Sunday, March 30, 2014

ከቤተ ክርስቲያኒቱ እምነትና ሥርዐት ውጪ ነው የተባለ አስተምህሮ አሳሳቢ መሆኑ ተነገረ


(ዕንቊ መጋቢት 2006 ዓ.ም.) የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንን አስተምህሮ በዘመናዊ አቀራረብ ከሚሰጡት ሦስት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አንዱና አንጋፋ በኾነው የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ፣ ከቤተ ክርስቲያኒቱ ቀኖናና ትውፊት ውጭ ነው የተባለ አስተምህሮ እንደ ሰደድ እሳት እየተቀጣጠለ ተማሪውን የርስ በርስ ግጭት ውስጥ ወደሚያስገባ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን የኮሌጁ ምንጮች አስታወቁ፡፡
 
በቅ/ሲኖዶሱ በይፋ ከተወገዙና በኑፋቄ አራማጅነት ከሚጠረጠሩ ግለሰቦችና ቡድኖች ጋራ ግንኙነት እንዳላቸውና በኅቡእ በሚንቀሳቀሱ ተማሪዎች የሚራመድ ነው የተባለው አስተምህሮ ፣ በአስተዳደሩ ተመርምሮ አልያም በመድረክ ተጋልጦ እልባት እንዲሰጠው የደቀ መዛሙርቱ ም/ቤት በጥር ወር መጀመሪያ ላይ ለኮሌጁ አስተዳደር ጥያቄ ቢያቀርብም ምላሽ ሳይሰጠው መቅረቱን የኮሌጁ ምንጮች ለዕንቊ መጽሔት ተናግረዋል፡፡

 
የም/ቤቱ አባላት ኮሌጁንና ደቀ መዛሙርቱን ለማገልገል በደቀ መዛሙርቱ ጠቅላላ ጉባኤ መመረጣቸውን ያስታወሱት ምንጮቹ ፣ አገልግሎታቸውን በቅንነትና በትጋት እንዲፈጽሙ ከፍተኛ ሓላፊነት ከተጣለባቸው አንዳንዶቹ ሃይማኖትን ለማጽናትና ለማስፋፋት ቤተ ክርስቲያኒቱ በጀት መድባ አገልጋዮቿን በምታስተምርበት ተቋም ከአስተምህሮዋ ውጭ ኑፋቄ ሲዘራ ድምፀ ተዓቅቦ በማድረግ የጋራ አቋም እንዳይደረስበት ይሠራሉ ብለዋል፤ ለእምነታቸውና ሥርዓታቸው የሚቆረቆሩ መምህራንና ተማሪዎችን ‹ማኅበረ ቅዱሳን›ና ‹ፖሊቲከኞች› እያሉ በተለያዩ ስልቶች በማሸማቀቅ ከሚታወቁት ችግር ፈጣሪ ደቀ መዛሙርት ጎን ተሰልፈው የሚፈጽሟቸው ተግባራትም እንዳሳሰባቸው ምንጮቹ አስረድተዋል፡፡
 
ለኮሌጁ አስተዳደር ዲን ከሁለት ወራት በፊት የገባው ደብዳቤ ምላሽ ሳይሰጠው በመዘግየቱና የችግሩ አያያዝ በም/ቤቱ አባላት መካከል ሳይቀር የአቋም ልዩነት በመፍጠሩ ይህንኑ የሚያስረዳ ሌላ ደብዳቤ በዚሁ ሳምንት በኹለት የም/ቤቱ አባላት ለዋና ዲኑ ጽ/ቤት መቅረቡ ተጠቁሟል፡፡
 
‹‹ችግሩን በዝምታ ለመመልከት ኅሊናችም ሃይማኖታችንም አይፈቅድልንም›› ማለታቸው የተጠቀሰው እኒህ የም/ቤት አባላት፣ በአቋም ተለይተናቸዋል ያሏቸው የም/ቤቱ አባላት ከእንግዲህ በም/ቤቱ ስም ለሚያስተላልፉት ማንኛውም ውሳኔ ሓላፊነት እንደማይወስዱ፣ ከልማቱ ይልቅ ጥፋቱ አመዝኗል ያሉት ም/ቤትም ታግዶ ጉዳዩ እንዲጣራ፣ እምነታቸውና ሥነ ምግባራቸው በተመሰከረላቸው ደቀ መዛሙርትም እንዲተካ መጠየቃቸው ታውቋል፡፡

1 comment:

  1. Men collegu bicha awode-mihretum eko yenesu mecheferya honwal
    Andand halafinet yalebachewo abatoch ena papasatim le batechristyan tilik agelgilot eyesete yalewon mehabere kidusan lemaskom defa kena eyalu yigengaly silezi yiha guday bachiru kaltemwache bizu tifatoch yidersalu
    Bicha Egziyabher amlak le abatochachin lib yistlin

    ReplyDelete