Friday, February 21, 2014

ታጣቂ ፖሊስ የቤተ ክርስቲያን ቅጽር ውስጥ የሚገባው እስከ መቼ ነው?


  •  የሰበካ ጉባኤ ምርጫ ሲከናወን መስቀል ይዘው የሚመጡ ብጹአን አባቶች ትተው ፓትሮል ሙሉ መሳሪያ የታጠቁ ፖሊሶች  የሚጋብዙም የቤተክርስቲያን አስተዳደሮችን ተመልክተናል፡፡



(አንድ አድርን የካቲት 15 2006 ዓ.ም)፡- በአሁኑ ሰዓት በአዲስ አበባ ውስጥ ካሉት አብያተክርስቲያናት ውስጥ አስተዳደራዊ በደሎች እየበረከቱ ይገኛል፡፡ ማኅደረ ስብሐትልደታ ለማርያምና ደብረ መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ፤ በተለምዶ አዲሱ ሚካኤል እና ግቢ ገብርኤል እና መሰል አብያተ ክርስቲያናት ስማቸው ከአስዳደራዊ በደል ጋር በየጊዜው ሲነሳ ይሰማል፡፡ በአሁኑ ወቅት በአስተዳደር በደል እና መሰል ጥያቄዎች ጋር አጉስታ ጽዮን ማርያም ቤተክርስቲያን ስሟ እየተነሳ በየጊዜውም ሁከት እየተፈጠረ ይገኛል፡፡ በቦታው በአሁኑ ሰዓት እጅግ በጣም ትልቅ እና ዘመን ተሻጋሪ ሕንጻ ቤተክርስቲያን እየተገነባ ይገኛል፡፡ ቦታው ላይ ያለ ምዕመንም ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይል ገንዘብ ያለው በገዘቡ ገንዘብ የሌለው በጉልበቱ ሕንጻ ቤተክርስቲያኑ እንዲያልቅ የበኩሉን አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል ፤ በሳምንት አንድ ጊዜ በእለተ ሰንበት ከምዕመኑ ለሕንጻው ማሰሪያ የሚሆን ቢያንስ ከ15ሺህ ብር ያላነሰ  በአውደ ምህረት ላይ ይሰበሰብ ነበር፡፡ ቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ በዋነኝነት የቅድስት ማርያም ታቦት ሲኖር በተጨማሪ ደግሞ የቅዱስ ኡራኤልና የመጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሀንስ ታቦቶች ይገኛሉ፡፡ በዚህ ቦታ ላይ በዓላት ሲከበሩ እጅግ ብዙ ብር ሲሰበሰብ በጆሯን ሰምተናል በአይናችን አይተናል፡፡ ነገር ግን የሚሰበሰበው ብር መዳረሻ በአሁኑ ወቅት ሕንጻው የሚገኝበት ሁኔታ እና በቦታው ላይ አለ ስለሚባለው አስተዳደራዊ ችግር ምዕመኑን ጥያቄ እንዲያነሳ አስገድዶታል፡፡



