጨሩ ሰዎች….አብዛኞቹ እስረኞች ይተዋወቃሉ ፤ ነገር ግን ቀጥሎ ያለውን ድርጊት ስለማያውቁት ፈገግታ የከዳውና ጉም የለበሰ ፊት ተሸክመዋልለለ ፤ አንዳንዶቹ ከፓትርያርኩ መስቀል ቀረብ ብለው ይሳለሙ ነበር ፤ ተራማጆች ነን የሚሉ ደግሞ በመጨረሻዋ ሰዓት እንኳን ፊታቸውን ሊፈቱላቸው ፍቃደኞች አልነበሩም፡፡ 

ኮ/ል ዘርይሁን አጋፋሪ ወታደር ዘውዱን ጠርቶ ወደ ቢሮው ወሰደው ፤ ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ  ወታደር ዘውዱ የ15 ሰዎች ሥም ዝርዝር ያለበትን ወረቀት ከውስጥ ይዞ ብቅ አለ፡፡ ለወታደሩ የተሰጠው ትዕዛዝ ወረቀቱ ላይ ያሉትን ሥሞች በቀደም ተከተላቸው እየጠራ ወደ ውስጥ እንዲዘልቁ ማድረግ ነበር፡፡ በመጀመሪያው ረድፍ ላይ የፓትርያርኩ የአቡነ ቴዎፍሎስ ስም ነበር፡፡ ወታደሩ እስረኞቹ ከቤቱ በስተግራ በኩል እንዲሰለፉ አዘዛቸው ፤  በዚሁ መሰረት  ስማቸው ሲጠራ ቋጠሮቻቸውን እንደያዙ የተተከሉትን አታክልት ተጠግተው ከፓትርያርኩ ጀርባ ተሰልፈው ቆሙ ፤ ቀጥሎም ‹ስማችሁ ሲጠራ የያዛችሁትን ቋጠሮ እዚሁ ትታችሁ ወደ ውስጥ ትገባላችሁ› የሚል መመሪያ ከሰጠ በኋላ ፡፡ ወታደር ዘውዱም በመጀመሪያ ‹‹ አቡነ ቴዎፍሎስ ..ይግቡ›› አለ፡፡ ፓትርያርኩም ቀና ብለው ካዩት በኋላ ደረጃውን እየተራመዱ ወጡ፡፡ በዚያች ቀን እድሜያቸው 69 ዓመት ከ 2 ወር ነበር ፡፡

ፓትርያርክ ቴዎፍሎስ ከውጭ ወደ ቤቱ የሚያስገባውን ደረጃ ወጥተው ሳሎኑን አቋርጠው ወደ ኮሪደሩ የሚወስደው በር ላይ እንደደረሱ ኮ/ል ዘርይሁን ‹‹ወደዚህ ..ወደዚህ አላቸው›› ፤ ወደተባሉበት ቦታ አመሩ ኮ/ል ዘርይሁን ፊትለፊት ተቀምጦ ታያቸው ፤ አጠገቡ ሊደርሱ ትንሽ ሲቀራቸው ‹‹ እዚያው ይቁሙ›› የሚል ትዕዛዝ ተላለፈላቸው፡፡ ፓትርያርኩ ትኩር ብለው ያዩት ነበር ፤ ኮረኔሉም ትኩር ብሎ አያቸው ፤ ያውቃቸዋል ….በደንብ ያውቃቸዋል…

‹‹አዎን አንድ ጊዜ ታላቁ ቤተመንግስት በነበረበት ጊዜ አይናቸውን ታመው ክቡር ዘበኛ ሆስፒታል ለሕክምና ሲላኩ አጅቦ አድርሶ መልሷቸው ነበር ፤ ሁኔታውንም እንዲህ ነበር

ፓትርያርክ ቴዎፍሎስ ታላቁ ቤተመንግሥት እስር ቤት ከገቡ በኋላ ዓይናቸውን ለመታከም ጃል ሜዳ ክቡር ዘበኛ ሆስፒታል ይባል ወደነበረው የሕክምና ተቋም ሲላኩ ኮ/ል ዘርይሁን አጅቦ ሲሄዱ አራት ኪሎ ይደርሳሉ ፤ ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን አጠገብ እንደደረሱ ፤ የሁለቱ መንታ ሕንጻዎች መገንባት ፍጥነቱን ተመልክተው ..
‹‹ጎሽ ! ጎሽ እነዚህ ሰዎች ሰውን ማሰርና መግደል ብቻ ሳይሆን ሥራም ያውቃሉ ማለት ነው›› ብለው ሲያበቁ ዞር ብለው ኮ/ልን
‹‹አንተ ሀገር የት ነው ?›› አሉት
ኮረኔሉም ‹‹ማቻክል›› ብሎ መለሰ
እርሳቸውም ‹‹ ታዲያ የማቻክል ልጅ ከሆንክ እስከ ዛሬ ለምን አልጠየከኝም? ›› አሉት
እሱም ‹‹ ዛሬ እኮ እንዳጅብዎት የተመደብኩት ለዚህ ነው አላቸው››
‹‹ደግ ይሁን ›› አሉ..
ኮ/ል ዘርይሁን ከዚህ በፊት በእንዲህ አይነት ሁኔታ በደንብ ያውቃቸው ነበር ፤ ዛሬ ግን በቀነ ጎዶሎ  ሊገደሉ ከፊቱ ቆመዋል፡፡

