አንድ አድርገን መጋቢት
2 2009 ዓ.ም
‹‹በጅማ ዩኒቨርስቲ መምህራን ኮሌጅ የኹለተኛ ዓመት የእንግሊዝኛ ቋንቋ ተማሪ የነበረው ወጣት፣
በማዕተብ ጉዳይ ከመምህሩ ጋራ ተጋጭቶ የትምህርቱ ውጤት በመበላሸቱ ራሱን አጠፋ፡፡›› የሚል ዜና ዛሬ መጋቢት
2 2009 ዓ.ም በወጣ የአዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ ወጥቶ ተመልክተናል፡፡
ጅማ ዩኒቨርሲቲ
ለኦርዶክሳዊያን ተማሪዎች የእምነት ነጻነታቸውን በመግፈፍ ካሉት ዩኒቨርሲቲዎች ቀዳሚውን ስፍራ ይይዛል በጅማ ዩኒቨርስቲ
የተለያዩ ካምፓሶች ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ የሚገኙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት ተከታይ ተማሪዎች በሥርዐተ
እምነታቸው የተደነገጉ የዐዋጅ አጽማዋትን በመጾም ክርስቲያናዊ ግዴታቸውን ለመወጣት መቸገራቸውንና የትምህርት ተቋማት የአምልኮ፣ የአለባበስና የአመጋገብ መመሪያውን * በአድሏዊነት
በሚያስፈጽሙ ሓላፊዎች ምክንያት በእምነት ነፃነታቸው ላይ የሚደርሰው የመብት ረገጣ በተለያዩ ጊዜያት ለሚመለከታቸው አካላት
አቤት ማለታቸው የሚዘነጋ አይደለም፡፡ ተማሪዎቹም በተለያዩ ጊዜያት ቅ/ሲኖዶስ ሃይማኖታዊ መብታቸውን የሚያስከብር አቋም እንዲወስድ በተደጋጋሚ መጠየቃቸው አይዘነጋም፡፡ ይህ መብት ረገጣ ዛሬ ላይ በመማር ማስተማር ሂደት
ውስጥ ባሉ መምህራን አማካኝነት የእምነቱን መገለጫዎች ተማሪዎች በሚማሩበት ክፍል ውስጥ ‹‹ማዕተብህን አውልቅ›› የሚል ደረጃ ላይ ደርሶ
የአንድ ተማሪ ሕይወት ሊያሳልፍ ችሏል፡፡
በ2006 ዓ.ም ሚኒስር
ሽፈራው ተክለማርያም ሲቪል ሰርቪስ ኮሌጅ በተካሔደውና 800 ያህል መካከለኛ አመራሮች ባሳተፈው ስልጠና ላይ ራሳቸውን በመሸፋፈን የሚመጡ የእስልምና እምነት
ተከታዮች ‹‹በቢሮ ፊታቸውን ተሸፍነው የሚመጡ ሙስሊሞችን አለባበሳቸው ከቦታው አንፃር ያለውን ተገቢነት በማንሣት እንዲያወልቁ ስንጠይቃቸው ‘እኛ ይኼን የምናወልቅ ከኾነ ኦርቶዶክሱም ክሩን ይበጥስ›› በሚል መነሻ ሚኒስትሩ ‹‹ማተቡም ቢኾን የጊዜ ጉዳይ ነው፤ መውለቁ አይቀርም›› የሚል መልስ በመስጠታቸው የጊዜው እጅግ አነጋጋሪ ጉዳይ ሆኖ ማለፉ ይታወሳል ፤ ይህ ጉዳይ
እጅጉን በማሕበራዊ ሚዲያ ላይ ሲገለባበጥ የተመለከቱት የወቅቱ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ሚኒስትር ዴኤታ አቶ እውነቱ ብላታ
ሚኒስትሩ ያሉትን ነገር ለማስተባበል “መንግስት ማዕተብ ማሰርን ለመከልከል የጀመረው አቅጣጫ አለ የሚሉ ወገኖች አሉ። በዚህ
ላይ የመንግስት አቋም ምንድን ነው?” በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ አቶ እውነቱ በሰጡት ምላሽ፣ “በሕገ መንግስት የሰፈረን
የሃይማኖት ነፃነት እና መብትን በምን መልኩ የኢትዮጵያ መንግስት መከልከል ይችላል። በመንግስት በኩል ማዕተብ ማሰር ለመከልከል
ፍላጎቱም ሆነ ይህን የመከልከል ሕጋዊ መሰረት የለውም። በማለት መልስ መስጠታቸው ይታወሳል፡፡ ሚኒስትሩም በወቅቱ ፋና
ብሮድካስቲን ላይ በመቅረብ ቃላቸውን ማስተባበላቸው የሚዘነጋ አይደለም፡፡
በጅማ ዩኒቨርሲቲ በየዓመቱ ከነሐሴ 1 – 16 ቀን በሚቆየው የፍልሰታ ለማርያም መታሰቢያ ጾም ‹‹የጾም ምግብ አይዘጋጅም›› በመባሉ በሥርዓተ እምነታቸው ላይ አድልዎና ጫና ሲደርስባቸው
ነበር፡፡ የፍልሰታ ለማርያም ጾም እና የረመዳን ጾም በአንድ ወቅት በዋለበት በ2005 ዓ.ም. ክረምት፣ ሙስሊም ጿሚ ተማሪዎች ምግብ ከማውጣት ጀምሮ የካፊቴሪያውን ሙሉ አገልግሎት ሲያገኙ፤ ለኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ክርስትና ጿሚ ተማሪዎች በአንጻሩ ተገቢ መስተንግዶ አለመዘጋጀቱ፣ የጾም ሰዓታቸውን ጠብቀው ለመመገብ እንዲችሉ ምግብ ቤቱ ክፍት አለመደረጉና የድርሻቸውን እንዳያወጡ መከልከላቸው፣ ይህንንም ተከትሎ ሥርዓተ እምነታቸው በመመሪያው አግባብ እንዲከበር በዩኒቨርስቲው ቅጽር ሰላማዊ ሰልፍ በማድረግ የጠየቁ ተማሪዎች በፖሊስ መደብደባቸው ይታወሳል፡፡
ይህ የዩኒቨርሲቲው የእግሊዘኛ
መምሕር ተማሪ ተስፋዬ ገመዳ ላይ የሃይማኖት ነጻነቱን ባለማክበር
ያደረሰው የእምነት ረገጣ ኦርቶዶክሳዊ እምነት ተከታዮች እና ቤተክርስቲያኒቱ ላይ የደረሰ መሆኑን ልንገነዘበው ያስፈልጋል፡፡ ቅዱስ
ሲኖዶስ ፤ የዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ ኃላፊዎች ፤ የሚመለከተው የመንግሥት ሚኒስትር መስሪያ ቤት አሁንም ይሁን ወደፊት እንደዚህ አይነት
አመለካከትን ከማጥፋት እና በወረቀት ላይ የሰፈረውን ሕግ እንዲከበርና እንዲተገበር በማድረግ ነገ የእምነቱ ተከታዮች ካለምንም ችግር
ትምህርታቸውን የሚከታተሉበትን መንገድ ማመቻቸት እና መንገድ መጥረግ ይገባቸዋል፡፡
የወልደ ገብርኤልን ነፍስ ከአብርሃም ፤ ከይሳቅ ፤ ከያዕቆብ ጎን ያሳርፍልን፡፡
‹‹ይኼ ማዕተብ የእምነቴ መግለጫ ነው›› ተማሪ ተስፋዬ ገመዳ
No comments:
Post a Comment