ከወራት በፊት ሐምሌ 2005 ዓ.ም የአካባቢው ወጣቶች ፤ አንዳንድ ምዕመናንና የውስጥ አገልጋይ ካህናት አሉ የተባሉትን ችግሮች በማንሳት ተወያይተው ነበር ፤ በወቅቱ የተነሱት ችግሮች ፤ ሕገ ወጥ ቅጥር ፤ ማንበብና መጻፍ የማይችሉ ገንዘብ ቆጣሪዎች(አገልግሎታቸውን ብቻ በማየት ለማጭበርበር እንዲመች ከተቆጠረው ገንዘብ በታች ለማስፈረም እንዲመች የሚል ክስ) ፤ ከሙዳይ ምጽዋት የሚገኝን ገንዘብ በሁለት ሰው ብቻ ማስቆጠር ፤ የሕጻው ግንባታ መዘግየት ፤ ቤተክርስቲያኒቱ በተቃጠለችበት ጊዜ ወደ 93ሺ ብር የሚጠጋ የሸሸ ገንዘብ ፤ ካህናትን ያለ አግባብ ከስራ ማገድ እና ደመወዝ መቁረጥ ፤ ምንም አይነት የሒሳብ ኦዲት አለመኖር እና ካህናቱም ሆኑ ምዕመናኑ ያለውን የገንዘብ መጠን እንዳያውቁ አለማድረግ ፤ ፖሊሶች ችግሩ በተፈጠረበት ጊዜ ዘወትር በግቢ መታየት ፤ ከስብከተ ወንጌል ይልቅ ገንዘብ ስብሰባ ላይ ብቻ ማተኮር (የሰርክ ጉባኤ በወር ከ3 ቀን ውጪ አለመኖር) እና መሰል በርካታ ጥያቄዎች ተነስተው ብጹዕ አቡነ እስጢፋኖስ በጊዜው መምጣት ባለመቻላቸው ተወካያቸውን ልከው ችግር ሰሚ እንጂ መፍትሄ የሚጠቁም የጉባኤ አካል ባለመኖሩ ከ5 ሰዓታት መነሻውና መድረሻው ባልታወቀ ንትርክ ስብሰባው ሊጠናቀቅ ችሏል፡፡ በወቅቱ ከበላይ አካል የመጡ ሰው ብጹዕነታቸው በተገኙበት ጥያቄዎችን መቅረብ እንዳለባቸው እና አሉ የተባሉት ችግሮች እንደሚፈቱ ቃል ገብተው ወቅቱ የፍልሰታ ጾም መግቢያ ስለነበረ ሱባኤውን ካጠናቀቅን በኋላ መፍትሄ እንሰጣለንም ብለው ነበር፡፡ ጠብ ያለ ነገር እስከ አሁን ባይኖርም፡፡

 

ዛሬ የካቲት 14 ጠዋት ረዥም ደውል ከቤተክርስቲያኒቱ ሲሰማ በአካባው ያለው ምዕመን ቤተክርስቲያን ላይ ምን ተፈጥሮ ይሆን? በማለት ከያሉበት ወደ ቤተክርስቲያኒቱ አመሩ ፤ በቦታው ላይ ግን ከፍተኛ አስተዳደራዊ አለመግባት ምክንያት አንዱ ወገን ፖሊስ ጋር በመደወል በርካታ ጠመንጃ የታጠቁ ፖሊሶች ግቢው እንዲወሩት አድርጎ ነበር ፤ ከወራት በፊትም በቦታው ስለሚከናወነው ብልሹ አሰራር ያገባኛል የሚሉ ወገኖች በቤተክርስቲያ ውስጥ ተሰብስበው ሲወያዩ ፖሊስ ግቢ ገብቶ ‹‹ተበተኑ›› እስከማለት ደርሶ ነበር ፤  ችግራችንን ከቤታችን ከመሰብሰቢያችን ተበትነን ወደ የት ሄደን ነው የምንወያየው? አለመግባባቱት ሊቀጳጰሱ አቡነ እስጢፋኖስ መፍትሄ እንደሚሰጡት ቢገለጽም እኛን ጥያቄ እንድናነሳ ያደረገን ነገር ሙሉ ጠመንጃ የታጠቁ የፖሊስ አባላቶች እንዲያ በዝተው መመልከታችን ነው ፡፡

 

ከዓመታት በፊት በአቡነ ጳውሎስ ፕትክና ዘመን የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችና በመንግሥት መካከል በተፈጠረው ግጭት ተማሪዎች መጠለያ ባሏት 5 ኪሎ ቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያን ከበላይ ባሉ አባቶች ፍቃድ የወታደር መኪና ግቢው ውስጥ በመግባት ጠራርጎ ሰንዳፋ ፖሊስ ማሰልጠኛና ፈጥኖ ደራሽ ውስጥ በእስር እንዳቆያቸውና በጊዜውም ተማሪዎቹ ላይ በደረሰ ድብደባ ከፍተኛ የአካልና የስነ ልቦና ችግር እንደደረሰባቸው የሚታወስ ነው፡፡  ምርጫ 97 አካባቢ በማኅደረ ስብሐት ልደታ ለማርያምና ደብረመድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ሰበካ ጉባኤ ፤ በአካባቢው ምዕመናንና በጠቅላይ ቤተክህነት መካከል በተፈጠረው አለመግባባት ፌደራል ፖሊሶች ስብከት ላይ የነበረውን ወጣት በፈቃዳቸው እያወጡ ሲቀጠቅጡ ድርጊታቸውን ምዕመኑም ሲቃወም እንደነበር እናስታውሳለን፡፡ ከዓመት በፊት ቤተል በሚገኝው ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያ የቤተ ክርስቲያን ቦታ ላይ ቆርሶ በመውሰድ በተፈጠረ  አለመግባባት ችግር ፌደራል ፖሊሶች ቤተመቅደስ ገብተው በማስቀደስ ላይ ያለውን ምዕመን ላይ አድማ በታኝ ጭስ እንደተኮሱ እና በወቅቱ ቅዳሴው ከመስተጓጎሉም በላይ በርካታ ሕጻናት አቅላቸውን ስተው ሲወድቁ እንደነበር እናስታውሳለን (ይህ ጉዳይ አሁን መፍትሄ አልባ ቢሆንም)፡፡