ኮ/ል ዘርይሁን በስህተት ሌላ ሰው እንዳይገድል በመጠንቀቅ ፤ የስም ዝርዝር የተጻፈበትን ወረቀት ከተመለከተ በኋላ ቀና ብሎ ‹‹ አቡነ ቴዎፍሎስ ነዎት አላቸው ›› ፤ እርሳውም ‹‹አዎን›› አሉት ፤ በማስከተልም ‹‹ወደ እኔ ጠጋ ይበሉ አላቸው›› ፤ ፓትርያርክ ቴዎፍሎስም ወደፊት በመራመድ ላይ እንዳሉ ከጨለማው ቦታ ውስጥ ቆሞ የነበረው ወታደር ወፍ ለመያዝ አድብታ እንደምትጠብቅ ድመት ከተደበቀበት ድንገት ተወርውሮ በሁለት እጆቹ ላይ ጠምጥሞ አጥብቆ የያዘውን ገመድ በአንገታቸው አስገባ ፤ ገመዱም እንዲሸበብ ከጉልበቱ ሸብረክ በማለት በራሱ ዙሪያ ተሸከርክሮ በማጎንበስ ነፍሳቸው እስክተወጣ በጀርባው ተሸከማቸው ፡፡ ነፍሳቸው መውጣቷን ሲያረጋግጥ ከአለቃው ፊት እንደ ግንድ ወረወራቸው ፡፡ ከዚያም በመሬት እየጎተተ ለሬሳ ማከማቻ ወደተዘጋጀው ክፍሎ ወሰዳቸው ፤  መጀርባም ዘረጋቸው…..
ከእሳቸውም ቀጥሎ እስከ 9፡30 ድረስ አንድ በአንድ ግቢው ውስጥ ያሉትን እስረኞች በዚህ ሁኔታ ጨረሷቸው ፤..  

ኮ/ል ለገሰ በላይነህ ግድያው እንደመፈጸሙ ሪፖርት ከደረሳቸው በኋላ መጥተው ከባሕር እንደወጣ አሳ መደዳውን የተነጠፈውን የሟች አስከሬን በመመለከት ወሬ ወደውጭ እንዳይወጣ ትዕዛዝ ሰጥተው እዛው እንዲቀበሩ አደረጉ፡፡

ይህ የግድያ ቲያትር ላይ የተሳተፉ ወታደሮች በሚቀጥለው ቀን በማዕከላዊ ምርመራ ወጪ ሶደሬ ሔደው እንዲዝናኑ ተደረገ ፤ ዘግናኙን ድርጊት ረስተው ለተመሳሳይ ዘግናኝ ግድያ እንዲዘጋጁ ለማድረግ ፤ከዚያ ሲመለሱ ገመድና ጓንት ይታደላቸዋል .. ወደ ቀደመ ስራቸው በሌላ ተልዕኮ ይሰማራሉ ፤ የሰው ልጅ አንገትን እንደ ዶሮ እየሸበቡ ያሳርፋሉ ፤ ለእነሱ ሕይወት ማለት ይኽው ነው….. ዛሬስ ግፍ አድራጊዎች ሕሊናቸው በምን የጸዱት ይሆን? የትስ ሀገር ቢኬድ ከሕሊና ዳኝነት ማን ይተርፍ ይሆን? መፍትሄው እንደሰው ሆኖ በማሰብ ማድረግ እና መደረግ የሌለበትን ነገር መለየት ብቻ ነው ….. 

አቡነ መርቆሬዎስ ፓትርያርክ ከሆኑ በኋላ ቤተክርስቲያን ለሌ/ኮ መንግሥቱ ኃ/ማርያም እንዲ ብላ ላከች ፤ ‹‹ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ በሕይወት አሉ ወይስ የሉም? በሕይወት ከሌሉ ጸሎተ ፍትሀት ልናደርግላቸው ይገባናል፡፡››  ሌ/ኮ መንግሥቱም በቁጣ ‹‹ ምን አድርግ ነው የምትሉኝ? ይኽው ሁለት ጳጳሳት ፤ ሁለት የካህናት ተወካዮች ፤ ሁለት የምዕመናን ተወካዮች የፈረሙበት ወረቀት …እርምጃ ይወሰድልን ብላችሁ የጠየቃችሁት እናንተ አይደላችሁም እንዴ? ››አሉ፡፡ ሚዛን የማያነሳ መልስ፣፣፣…ገነት አየለ ስትጠይቃቸውም ‹‹ይህን የሚያውቀው ተስፋዬ ወ/ሥላሴ ነው አሉ›› ነገር ግን የመጀመሪያ ልጃቸው በ1980ዎቹ መጀመሪያ አካባቢ በአንድ አጋጣሚ የቤተሰብ ወዳጅ በሆነ ሰው ቤት የአቡነ ቴዎፍሎስን ፎቶ ግራፍ አልበም ውስጥ አይታ ወደ ቤት ከተመለሰች በኋላ ‹‹እኒያ የድሮ ጳጳስ ዘመዳችን መሆናቸውን ታውቅ ነበር? ብላ ስትጠይቃቸው መንግሥቱም እየተርበተበቱ ‹‹ አይ አላቅም ነበር …ታዲያ …. እኮ… ጥፋተኛው እሳቸው ናቸው …. እኔ ምን ላድርግ? ›› ብለው ነበር፡፡ ኮ/ል ተስፋዬ ወ/ሥላሴ በገመድ አንቀው ሰዎችን የገደሉትን የልዩ ኃይል አባላት ሰብስበው እንዲያመሰግኑላቸው ሲያዟቸው  መንግሥቱ ሟቾቹ እነማን እንደሆኑ አያውቁም ነበር? ….

ምንጭ ፡- ቀዳማዊ ቴዎፍሎስ ፓትርያርክ (የሕወት ታሪክ)
 ፀሐፊ - ታምራት አበራ ጀምበሬ
አዲስ አበባ
2009
       

No comments:

Post a Comment