Wednesday, April 23, 2014

ባለፉት 40 ዓመታት ለቤተክርስቲያን ‹‹ዘመነ ደርግ ረመጥ ፤ ዘመነ ኢሕአዴግ ዳጥ ››


·        በዘመነ ደርግ ሲኖዶስ እንዲበተን ተደርጓል ፤ መስቀል ለጨረታ ቀርቧል ፤ ፓትርያርኩ የሕይወት መስዋዕትነትን ስለ እምነታቸው ተቀብለዋል ፤ አብያተክርስቲያናት ተዘግተዋል ፤ የምዕመናን መንፈሳዊ ሕይወት ፈተና ላይ ወድቋል ፤  ……

(አንድ አድርገን ሚያዚያ 16 ፤ 2004 ዓ.ም )፡- የኢትዮጵያ ቤተ ክርስትያን ክብር ባህል እምነትና ስርዓት መንግሥትና ቋንቋ ያቋቋመች የማትናወጥ ከመሆኗ ጋር ከሔኖክ ፤ ከኖህ ፤ ከመልከ ጼዴቅ ከነብያትና ከሀዋርያት ተላለፈውን ትምህርት ስርዓት ፤ እምነት ከትውልድ ወደ ትውልድ ስታስተላልፍ የኖረች በማስተላለፍ ላይ ያለች ፎኖተ ህይወት መሆኗ የተረጋጠ ነው፡፡ ቅዱሳን አበውን ፤ ኃያላን ነገስታትን ፤ ልዑላን መሳፍንትን ፤ ክቡራን መኳንንትን ፤ ዐይናሞች ሊቃውንትን በስጋ በነፍስ ወልዳ ያሳደገች ፤ የሌላ የማትፈልግ የራሷ የማትለቅ ዕጥፍ እናት ፤ ስንዱ እመቤት ናት፡፡(አለቃ አያሌው ታምሩ)

በቅዱስ መጽሐፍ ስለ ቅድስናዋ እግዚአብሔር ደጋግሞ የመሰከረላት አገራችን ኢትዮጵያም ቅድስት ክብርት ሐገር ናት ፡፡ ሰይጣን በእባብ አድሮ አዳምንና ሔዋንን እንደተዋጋቸው ሁሉ በልዩ ልዩ ሥጋውያንና መንፈሳውያን የውጭ ጠላቶች አድሮ ኢትዮጵያን ሲዋጋ ኖሯል፡፡  ዛሬም በመዋጋት ላይ ነው ፡፡ ነገር ግን የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ትጥቋን አጥብቃ ከቆመች ሳታርፍ ፤ ከዘረጋች ሳታጥፍ በኖረችበት ዘመን ሁሉ ኢትዮጵያ ሳትደፈር ኖራለች፡፡ በ10ኛው መቶ ዓመት የጉዲት ወረራ ፤ የ16ኛው መቶ ዓመት የግራኝ ወረራ ፤ ከ17ኛው እስከ 20ኛው መቶ ዓመት ተደጋግሞ የደረሰው የካቶሊክ ፤ የፕሮቴስታንት ፤ የቱርክና የግብጽ እስላማዊ ወረራ ተደጋግሞ የከሸፈው ባልተበረዘውና ባልተከለሰው የኢትዮጵያ  ቤተ ክርስቲያን  የእምነት ኃይል ነው፡፡ የአምስት ዓመት የፋሽስት ወረራም ጉዳት ማድረሱ የታወቀ ቢሆንም ከስሩ የተነቀለው ፤ ቁጥቋጦው የተመለመለ ፤ እንደ አንበጣ በዝቶ የመጣው የፋሽስት ሰራዊትም የውሀ ሽታ ሆኖ የቀረው በኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን የእምነት ኃይልና በልጆቿ ደም ነው፡፡