 

ይህን ሁሉ ነገር ሲሆን በአንዋር መስኪድ ሙስሊሞች ባነሱት ጥያቄ እና በውስጣቸው በተፈጠረው አለመግባባት ግን ኢቲቪ እንደነገረንና በቴሌቪዥን መስኮት እንዳሳየን ከሆነ አንድም ፌደራል ፖሊስ ወደ መስኪድ ሳይገባ ሰላማዊ ሰዎች በሰላም እንዲወጡ ካደረገ በኋላ ችግር ፈጥረዋል ያላቸውን ሰብስቦ በመውሰድ ለጥቂት ቀናት በእስር ማቆየት መልቀቁ የሚታወቅ ነው፡፡

 

ችግር በተፈጠረ ቁጥር ፖሊስ መኖሩ ችግሩን ወደሌላ አቅጣጫ እንዳይሄድ ማድረጉ መልካም ሆኖ ሳለ ፤ ለእኛ ጥያቄ የሆነብን ነገር በየቤተክርስቲያኑ ትንሽ ችግር በተፈጠረ ቁጥር ከላይ ከብጹአን  አባቶች ይልቅ ታጣቂ ፖሊስ ቤታችን የሚገባው እስከመቼ ነው? እኛስ ችግራችንን መፍታት አቅቶን በችግር ላይ ችግር የምንጨምረው እስከመቼ ነው? ሕጉ ፖሊስ ከነ ትጥቁ የእምነት ተቋማት ላይ ዘልቆ እንዳይገባ ቢከለክልም ሕጉ እንዲጣስ እኛም የበከላችንን አስተዋጽ እየተወጣን እንገኛለን፡፡ ከዚህ በፊት በአጉስታ ጽዮን ማርያም በቦታው ተገኝተን ስብሰባውን እንደተከታተልነው የምዕመኑ ጥያቄ ሲጠቀለል ‹‹ካህናት ያለ ጥፋት በደል አይድረስባቸው›› ፤ ‹‹ኦዲታችሁን አሳዩን›› ፤ ‹‹ሕንጻ ቤተ ክርስቲያኑ ለምን ቆመ?›› ፤ ‹‹ሙዳይ ምጽዋት በአግባቡ ይቆጠር›› ፤ ‹‹የሰርክ ጉባኤ ያስፈልገናል›› የሚሉ እና በመግባባትና በመወያየት የሚመለሱ ጥያቄዎች ብቻ ነበሩ፡፡ ይህን ጥያቄ መመለስ የሚገባው አካል ግን ምዕመኑን ጠርቶ ከማወያየት ይልቅ የፖሊስን ስልክ መደወል ሲቀናው ይታያል፡፡

 

የሰበካ ጉባኤ ምርጫ ሲከናወን መስቀል ይዘው የሚመጡ ብጹአን አባቶች ትተው ፓትሮል ሙሉ መሳሪያ የታጠቁ ፖሊሶች  የሚጋብዙም ቤተክርስቲያኖች ተመልክተናል፡፡ ፖሊሶቹ ከአስመራጮች እኩል የተመራጮችን ስም ሲጽፉ መመልከት ምን ማለት ነው?

 

 


አካሄዳችን እናስተካክል

2 comments:

  1. እኔ የምፈራው ከትንሽ ግዜ በሃላ ክላሽ እየተሳለማቹ ግቡ እንዳንባል ነው ወይ ጉድ ስንቱ የሞተላት ቤተ ክርስትያን እንደዚህ ትሁን ሞኝ ሰው እግዚአብሄር ዝም ሲል የሌለ ይመስለዋል ብቻ እሱ ራሱልቦና ይስጥልን

    ReplyDelete
  2. + awo yehe kenem yalefal Egeziabeher edeme yeseten !

    ReplyDelete