ከታምራት ፍሰሃ
(አንድ
አድርገን መጋቢት 23 2006 ዓ.ም)፡- በአገር አቀፍ ደረጃ የከፍተኛ ተቋም ተማሪዎችን አሰባስቦ ስላስተማረ ፡ ብዛት ያላቸውን በግእዝ የተፃፉ መፃህፍትን ተርጉሞ ለወጣቱ የሚጠቅሙና የሚያንፁ መፃህፍትን አሳትሞ ስላቀረበ ፤ እጅግ የበዙ ገዳማትንና አድባራትን ስለረዳ ፤ የአብነት ተማሪዎችና መምህራንን ራሳቸውን እንዲችሉ እጅግ ብዙ ፕሮጀክቶችን ቀርፆ በተግባር ስላዋለ ፤ የፈረሱ አብያተ ክርስቲያናትን ስላሳነፀ ፤ ብዙ ሺህ ኢአማንያንን በፈቃዳቸው አስተምሮ እንዲጠመቁ ስላስተባበረ ፤ የካህናት ማሰልጠኛዎች በየቦታው እንዲቋቋሙ ስላስተባበረ ፤ አፅራረ ቤተ ክርስቲያንን ነቅቶ ስለጠበቀ ፤ የመናፍቃንን አላማ ግልፅ ስላደረገ ፤ ቤተ ክርስቲያንን ከተሃድሶዎች ስለተከላከለ ፤ የክርስቶስን ወንጌል በየገጠሪቷ ክፍል እየዞረ ስላስተላለፈ ፤ ወጣቶች በነፃ ያለምንም ክፍያ ቤተክርስቲያንን እንዲያገለግሉ አርአያ ስለሆነና
ስላስቻለ ፤ በጣም ርቀው የነበሩ ክርስቲያኖችን አቅርቦ ለቤተክርስቲያን በሙያቸው እንዲያገለግሉ ያስላስተባበረ ማኅበር አክራሪ ከተባለ እንግዲህ እኔም አክራሪ ልባል እወዳለሁ!!!በከፍተኛ ትምህርት
ተቋማት ተማሪዎች ላይ በማተኮር የተማረው ትውልድ ሃይማኖቱን የሚወድ፣ ግብረ ገብነት ያለው፣ ሀገሩንና ቤተ ክርስቲያኑን በዕውቀቱ፣
በሞያውና በገንዘቡ የሚያገለግል ብቁ ዜጋ ይኾን ዘንድ በቅዱስ ሲኖዶስ ጸድቆ በተሰጠው መተዳደርያ ደንብ መሠረት በመሥራት ላይ ያለ ተቋም
አክራሪ ከተባለ እኔም አክራሪ ልባል እወዳለሁ ፡፡
ከሙስና መራቅ ፤ ሃገርን መውደድ ፤ ቤተ ክርስቲያንን ማወቅ ፤ ክርስቶስን ማምለክ አክራሪ ካስባለ እኔም አክራሪ ተብየ እንድከሰስ እወዳለሁ!!! እንዲህ ያለ አክራሪነቴን እወደዋለሁ!!! የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ክርስቶስ መሰረቷ ነው ፡ ድንግል ማርያምም ክብሯ ናት ማለት አክራሪ ካስባለ ፤ አክራሪ ተብሎ መሞት ክብር ነው!!! ክርስቶስን በካደ ትውልድ መካከል በዲያቢሎስ በምትደምቅ አለም ለመዋብ በሚቋምጥ ሰው መካከል እውነት ውሸት መስላ መወቀሷ ፡ ውሽትና ክፋትም ከሚሰሯት ጋር መከበሯ የሚጠበቅ ነው፡፡ ዲያቢሎስ የተጣባት ክርስቶስ የራቃት ህሊና ፦ የገደላትን እየሾመች የሞተላትን መጥላቷ የሚጠበቅ ነው፡፡ ነገር ግን ፦ እኛ ከዚህ ህብረት አለመሆናችን ይታወቅ ዘንድ : አንድም እውነት ስለሆነው ስለ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ምስክርነት ከእውነት ጎን እንቆማለን፡፡ “ሲነቅፉአችሁና ሲያሳድዱአችሁ በእኔም ምክንያት ክፉውን ሁሉ በውሸት ሲናገሩባችሁ ብፁዓን ናችሁ።”ማቴ 5፡11