Wednesday, November 6, 2013

ዘመቻ ፀረ-ተሃድሶ በደብረ ብርሃን


  • ‹‹ኢየሱስ አማላጅ ነው የሚል ምዕመንም ሆነ ካህን በሀገረ ስብከቴ እንዲኖር አልፈቅድም››ብጹዕ አቡነ ኤፍሬም
  • ‹‹አምስት ዓመት ከጣልያን ጋር የተዋጋነው ለሀገራችን ብቻ ሳይሆን ለሃይማኖታችን ጭምር ነው›› አባት አርበኛ
  • ‹‹የዘርያቆብ ከተማ ኑፋቄ አይዘራባትም›› የቅድስት ሥላሴ ቤተክርስቲያን ካህናት


(አንድ አድርገን ጥቅምት 27 2006 ዓ.ም)፡- በአሁኑ ሰዓት በደብረ ብርሃን ሥላሴ ቤተክርስያን አስተዳዳሪ በትምህርተ ሃይማኖት ፤ በአስተዳደር እና መሰል ጉዳዮች ላይ የተነሳባቸውን የካህናትና የምዕመኑን ተቃውሞ በማስመልት አጠር ያለች ዘገባ ማቅረባችን ይታወቃል፡፡  ይህን ዘገባ ያነበቡ ብዙዎች(በሁለት ቀን 6ሺ ጊዜ ተጎብኝቷል) የእኝን ሰው መጨረሻ ተከታትላችሁ አቅርቡልን ባሉን መሰረት ጉዳዩ የደረሰበትን ደረጃ እንዲህ አቅርበነዋል፡፡


በቀን 24/02/2006 ዓ.ም ከቀኑ 8፡30 ላይ በሰ/ሸዋ ሀገረ ስብከት በሊቀ ጳጳሱ ቢሮ ካህናት ፤ የአካባቢው ምዕመናን እና የሀገር ሽማግሌዎች በመገኝት የደብረ ብርሃን ቅድስት ሥላሴ ቤተክርስቲያን አስተዳዳሪ ላይ ያዩትን ሃይማታዊ ህፀፅ ለሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ለብፁዕ አቡነ  ኤፍሬም አቅርበዋል፡፡  ካህናት ፤ ምዕመናን ተወካዮችና የሀገር ሽማግሌዎች ስለ አስተዳዳሪው “ቆሞስ አባ” ማርቆስ የምንፍቅና ስብከትና አስተዳደር በሰፊው አብራርተዋል፡፡ ይህን የተመለከቱት ብፁዕነታቸው አቡነ ኤፍሬም አይናቸው እምባ እያቀረረ

‹‹ቅድስት ቤተክርስቲያን እንዲህ መጫወቻ ትሁን ፤ ያላችሁት ሁሉ አሳዛኝ ነው ፤ የአስተዳዳሩን ችግር ተውትና ‹ኢየሱስ አማላጅ› ላላችሁት ሰኞ ጥቅምት 25 ቀን 2006 ዓ.ም ከጠዋቱ 3፡00 ምስክር ይዛችሁ ኑ ጌታችንን አማላጅ ብሎ የአርዮስ ምግባር የሚደግም ካህንም ሆነ ምዕመናን በአህጉረ ስብከቴ አይኖር ….. ልጆቼ በርቱ..እርሱ ይርዳችሁ….›› በማለት አባታዊ ምክርና ትዕዛዝ አስተላፈዋል፡፡