ዛሬ ሁሉ ባለ ሀገር ነኝ በማለት ለአገሪቱ ባለ ውለታ መስሎ ይታይ እንጂ ለ3000 ዓመታት ለኢትዮጵያ ቆማ የኖረች የሰላም ፋና የኢትዮጵያ ቤተክርስትያን ብቻ ናት፡፡ የነብያት ፤ የሐዋርያት እምነት ከተሰበከበት ጊዜ ጀምሮ በሐዋርያት ዘመንም ሆነ በተከታታዩ ዘመን በውጭ የታየውና የተነገረው የመናፍቃን ትምህርትና ግብር በኢትዮጵያ የታየበት ጊዜ የለም፡፡ ይልቁንም በ444 ዓመተ ምህረት በኬሌቄዶን በተደረገው ጉባኤ ምክንያት በውግዘት መለያየት ከተደረገ ወዲህ ኢትዮጵያ ቤተክርስትያን ከሮምና ከቁስጥንጥንያ ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት ሳታደርግ እስከ 20ኛው ክፍለ ዘመን ኖራለች፡፡

በዚህ ዘመን ሁሉ የአበው ስርዓት ሳይፈርስ ፤ ህጉም ውግዘቱም ሳይጣስ ተጠብቆ ኖሯል ፡፡ ልዩ ልዩ የሃይማት ተከታዮች የመንግስት መልዕክተኞች እየሆኑ ጠብ እየቀሰቀሱ ፤ ጦርነት እያስነሱ ቢፈታተኗም የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን አበው ግን በመስቀልና በሰንደቅ አላማቸው ስር ሆነው ደማቸውን ሲያፈሱ ኖሩ እንጂ የመላላት ግንባር አላሳዩም፡፡ ከዚህም የተነሳ በ1928 ዓ.ም የዘመተው የፋሺስት ሰራዊት ኢትዮጵያን ሲዋጋ ስንቅና ትጥቁን አዘጋጅታ ባርካ ያዘመተችው የልዮን መንበር ስትሆን በዚህም ጦርነት ሁለቱ ታላላቅ አባቶች አቡነ ጴጥሮስና አቡነ ሚካኤል ሰማዕትነትን ሲቀበሉ ፤ በደብረ ሊባኖስ ፤ በዝቋላ ፤ በዲማ ፤በዋሸራና በሌሎች አብያተ ክርስትያን ብዙ ካህናትና ምዕመናን መስዋዕት ሆነዋል ፡፡ ይህም በጦር ሜዳና በአምስት ዓመት ሙሉ በየአቅጣጫው ከተደረገው ጦርነት ሌላ ነው፡፡

