በዘመኑ በዓለም ከነበሩት ኃያላን መንግሥታት አንዱ ቀዳሚ የነበረው የአክሱም ዘመነ መንግሥት፣ በሥልጣኔው ጫፍ የነካ እንደነበር ቢወሳም፣ እስከዛሬ የአክሱም ነገረ-ሥልጣኔ ከአምስት በመቶ በላይ አለመጠናቱን ተመራማሪዎች ይናገራሉ፡፡ በተለይ በሥነ ሕንፃ፣ ሥነ መድኃኒት፣ ቅርጻ ቅርጽ፣ አስተዳደር፣ የሥልጣን ሽግግር፣ የሥነ ከዋክብት፣ ንግድና እርሻ፣ የባህር ላይ እንቅስቃሴ ጫፍ ለነካው ለዘመኑ ቴክኖሎጂም ግራ የሚያጋቡ እንደሆኑ ምርምሮች ያመለክታሉ፡፡
የሥልጣኔውን ልዕልና ይመሰክሩ ዘንድ በተለይ የአክሱም ዘመነ መንግሥት በተቆረቆረበት መንደር ዛሬም ድረስ ቆመው የሚገኙት ከአንድ ድንጋይ የተጠረቡ ሰማይ ጠቀስ ሐውልቶቹ፣ በትግራይና በዛሬ ኤርትራ አካባቢ የሚገኙ በሺሕ የሚቆጠሩ ከተራራ የተፈለፈሉ የሕንፃ ሥራዎች፣ መቃብሮችና ከመሬት ወለል በታች በቁፋሮ በመገኘት ላይ ያሉት (ከአክሱም ዘመንም ቀድመው የተሠሩ) ቤተመንግሥቶችና በውስጣቸው የሚገኙ ጥንታዊ ቁሳቁሶች የተመራማሪዎች ቀልብ እየሳቡ ሲሆን፣ አንድ ነገር ግን የተዘነጋ ይመስላል፡፡
ብዙዎቹ ምሁራን እንደሚሉት፣ የዘርፈ ብዙ የአክሱም ሥልጣኔ መሠረት የሆነው የግዕዝ ቋንቋ ኃይማኖታዊ ቋንቋ ብቻ እስኪመስል ድረስ በቤተክርስቲያን ተወስኖ በመቅረቱ፣ ከዘመናዊ ትምህርት ተጣጥሞ አለመሰጠቱ፣ በቋንቋው ተጽፈውና ተሰናድተው በየገዳማቱና በዓለም ተበታትነው (ተወስደው) የሚገኙ መጻሕፍት የግዕዝ ምስጢሮች እንዳይታወቁና ተገቢ ምርምር እንዳይካሄድባቸው ምክንያት ሆነዋል፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን የግዕዝ ቋንቋ ሥነ ጽሑፍ፣ የግዕዝ ፊደላትና የግዕዝ ቁጥሮች የወጣት ምሁራንን ቀልብ እየሳቡ መጥተዋል፡፡
አሁን አሁን አንዳንድ የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች የግዕዝ ማዕከላት በመክፈት በዚሁ የጥንታዊ ኢትዮጵያውያን መግባቢያ የሆነውን ግዕዝ ቋንቋ ለማስተማር ጥረት እያደረጉ ነው፡፡ እስከዛሬ ቋንቋው ለቤተክርስቲያን አገልግሎት ከመዋሉና ከቋንቋው ፈተናነት ውጪ እዚህ ግባ የሚባል ጥናትና ምርምር ሲደረግበት አይስተዋልም ነበር፡፡
ለጉዳዩ ትልቅ ትኩረት ከሰጡ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መካከል የመቐለ ዩኒቨርሲቲ አንዱ ሲሆን፣ የግዕዝ ማዕከል በማቋቋም ምርምር ማካሄድ ጀምሯል፡፡ ‹‹ያሬድ የኢትዮጵያ ጥንታዊ ጽሑፍና ብራና ጥናቶች ማዕከል›› ይባላል፡፡ ማእከሉ በመቐለ ዩኒቨርሲቲ ዓደ ሐቂ ግቢ ውስጥ የሚገኝ ሆኖ ኅዳር 2008 ዓ.ም. ተቋቁሞ በግዕዝና ተያያዥ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ በርከት ያሉ አውደ ጥናቶች አዘጋጅቷል፡፡ መደበኛ ባልሆነ መልክ በዩኒቨርሲቲው የግዕዝ ትምህርት ይሰጣል፡፡ መደበኛ የሆነ ትምህርት ለመስጠትም ሥርዓተ ትምህርት ቀረጻ ላይ መሆናቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡
ሰሞኑን ‹‹አገር አቀፍ የግዕዝና ፊደል አውደ ጥናት›› በሚል ያሬድ ማዕከል ሦስተኛውን የምርምርና አውደ ጥናት (ጉባኤ) ያዘጋጀ ሲሆን፣ ከአገር ውስጥና ከውጭ አገር የምርምር ሥራዎች ቀርበው ውይይት ተካሂዶባቸዋል፡፡ የመጀመርያው ጉባዔ 2007 ዓ.ም. በባህር ዳር ሁለተኛ ጉባዔ ደግሞ ባለፈው ዓመት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲዎች የተካሄዱ መሆኑን የማዕከሉ ሕዝብ ግንኙነት መምህር ገብረጽዮን መሐሪ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
የማዕከሉ አስተባባሪ ዶ/ር ሐጎስ አብርሃና የመቐለ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ክንደያ ገብረ ሕይወት መክፈቻ ንግግር አሰምተው ሦስተኛው አገር አቀፍ የግዕዝ ጉባኤ፣ በይፋ የተከፈተ ሲሆን፣ ከአሥር በላይ ጥናቶች ቀርበዋል፡፡
በግዕዝ ላይ ዕውቀት ያላቸው የኦርቶዶክስ ኃይማኖት መዘምራንና ሊቃውንት በጉባኤው ላይ የተገኙ ሲሆን፣ ቁጥራቸው በርከት ያሉ የቋንቋና የሥነ ጽሑፍ ተመራማሪዎችም ታድመዋል፡፡ የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብም እንዲሁ፡፡
የመቐለ ዩኒቨርሲቲ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ፕ/ር ምትኩ ኃይለ ባቀረቡት መልዕክት፣ አንዳንድ አስገራሚ ነጥቦችን ያሰሙ ሲሆን፣ በተለይ ደግሞ በጀርመንና በተቀሩት አውሮፓ አገሮች ዛሬ በምርምር ተገኝተዋል ተብለው ኢትዮጵያን ጨምሮ ወደ ተቀረው ዓለም እየተሰራጩ የሚገኙ መድኃኒቶች ቅመማ፣ የሥነ ሕንፃ ዕውቀትና የብረት ማቅለጥ ቴክኖሎጂ በጥንታዊ የግዕዝ መጻሕፍት እንደሚገኙ ጠቆም አድርገው፣ እስከ ዛሬ ተገቢ ምርምር አለመደረጉ እንደሚያስቆጭ ተናግረዋል፡፡
‹‹ግዕዝ ውስጥ የሌለ ነገር የለም፤ ፊደላቱ፣ ቁጥሮቹም፣ ፍልስፍናው ዕድገቱ መጠናት ይኖርበታል፤›› በማለት በየገዳማቱ እስከ 500 ሺሕ የሚደርሱ ጽሑፎች እንደሚገኙ በመግለጽ እስከዛሬ ግን እዚህ ግባ የሚባል ጥናትና ምርምር አልተደረገባቸውም ብለዋል፡፡ ‹‹ወጣት ምሁራን ግዕዝን እንደ ትልቅ የዕውቀት ጎተራ አድርጋችሁ ተመልከቱት፤›› በማለት ፕሮፌሰር ምትኩ የቁጭት ንግግራቸውን ቋጭተዋል፡፡
የፕሮፌሰሩ ንግግር ሳይደርቅ በዕለቱ ከቀረቡ አሥር ምርምሮች ቀዳሚዎቹ ከጀርመንና ከአሜሪካ በመጡት የግዕዝ ቋንቋ ተናጋሪዎች የቀረቡ ነበሩ፡፡ ጀርመናዊው ፈረን ረይነር ቮይት፣ ንግግራቸውን የጀመሩት በግዕዝ ቃላት እያዋዙ ሲሆን፣ በበርሊን ዩኒቨርሲቲ የግዕዝ ተቋም ተመራማሪ ናቸው፡፡ ‹‹The
Gerund in classical Ethiopic›› በሚል ርዕስ ነበር ጥናታዊ ጽሑፋቸውን ያቀረቡት፡፡
ትግርኛ፣ አማርኛና ሌሎች የሴም ቤተሰብ ቋንቋዎችን ከላቲን እያነፃፀሩ አናባቢና ተናባቢያቸውን፣ ከግዕዙ የተወሰኑ ፊደላትና ድምጸት ለይተው አቅርበዋል፡፡ ጥናታቸው በዋናነት በእንግሊዘኛ ቋንቋ የቀረበ ቢሆንም፣ በመሃል የግዕዝ ሐሳቦችንና ዓረፍተ ነገሮችን ጣል ጣል እያደረጉ ነበር፡፡ የግዕዝ ፊደላትና ቃላት፣ ትግርኛና አማርኛ የተወራረሱበት አግባብንም አመላክተዋል፡፡
ዕጩ ዶ/ር ኢስቤላ ዛውግ በበኩላቸው፣ ከአሜሪካ ዋሽንግተን ዩኒቨርሲቲ የመጡ ናቸው፡፡ ‹‹Geez
In The Interface: Coding For Linguistic Continuity In The Face of Digital
