Thursday, March 9, 2017

በ1836 ዓ.ም ፡ አንድ ቀን በጎንደር

(አንድ አድርገን : መጋቢት 1 2009 ዓ.ም)
ጠዋት በማለዳ ከየአድባራቱ በሚወጣው መንፈሳዊ ዜማ ጎንደር ከእንቅልፏ ትነቃለች፡፡ የማለዳው ቅዳሴ የሚጀመረው ገና መሬትና ሰማይ ሳይላቀቅ ነው፡፡ በአዘቦት ቀን ፀሎት አጥባቂ የሆኑት ምዕመናንና ነዳያን በሌሊት ተነስተው ወደ አቅራቢያቸው ቤተክርስቲያ መገስገስ ሲጀምሩ የተቀረው ሕዝበ ክርስቲያን ጥቂት ረፈድ አድርጎ ጎኅ ሲቀድ ይደርሳል፡፡ በበዓል ቀን ግን ምዕመና አንድ ቤተክርስቲያን ብቻ ሳይሆን ብዙዎቹን ተሳልመው ይመጣሉ፡፡ በተለይ የአቡነ ተክለሃይማት ተሳላሚ በጣም ብዙ ነው፡፡ ምክንያቱም የተከበረውና የተቀደሰው የእኚኅ ኢትዮጵያዊ ቅዱስ ክብር አርፎበታል ተብሎ ስለሚታመን ሁሉም ወደዚያ ይጎርፋል፡፡
ኢትዮጵያውያን በየሳምንቱ ከሚጾሙት አርብ ሮብ ሌላ በጣም ጥብቅ የሆነ ሥርዓት ያላቸውን አጽማት ለብዙ ወራት ይጾማሉ፡፡ በፆም ጊዜ ቅዳሴ የሚገባው ከሰዓት በኋላ ወደ ስምንትና ዘጠኝ ሰዓት ገደማ ነው፡፡ ከቅዳሴው ሲወጡ ምሳና ራታቸውን በአንድ ላይ አንድ ጊዜ ይመገባሉ፡፡ ከዚህ ውጪ ምንም ነገር አይቀምሱም፡፡

ሰዓት መቁጠሪያ የላቸውም፡፡ ነገሩን በማቃለል የጸሐዩዋን አካሄድ በሰማይ ላይ በመከተል ቀኑን ስድስት ቦታ ይከፍሉታል፡፡ ቄሶችና አንዳንድ የተማሩ ሰዎች ትንሽ ሻል ያለ ዘዴ ይጠቀማሉ፡፡ ጀርባቸውን ለፀሐይ ይሰጡና መሬት ላይ የሚያርፈውን የጥላቸውን ርዝመት በእርምጃቸው እየለኩ ግማሽ እርምጃ ፤ አንድ እርምጃ እያሉ ይቆጥራሉ፡፡ ለምሳሌ በቀኑ ውስጥ የሚጾሙበት ሰዓት ጥላው ይህን ያህል እርምጃ ሲሄድ ወይም ጥላው ጋር ሲደርስ ብለው ይወስናሉ ፡፡ አንዳንዴ የቆጠሩት እርምጃ ጥላውን ሲከተል ከቅዳሴ የሚወጡበት ጊዜ እስከ ፀሐይ መጥለቂያ ሰዓት ድረስ ሊሄድ ይችላል፡፡ እስከዛ እህል የሚቀምስ የለም፡፡
ጠዋት ጠዋት ጎንደር በእንቅስቃሴ ትሞላለች፡፡ ሮብና አርብ ቤተክርስቲያቹ ክፍት ሆነው ስለሚውሉ አሮጊቶች ፤ ወታደሮች ፤ አላፊ መንገደኞች ፤ በጸጥታ ጸሎት ሲያደርሱ ሌሎች በቤተ ክርስቲያኑ አፀድ በሚገኙ የዛፍ ጥላዎች ስር አረፍ ብለው በለሆሳስ ሲወያዩ ይታያሉ፡፡ ከጠዋት ወደ ሁለት ሰዓት ላይ የከተማው ነዋሪዎች አጼው  ፤ አቡኑ ፤ እጨጌው ፤ ነጋድረሱ ፤ከንቲባው አንዳዴም የሀገር ሽግሌዎች ወደሚያስችሉባቸው ችሎቶች ይጎርፋሉ፡፡ ለዚሀ ጉዳይ ሆን ብለው የተሰሩ አዳራሾች ስለሌሉ አብዛኛውን  ጊዜ ችሎት የሚውለው ሰፋ ያለ ሜዳ ተፈልጎ እዚያ ላይ ነው፡፡ ዳኞች ጥላ ተይዞላቸው ይሰየሙና ሕዝቡ ዙሪያውን ተቀምጦ ክርክሩን ያዳምጣል፡፡
ቀኑ እየተገባደደ ሲሄድ መነኮሳት ፀሎታቸውን በለሆሳስ ሲያነበንቡ ፤ የቆሎ ተማሪዎች የኔቢጤዎችና አካለ ስንኩላን ከቤት ቤት እየዞሩ ዕለተ ቀኑ የሆነውን መልአክ ስም በመጥራት ቁራሽ ሲለምኑ ይታያሉ፡፡ የመድኃኔዓለም ፤ የአቡነ ተክሃይማኖትና የድንግል ማርያም ሰም በተደጋጋሚ ይጠራል፡፡ ነጫጭ ሻሻቸውን ለብሰው የጠመጠሙ ቀሳውስት ፤ ፀሎታቸውን በቃላቸው ጮክ ብለው እየደገሙ የሚጓዙ ደብተሮች ፤ ከየትምህርት ቤታቸው ተለቀው እየተንጫጩ የሚሄዱ ሕጻናት እነዚህ ሁሉ ጎንደርን ጎንደር የሚያሰኟት እሴቶቿ ናቸው፡፡
ከቀኑ አሥራ አንድ ወይም አሥራ ሁለት ሰዓት ግድም የቤተክርስቲያች ደውሎች ይደወላሉ፡፡ ከየአድባራቱ የሚሰማው ደውል አየሩን እየሰነጠቀ ሲያቃጭል ቅዳሴ አልቆ ጦም ያበቃ መሆኑን ያበስራል፡፡ ከዚያ በኋላ ሁሉም በየቤቱ ይከተታል፡፡ መንገዶች ጭር ይላሉ፡፡ ያን ጊዜ ብቻ እህል ወደ አፍ የሚደረገው፡፡
ፀሐይቱ ጠልቃ ከተማይቱ ረጭ ስት ጨለማን ተገን አድርገው ለስርቆት ከሚሰማሩ ሌቦች በቀር ማንም ደጅ አይቀርም፡፡ ሌሊቱ ሲገፋ ጅቦች ከተማዋን ይረከባሉ፡፡ ለሊቱን ከእንቅልፉ የነቃ የጎንደር ነዋሪአውሬዎቹ በቀፋፊ ጩኽታቸው የለሊቱን ጸጥታ ሲያደፈርሱ እና ሳቃቸውን በመልቀቅ ሲያሽካኩ ሊሰማቸው ይችላል፡፡
‹‹በኢትዮጵያ ከፍተኛ ተራሮች ቆይታዬ› መጽሐፍ የተወሰደ
ደራሲ ፡ አርኖ ሚሼል ዳባዱ
ተርጓሚ ፡- ገነት አየለ አንበሴ
ገጽ 119-131 


ለረዥም ወራት መረጃ ማስተላለፍ ያቆምንበት ምክንያት እንዳለ ሆኖ በቅርብ ጊዜ እንመለሳለን 

No comments:

Post a Comment