ይህ የቀደመ ታሪክ ነው ፤ ከ1967 ዓ.ም እስከ 1983 ዓ.ም ድረስ በዘመነ ደርግ ብዙ ጠባሳ በሀገሪቱ ላይ ቀጥሎም በቤተክርስቲያን ላይ አሳልፎ አልፏል፡፡በደርግ ሰዓት ህዝቡም ከባድ ቀንበር ተሸክሟል መከራም ደርሶበታል ፤ ቤተክርስትያን ላይ የደረሰው ፈተና ግን ከባድ ነው፡፡ አሁን ያለውን የቤተክርስቲያኒቱን ፈተና ከቀድሞው ጋር ሲነጻጸር ምን እንደሚመስ ለማረዳት ያስችል ዘንዳ ከደረሱት መከራዎች በጥቂቱ እኒህን ይመስሉ ነበር፡፡
·        ሁለተኛው ፓትርያርክ አቡነ ቴዎፍሎስ በውጭ ጠላቶች ቀስቃሽነት ፤ በቤተክርስትያን አንዳንድ አባሎች ተባባሪነት ከመንበር ወርደው ተገደለዋል፡፡
·        ቤተክርስያንቲቱ ለዘመናት ለሃገር አንድት የከፈለችው መስዋዕትነት ተረስቶ ያሏትን አብያክርስቲያት በመዝጋት ተተኪ ዲቆናት ፤ ቀሳውስትና አባቶች እንዳይኖሩ ያላትን የሰው ኃይል ወደ ወታደራዊ ኃይል በመቀየር ባሏት አገልጋዮች ብቻ እየተገለገለች እንድዘልቅ ተደርጓል፡፡ ዘመኑ እምነትንና ስብከተ ወንጌልን ለማስፋፋትም ሆነ ያሉትን ክርስቲያኖች በዕምነታቸው ጸንተው ዘመኑን እንዲዘልቁ ለማድረግ እጅግ አስቸጋሪ ነበር፡፡
·        በመሀመድ ጋዳፊና በሊቢያ ጉባኤ ድጋፍ ‹‹ሃይማኖት አይለያየንም›› በሚል ቤተክርስቲያንን ከጉልላቷ ከመስቀል ለይቶ ባዶ ራስ አድርጎ ከእስላም መስኪድ አገናኝቶ የተሳለ ምልክት ያለበት ወንጌልን የሚነቅፍና ቁራን የሚያቅፍ መጽሀፍ በቤተክርስትያን ታትሞ ተበተነ፡፡ በወቅቱ የኮሚኒስት ማኒፌስቶ ለመጀመሪያ ጊዜ በቤተክርስትያን ማተሚያ ቤት ታትሞ የተበተነ ሲሆን በዚሁ መሰረትነት የቤተክርስትያ ስብከት ፤ ወንጌልና ሶሻሊዝም አንድ ነው ፤ የኮሚኒስ ሥርዓት የሐዋርያት ስርዓት ነው በሚል መስመር  አሁን ላይ ካድሬዎች በምንላቸው የወቅቱን ስርዓት በተጠመቁ ሰዎች አማካኝነት ተስፋፋ፡፡
·        በ1970 ዓ.ም መጨረሻ ላይ ‹‹ከሀገር ወዲያ ሀይማት የለም›› በሚል አርእስትና ‹‹ብቸኛው ፓትርያርክ›› በሚል አርእስት ለኢትዮጵያ በአብዮቱ የተጠመቁ ጳጳሳት ያስፈልጓታል በሚል አስተያየት የያዘ ‹‹ዜና ቤተክርስትያን›› በተከታታይ ከታተመ በኋላ ፤ ጥቅምት 14 ቀን 1971 ዓ.ም የአዲስ አበባ አድባራና ገዳማት አስዳሪዎች ፤ ቀሳውስትና ዲያቆናት ፤ መዘምራንና ማህበረ ምእመና ፤ በጊዜው የነበሩት ሶስተኛው ፓትርያርክ በተገኙበት ‹‹ አሮጊይቱ ቤተክርስትያን ትውደም ! አሮጌ ሲኖዶስ ይውደም ! ሲኖዶስ ቅዱስ አይባልም !›› በሚል መፈክር በስብከተ ወንጌል አዳራሽ ከተሰማ በኋላ የፊተኞቹ አበው ጳጳሳት በጡረታ ተገለው ሲኖዶስ ፈረሰ፡፡ ጥር 13 ቀን 1973 ዓ.ም አዲስ ሲኖዶስ ተመሰረተ፡፡
·        ቤተክርስትያኒቱ ለኮሚኒስት ስርዓት የጀርባ አጥንት ሆና ከመገኝቷ የተነሳ እንኳን መዘምራኑ ፤ ዲያቆናቱ ፤ ቀሳውስቱና መነኮሳቱ ሳይቀሩ የቀበሌ ሊቃነ መናብርት  ፤ አብዮት ጥበቃ ሰራዊት ፤ የሸንጎ አባል በመሆን የክርስቶስንና የሰውን ደም አንድ ላይ ሲቀዱ ኖረዋል ፡፡ በጠቅላይ  ቤተክህነት የኮሚኒስቶች ድርጅት ተቋቁሞ ሲያራምደው የኖረው ሥርአት በመኢሰማ ሊቀ መንበርነት በ1970 ዓ.ም በኮሚኒስት ሰንደቅ አላማ የቤተክህነት ግቢ አስጊጦ ደም ለማፍሰስ ተዘጋጅቶ የነበረው የአመጻ ዝግጅት እግዚአብሔር ባያበርደው ኖሮ ውጤቱ አሳዛኝ በሆነ ነበር፡፡ ነገር ግን ያን ኃያል እግዚአብሔር ባወቀ ስለ ሻረው ብዙዎች ቢጨፈጨፉም ስር ሳይሰድ ተነቅሎ ቀርቷል፡፡ ለዚያ የአመጽ መንግስት የቤተ ክርስቲያን አባሎች ባደረጉት ድጋፍ መስቀል ለጨረታ ቀርቧል ፡፡ በእናት ሀገር ጥሪ ምክንያት ጾም ተሽሮ ስጋ እንዲበላ ሲደረግ  የቤተክርስትያኒቱ መሪዎችም እየባረኩ በልተዋል፡፡ ‹‹በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ›› በማለት ፈንታ ‹‹በስመ ሌሊን ወማርክስ ወኤግልስ›› ብንል ምናለበት ? ይቤ ማቴዎስ ፤ ይቤ ማርቆስ የሚባል ከሆነ ይቤ ሌኒን ማርክስ ፤ ይቤ ኤንግልስ ብንል ምናለበት  በማለት ሁሉም ነገሮች በስላቅ ተከናውነዋል፡፡
·        በከፍተኛ የቤተ ክርስትያኒቱ አባላት ሳይቀር የኮሚኒስት ደብተር የተያዘበት ጊዜም ነበር፡፡ በተደጋጋሚ ጊዜ ከልዩ ልዩ ሀይማኖቶች ክፍሎች ጋር በአፍሪቃ አዳራሽ ስለ እምነት አላስፈላጊነት ሳይቀር የአንድነት ስብሰባ የተደረገበት ጊዜ ነበር፡፡
·        ኢትዮጵያ ጠብቃው የኖረችውትምህርተ ሃይማኖት በአበው ተጠብቆ የኖረውን ያህል ፤ ቃሉ ተለውጦ  እምነቱ ተናውጦ  መሰረቱ ፈርሶ በኑፋቄ ጠባይ ተዘጋጅቶ የቀረበው መጽሐፍ ቅዱስ‹‹በሲኖዶስ ታይቶ ተመርምሮ ተፈቅዷል››  የሚል መግለጫ ይዞ ወጥቶ ነበር፡፡ በዚህ ጊዜ ስለ ቤታቸው የተቆረቆሩ ሁሉ አቤት ባዮች አልጠፉም ነበር ፡፡ በተለይም የሊቃውንት ጉባኤ የተደጋገመ አቤቱታውን አቅርቧል፡፡ ግን ሰሚ አላገኝም ፡፡ ከዚህም ጋር ‹‹ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን መሰረተ እምነት›› ፤ ‹‹ ትምህርት መለኮት››፤ ‹‹የዋልድባ ታሪክ›› በሚሉ ስሞች የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያንን ትምህርት የሚቃረኑ መጻህፍት ታትመው ተበትነዋል፡፡ እነዚህም መጻህፍት ፤ ‹‹እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የውርስ ኃጥያት አለባት ›› ፤ ‹‹መንፈስ ቅዱስ አካሉ ዝውር ነው ፤ መለኮት በአካል ሶስት ነው፤›› የሚል ትምህርት የተሰራጨባቸው ጊዜያት ነበሩ፡፡

