(አንድ አድርገን የካቲት 21 2006 ዓ.ም)፡-ኦልማን የተባለ የታሪክ ፀሃፊ በ379 በቁስጥንጥንያ የነበረውን የሃይማኖት ሁኔታ እንደሚከተለው ገልፆት ነበር፡፡
‹‹ ሃይማኖታዊ ጉዳይ እንደማንኛውም ተራ ወሬ ስራ መፍቻና የቀልድና የመዝናኛ ጉዳይ ተደርጎ ይቆጠር ነበር፡፡
ቲያትር ቤት ውስጥ የነበረው ሁኔታ ወደ ቤተክርስቲያን መጣ ፤ የቤተክርስቲያን ብቸኛ ሃብት ተደርጎ ይታይ የነበረው ጉዳይ ወደ ቲያትር ቤት አዳራሽ ተወሰደ ፤ በአንድ ወቅት የተሻለ ክርስቲያናዊ ትርጉም ይሰጠው የነበረና ወደ ቀልድ መድረኮች የማይመጣው የቤተክርስቲያን ምስጢር በአደባባይ የብዙዎች መዘባበቻ ፣ ከንፈር መምጠጫ ሆነ፡፡
በቁስጥንጥንያ መንበር ላይ የተቀመጡት አርዮሳውያን መሪዎች ይህ እንዲሆን የሚያበረታቱ ለሃይማኖትም ጉዳይ ደንታ ቢሶች ነበሩ፡፡ የቤተ ክርስቲያን የነበረውን ህዝብ ፣ ታላቅ ከበሬታ ይሰጠው የነበረውን ጉባኤ አቃለሉት ፤ ናቁት ፤ ነዋሪዋቹም እውነተኛ የነበረውን ነገር እርቃኑን አስቀሩት ፤ ቅዱስ የነበረው አለማዊ በሆኑ ሰዋች ከንፈር ተቃለለ ፤ ከዚህ ሁሉ በጣም የከፋው ፣ ሊቆጣጠሩት ያልቻሉት ቤተክርስቲያንን ማቃለልና መዘባበቻ ማድረግ ሰዋቹን ደስታ የሚሰጣቸው ነገር ሆነ ፤ ደስታ ብለው በቆጠሩት ነገር ላይ ጊዜያቸውን ማባከን ተያያዙት ፤ ቤተክርስቲያንን ወደ ቲያትር መድረክነት ፣ ሰባኪወቻቸውንም ወደ አክተርነት ለወጧቸው፡፡
ሕዝቡንም ከቤተ ክርስቲያን አውጥተው በአዳራሽ እንዲሰበሰብና የቀደመ ማንነቱን ቀስ በቀስ እንዲረሳ አደረጉት ፤ ተሳካላቸውም፡፡