Thursday, March 16, 2017

ቅዱስ ሲኖዶስ በቆሼ አካባቢ ሕይወታቸውን ላጡ ወገኖች 7 ቀን የሚቆይ ጸሎተ-ፍትሐት እንደሚደረግ ገለጸ


·        ሼክ መሃመድ አሊ አላሙዲን እና ቤተሰቦቻቸው 40 ሚሊየን ብር ድጋፍ አድርገዋል፡፡

(አንድ አድርገን መጋቢት 7/2009 . ) :- የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ  ቆሼ በተሰኘው አካባቢ መጋቢት 2 ቀን 2009 . ምሽት 130 በደረሰ አደጋ ህይወታቸውን ላጡ ወገኖች ከመጋት 7/2009 .  ጀምሮ ለሰባት ቀናት የሚቆይ ጸሎተ-ፍትሐት በመላው ገዳማት እና አድባራት እንደሚደረግ ገለጸ፡፡ ቅዱስ ሲኖዶስ በአደጋው ለተጎዱና መጠለያ ላጡ ወገኖች የሚውል 200 ሺህ ብር እርዳታ እንዲሰጥ መወሰኗንም አስታውቋል፡፡የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳይ ጠቅላይ ምክር ቤትና የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት እያንዳንዳቸው ለተጎጂዎች የሚውል 100 ሺህ ብር ድጋፍ አድርገዋል፡፡ የሚድሮክ ኢትዮጵያ እህት ኩባንያዎች እና የሚድሮክ ኢትዮጵያ ሊቀ መንበር ሼክ መሃመድ አሊ አላሙዲን እና ቤተሰቦቻቸው  ለተጎዱ ወገኖች የሚውል 40 ሚሊየን ብር ድጋፍ ሲያደርጉ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት በበኩሉኩ የ5 ሚሊየን ብር ድጋፍ ማድረጉን አስታውቋል::

በተጨማሪ ኢትዮ ቴሌኮም ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች የአንድ ሚሊየን ብር ድጋፍ ሲያደርግ የኮተቤ ሜትሮ ፖሊታን ዩኒቨርሲቲ አስተዳደር ሰራተኞችና መምህራን  ለተጎጂ በተሰቦች የ324 ሺህ ድጋፍ አድርገዋል፡፡ እስከ ዛሬ ድረስ የሟቾች ቁጥር 113 የደረሰ ሲሆን በአደጋው ህይወታቸውን ካጡት ውስጥ 38 ወንዶች ሲሆኑ፤ 75 ደግሞ ሴቶች መሆናቸው ታውቋል ፤ የከተማዋ አስተዳደሩ የአስከሬን ፍለጋው ወደ መጠናቀቁ እንደሚገኝ ገልጿል፡፡የከተማ አስተዳደሩ ጉዳት የደረሰባቸው ነዋሪዎቹን በዘላቂነት ለማቋቋም በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝ ከማስታወቁ በተጨማሪ በአደጋው ህይወታቸውን ላጡ ሰዎች የቀብር ማስፈጸሚያ የሚውል የገንዘብ ድጋፍም አድርጓል።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነት ተከታዮች ሕይወታቸውን ያጡ ዜጎች ስርዓተ-ቀብር  የአብዘኞቹ በመከኒሳ  ደብረ አቡነ አረጋዊና ቅዱስ ገብረክርስቶስ ቤተክርስቲያን ተፈጽሟል፡፡ አሁንም ነዋሪዎች እንደሚሉት ያልተገኙ አስከሬኖች እንዳሉ ገልጸዋል ፤ በቦታው ላይ ከአስራ ሰባት በላይ ሕጋዊ ይዞታ ያላቸው ቤተሰቦች ላይ የቆሻሻው ክምር የተጫናቸው ሲሆን ቆሻሻው ላይ በላስቲክ  በመከለል ኑሯቸውን የሚገፉ በርካታ ነዋሪዎች እንዳሉም ተጠቁሟል::
ኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያን  "በደረሰው ሕልፈተ ሕይወት ለተጎዱ ቤተሰቦች እግዚአብሔር አምላክ መጽናናትና ብርታትን እንዲሰጥ፤ የሟቾችንም ነፍስ በመንግስቱ እንዲቀበል ፀሎት ይደረጋል" ብላለች፡፡

No comments:

Post a Comment