በዘመኑ የነበሩ የመንግሥት ባለስልጣናት ቤተሰቦቻቸውንም ይሁን ራሳቸውን በቤተክርስቲያን በሚደረጉ አገልግሎቶች እንደ ምዕመን ማሳተፍ መቻል ለከፋ አደጋ የሚያጋልጥበት ወቅት ነበር፡፡ ቤተ ክርስቲያን በዘመኑ የማታስፈልግ አድርገው ከማሰብም በተጨማሪ ከአሁኑ ስርዓት የባሰ የነፍጠኞች የአድሀሪዎች መሰብሰቢያ አድርጎ የመመልከት ችግርም ነበር፡፡ የአሁኖቹ ባለስልጣናት ቤተ ክርስቲያኒቱ ላይ ቀድሞ ከተሸከመችው የ17 ዓመት ቀንበር የሚያንስ አሸክመዋት ቢገኙም ዘረኝነት ፤ ጎጥ እና ጠባብነትን መሰረት ባደረገ መልኩ አዳዲስ ፈተናዎች ባሳለፍናቸው 20 ዓመታት እንድናሳልፍ አስገድደውናል፡፡  እንደ እኛ እምነት  አሁንም ቢሆን ቤተ ክርስቲያን ፈተና ላይ ብትሆንም ከቀድሞ ጋር ግን የሚነጻጸር ሆኖ አናገኝውም፡፡