ሰኞ በማለዳ በ25/02/06 ከጠዋቱ 2፡00 ጀምሮ በመንበረ ጵጵስና የተሰበሰቡት ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን ምዕመናን ከ3፡30 ጀምሮ የምስክርነት ቃላቸውን ሊቀ ጳጳሱ በተገኙበት እስከ ቀኑ 6 ሰዓት ድረስ ሲሰጡ አርፍደዋል፡፡ ዋና ዋና ፍሬ ሃሳቦቹ
  • ‹‹ኤልሻዳይ ቴሌቪዥን ተመልከቱ ጥሩ መልዕክት የሚገኝው ከእርሱ ነው›› ማለታቸውን የሰው ምስክር ተሰምቶባቸዋል
  • ‹‹አማላጅነት የጌታ ተግባር ነው፤ ኢየሱስ አማላጃችን ነው እሱ ሁሉን ፈጽሞልናል›› ብለው መስበካቸውን
  • ‹‹ማርያምን ስሰብክላችሁ ደስ ይላችኋል ፤ ስለ ኢየሱስ ግን ይከፋቸዋል ፤ ማርያም እኮ ከእግዲህ ዋጋ የላትም›› ብለው ማስተማራቸውን
  • ተአምረ ማርያም ፤ ድርሳናት ፤ ገድላት በጸበል ቤት እንዳይነበቡ ማገዳቸውን በርካታ ምዕመናንና ሊቃውንተ ቤተክርስቲያና በምስክርነት ቆመው መስክረውባቸዋል፡፡

ይህን ምስክርነት ከሰዎች አንደበት የሰሙት ሊቀ ጳጳሱ ፈጣን ምላሽ እንደሚሰጡ ተናግረው እንግዶችን በጸሎት ከባረኩ በኋላ
‹‹ልጆቼ እግዚአብሔር መናፍቃንን ልብ ይስጥልን እናንተንም በእምነታችሁ ያጽናልን››ብለው ሸኝተዋል፡፡

ይህ አደራጅ ሳይኖረው ቅድስት ቤተክርስቲያንን ለመጠበቅ የሚንቀሳቀስ የካህናትና ምዕመናን ጸረ-ተሀድሶ ዘመቻ ያስደነገጣቸው ‹‹አባ›› ማርቆስ በየመንግሥት መስሪያ ቤቱ ‹‹ስሜ ጠፍቷል ፤ ሽብር ተነዝቶብኛል ፤ ካህናቱ ህዝቡን አሳምጸውብኛል›› በማለት የሀሰት ፕሮፖጋንዳ ሲነዙ ውለዋል፡፡ አንዳንድ ጥቅመኞች እና የተሃድሶ አቀንቃኞች ነገሩን ተድበስብሶ እንዲታለፍ ያለፉትን ቀናት ሲጥሩ ውለዋል ፡፡ በተወሰኑ ጸረ-ተሃድሶ አቋም ይዘው የሚንቀሳቀሱ ካህናት እና ተሰሚነት ባላቸው የሀገር ሽማግሌዎች አማካኝነት የማስታረቅ ጥያቄ ከአባ ማርቆስ ደጋፊዎች (የጥቅም ተጋሪዎች) የቀረበ ቢሆንም የቀረበላቸውን ጥያቄ ጉዳዩ ሃይማኖታዊ በመሆኑ የዕርቅ ጥያቄውን የሀገር  ሽግሌዎች ውድቅ አድገውታል፡፡

ተወካይ የአገር ሽማግሌዎች መሀል አንዱ አባት ከአገረ ስብከቱ ሲወጡ
‹‹ጣልያንን አምስት ዓመት የተዋጋነው ለሀገሪቱ ብቻ አይደለም ለሃይማኖታችን ጭምር ነው፡፡ የቤተክህቱን ትምህርት ጠልቀን ባንማረውም የኛ የሆነውንና ያልሆነውን ቀልባችን እኮ ይነግረናል›› ሲሉ ተደምጠዋል፡፡