Extinction›› በሚል ጥናታቸውን ያቀረቡ ሲሆን፣ በግዕዝ ቋንቋ አንቱ የተባሉ አሜሪካዊት ናቸው፡፡ ምሁሯ እንደሚሉት፣ ለቋንቋው በቂ ትኩረት ካልተሰጠ በዲጂታል ዘመን ምክንያት ግዕዝ አሁንም ካለበት ደረጃ ጨርሶ የመጥፋት ሰፊ ዕድል ሊገጥመው ይችላል፡፡ ለአንድ ቋንቋ መጥፋት ዋና ምክንያት ያሏቸውን አራት ነገሮች ማለትም ቅኝ መገዛት፣ ሉላዊነት፣ ከተሜነት መስፋፋት እንዲሁም ዲጂታል ዘመንን ጠቅሰው፣ በዲጂታል ድረ ገጽ ኮምፒውተር የቋንቋውን አጠቃቀም ዲጂታል ለማድረግ በቂ ትኩረት እንዲሰጥ ጠይቀዋል፡፡ ድምዳሜያቸውም፣ ‹‹መፃኢያችን ምን እንደሚመስል መጀመሪያ ማወቅ ይኖርብናል›› የሚል ግብ አስቀምጧል፡፡ ታሪካዊ፣ ሀብታምና የሥልጣኔ መሠረት የሆነው ቋንቋ መጥፋት የማንነት መዛባት፣ የባህል መበረዝና የትውልዶች አለመቀባበል ሊያጋጥም እንደሚችልም ጠቁመዋል፡፡
ዶ/ር ኢሳያስ ታጀበ የግዕዝ ፊደላት ቅርፅ ባህሪና አወራረስ ዙሪያ ጽሑፍ ያቀረቡ ሲሆን፣ በተለይ ለሳሆ (ኢሮፕ) ቋንቋ እንዲመች ተደርጎ የቀረበበትን በምሳሌያዊነት በመጥቀስ፤ የግዕዝ ገበታ የሴም ዘር ግንድ ላልሆኑት ኦሞቲክ ቋንቋዎችም ጭምር ጥቅም ላይ ሊውል የሚችልበት መንገድን አሳይተዋል፡፡ መጠነኛ የጽምፅና የቅርፅ ማሻሻያም ተደርጎባቸው አሳይተዋል፡፡
አቶ ሙሉጌታ ስዩም የተባሉ ተመራማሪ በበኩላቸው፤ የማሊ ቋንቋ ፊደል ግዕዙን መሠረት አድርጎ የተቀረፀበትን አግባብ አቅርበው፣ በርካታ የአፍሪካ የቋንቋ ምሁራን የግዕዝ ፈደላትን ለቋንቋቸው ጽሑፍ ለማዋል ፍላጎት ያላቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡
‹‹ሞክሼ ሆሄያትና የኢትዮጵያ ቋንቋና ጥናት›› በሚል በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሥነ ጽሑፍ መምህር የሆኑት አቶ ይኩኖ አምላክ መዝገቡ ባቀረቡት ጥናት አማርኛና ትግርኛ በጥልቀት ማጥናት ሲፈለግ ሥር መሠረቱ ግዕዝና ገበታው መሆኑን ጠቁመው፣ በተለይ በአማርኛ ተመሳሳይ ድምፅ ያላቸው ፈደላት እንዲቀነሱ የሚደረግ ዘመቻን አጣጥለውታል፡፡ ‹‹በዘመናችን እንኳንስ ሌላ ዓይነት ሊጨመር ከጥንት የቆየው ፈደልና ንባብ ሥርዓት፣ የፊደሉ አግባብ እንደ ጥንቱ አልተጠበቀም፡፡ የሚሠራው በልማድ በድፍረት ስለሆነ ሥርዓቱ ሁሉ ፊደሉም ሳይቀር መጉደልና ማነስ መናድና ማፍረስ፣ መጥፋት፣ መበላሸት ጀምሯል፤›› የሚለውን ጥቅስ ተውሰው፣ የፊደላቱ መቀነስ የሚያስከትለውን መዘዝ አስምረውበታል፡፡
‹‹ከዋክብትን ያጠፋ ትውልድ በጨለማ መዋጡ እንደማይቀር …..፣ ፊደሉ ይቀነስ የሚሉንም ኧረ ለኔስ ብርሃን ነው የሚበጀኝ እንበላቸው›› በማለት፣ ዘመቻው ‹‹ሃይ›› ሊባል ይገባል የሚል ድምዳሜያቸው በጭብጨባ የታጀበ ነበር፡፡ ሐ፣ኸ፣ ዐ፣ ጸ የመሳሰሉት ፈደላት ጥቅም ከዓረብኛም ጭምር እያመሳከሩ የመቀነስ አዝማሚያውን የቋንቋ ሳይንሳዊነት የሌለበት በማለት ይተቻሉ፡፡
መምህር ዙፋን ገ/ሕይወት፤ መምህር ደሳለኝ ኪሮስና ሀብተ ንጉሥ፣ ዶ/ር ፍሬሕወት ባዩ እንዲሁም መምህር ተወልደ ብርሃን መዝገበ፣ በግዕዝ ገበታ ቁጥሮች አጠቃቀም፤ መወራረስ፣ ምሥጢራዊ መልዕክት በማስተላለፍና ተያያዥ ጉዳዮችን የሚመለከቱ ምርምሮች አቅርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡
Source :- EthiopianReporter
dink tsihuf new ,mechereshawen egzeabeher yasamirew.
ReplyDeleteDr or Ato Mulugeta Seyou?
ReplyDelete