በልጁ ቆዳ የሚቀበር ምዕመን ስለማይኖር እኛም የዘመኑን ልዩነት እና የፈተናው ክብደትና ቅለት በማስተዋል ቤተ ክርስቲያኒቱ ላይ ለሚደርስ ማንኛውም ቀንበር የምንሸከምበትን ትከሻ ልናደላድል ደስታውንና በዓሉን ብቻ ሳይሆን መከራዋንና ፈተናዋን አብረን ልናሳልፍ ይገባል፡፡ትልቁ ተስፋችን እግዚአብሔር አምላክ ቢሆንም በየዘመኑ ለሚነሱ ፈተናዎች  ምዕመኑ እንደ ምዕመንነቱ ፤ ከላይ እስከ ታች ያሉት አገልጋዮች እንደ ተሰጣቸው ሃላፊነትና ሥልጣን  ፈተናዎችን ከመመከት አንጻር ሁሉም የራሱን ሃላፊነት መወጣት መቻል አለበት፡፡ ባለፉት 40 ዓመታት ዘመነ ደርግ ረመጣችን ቢሆንም ፤ በዘመነ ኢሕአዴግ የምዕመኑ ቁጥር ቢቀንስ እንኳን ከዘመነ ደርግ በተሻለ ስለ እምነቱ የሚያውቅ ምዕመን ስለተፈጠረ ከዳጥነት አያልፍም የሚል እምነት አለን፡፡


ያለንበትን ፈተና እየኖርንበት ስለሆነ የአሁን ፈተናችን ለናንተው መንገር ለቀባሪው ማርዳት ነው የሚሆነው ...

ቸር ሰንብቱ



1 comment:

  1. በልጁ ቆዳ የሚቀበር ምዕመን ስለማይኖር እኛም የዘመኑን ልዩነት እና የፈተናው ክብደትና ቅለት በማስተዋል ቤተ ክርስቲያኒቱ ላይ ለሚደርስ ማንኛውም ቀንበር የምንሸከምበትን ትከሻ ልናደላድል ደስታውንና በዓሉን ብቻ ሳይሆን መከራዋንና ፈተናዋን አብረን ልናሳልፍ ይገባል፡፡ትልቁ ተስፋችን እግዚአብሔር አምላክ ቢሆንም በየዘመኑ ለሚነሱ ፈተናዎች  ምዕመኑ እንደ ምዕመንነቱ ፤ ከላይ እስከ ታች ያሉት አገልጋዮች እንደ ተሰጣቸው ሃላፊነትና ሥልጣን  ፈተናዎችን ከመመከት አንጻር ሁሉም የራሱን ሃላፊነት መወጣት መ

    መቻል አለበት፡፡ ባለፉት 40 ዓመታት ዘመነ ደርግ ረመጣችን ቢሆንም ፤ በዘመነ ኢሕአዴግ የምዕመኑ ቁጥር ቢቀንስ እንኳን ከዘመነ ደርግ በተሻለ ስለ እምነቱ የሚያውቅ ምዕመን ስለተፈጠረ ከዳጥነት አያልፍም የሚል እምነት አለን፡፡



    ያለንበትን ፈተና እየኖርንበት ስለሆነ የአሁን ፈተናችን ለናንተው መንገር ለቀባሪው ማርዳት ነው የሚሆነው 

    ReplyDelete