ማክሰኞ ከሰዓት በኋላ በሰ/ሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀጳጳስ በተጻፈ ደብዳቤ ለሀሙስ 28/02/2006 ዓ.ም ‹‹አባ›› ማርቆስ የእምነት ክህደት ቃላቸውን በአካል ቀርበው እንዲሰጡ ደብዳቤ እንደደረሳቸው ለማወቅ ተችሏል፡፡ ይህ ድንገተኛ ደብዳቤ በፈጠረው ድንጋጤ እና መረበሽ በ‹‹አባ›› ማርቆስ ዙሪያ ያሉ አስር ያህል ግለሰቦችን መንበረ ጵጵስና በመግባት ጉዳዩን የማለዘብና የጥቅም ግጭት ለማስመሰል ሞክረው ነበር፡፡ ሆኖም ግን በትህትና ተቀብለው ያስተናገዷቸው  ደገኛው መፍቅሬ ሃይማኖት ብፁዕ አቡነ ኤፍሬም ውጤቱን ለሀሙስ ጥቅምት 28 እንዲጠብቁ በመንገር በሰላም አሰናብተዋቸዋል፡፡

ይህ ጉዳይ የደብረ ብርሃን ሥላሴ ቤተክርስቲያን ጉዳይ ብቻ አይደለም ፤ ነገ እኚህ ሰው ከዚህ ቦታ ለቀው በሚሄዱበት ወቅት የአዲስ አበባው ቤተክህነት ወደየትኛው ሀገረ ስብከትና  ቤተክርስቲያን አስተዳዳነት እንደሚመድባቸው አይታወቅም ፤ ስለዚህ ምዕመኑ ሊሸከማቸው ያልፈቀደውን በትምህርተ ሃይማኖት ህጸጽ ያለባቸውን ሰው መረጃ ሊኖረው ግድ ይላል ፤ ስለዚህ ‹‹አንድ አድርገን›› ጉዳዩን ሁሉም የራሱ በማድረግ  ሊመለከተው ግድ ይለዋል የሚል ፅኑ እምነት አላት፡፡ እኚህ ሰው አዳማ ላይ ችግር ሲፈጥሩ ቤተክህነቱ ደብረዘይት ላካቸው ፤ ቀጥሎ ደብረዘይት ችግር ፈጥረው ሲገኙ ደብረ ብርሃን ላካቸው  ነገ ደግሞ በእርግጠኝነት አሁን ካሉበት ቦታ ሲነሱ የአዲስ አበባው ቤተክህነት የሌላ ደብር አስተዳዳሪ አድርጎ እንደሚልካቸው ይታወቃል፡፡ ስለዚህ ከቤተክህነቱ በኩል ተልከው ቢመጡ እንኳን የሚያቀርብም የሚገፋም ፤ የሚመርጥም የሚያወርድ መዕመን ነውና መረጃው የሁላችን ሊሆን ግድ ነው፡፡

‹‹አባ›› ማርቆስ ምንፍቅና ትምህርት ሃይማኖታቸውን የለወጡ ሰዎችን መረጃ የምናቀርብ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

2 comments:

  1. በርቱ!ለሆድ አደሩም የድንግል ልጅ ቆም ብለው የሜያስተውሉበት ልቦና ይስጣቸው።

    ReplyDelete
  2. The Angry Ethiopian/ቆሽቱ የበገነውNovember 10, 2013 at 6:48 AM

    ‹‹ኢየሱስ አማላጅ ነው የሚል ምዕመንም ሆነ ካህን በሀገረ ስብከቴ እንዲኖር አልፈቅድም››ብጹዕ አቡነ ኤፍሬም
    ‹‹አምስት ዓመት ከጣልያን ጋር የተዋጋነው ለሀገራችን ብቻ ሳይሆን ለሃይማኖታችን ጭምር ነው›› አባት አርበኛ
    ‹‹የዘርያቆብ ከተማ ኑፋቄ አይዘራባትም›› የቅድስት ሥላሴ ቤተክርስቲያን ካህናት

    እንደ ታላቁ ዘርዓያዕቆብ አይነት ሁለገብ የሆነ ንጉሰ ነገሥት በኢትዮጵያ ላይ ነግሶ አያቅም።

    ReplyDelete