Sunday, November 10, 2013

‹‹ተዋሕዶ›› ነን ባዮች በሕብረት በመሆን ገዳሞች ላይ እየዞሩ ይገኛሉ


  • ቦሌ ሚካኤል ቤተክርስትያን ውስጥ የቅዳሴ ስነ ሥርዓት እየተካሄደ እያለ ወደ ቤተ መቅደስ በመግባት “ኤልያስ መጥቷል የተዋህዶን ነገር በደንብ መናገር አለብኝ፤ እናንተ በከንቱ ነው የምትደክሙት፤ ኦርቶዶክስ ትክክለኛ ሃይማኖት አይደለም፤ በውስጡ ቅባትና ዘጠኝ መለኮት የሚገለጽበት ነው፡፡ እውነተኛ እና ትክክለኛ ሃይማኖት ተዋህዶ ብቻ ነው፤ ይሄንን እውነታ ለህብረተሰቡ አስተምራለሁ እሰብካለሁ” በማለት ሃይማኖታዊ ስነሥርዓቱ እንዲታወክ አድርገዋል፡፡


 (አንድ አድርገን ህዳር 1 2006 ዓ.ም)፡- አቶ አበበ ነጋሽ የሚባል ሰው በደብረ ብርሃን ኩክ የለሽ ገዳም ‹ትውልድ አልቋል› ፤ ‹8 ሺ ደርሷል› ፤ ‹ሰንበትና ነቢያት ይከበሩ› ፤ ‹ስለ ሰንበተ አይሁድ› ፤ ‹ትውልድ ሊቀጠፍ ነው› ፤ ‹ኤልያስ ወደ ምድር ወርዷል› ብሎ ሲሰብክ ተይዞ ‹የሌላ ሃይማኖት ተከታይ ሆኖ ሳለ በኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስያን ገዳም ስብከት በማከናወንና የሃይማኖት ተከታዮች ውስጥ ሁከት በማነሳሳት›› እና ተያያዥ ክሶች ቀርበውበት ፍርድ ቤት መቅረቡን መዘገባችን ይታወሳል፡፡ ከቦታው በደረሰን መረጃ መሰረት ይህን ጉዳይ ፍርድ ቤቱ  ወደ ማህበራዊ ጉዳይ ፍርድ ቤት አዙሮ እየተመለከተው መሆንን ለማወቅ ችለናል፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ ጀማነሽና እንከተለዋለን የሚሉት የእምነቱ ተከታዮች ከፍተኛ እንቅስቃሴ ላይ መሆናውን ለማወቅ ተችሏል፡፡ ዛሬ ህዳር 1 2006 ዓ.ም የዳዊት ኮከብ ቀስተደመና እና መሰል እኛነታችን ይገልጻል ያሉትን ልብስ በመልበስ በብዛት በመሆን በደብረ ብርሃን ኩክ የለሽ ገዳም አዳራቸውን ለማድረግ ተጉዘዋል ፤ ቦታው ላይም  እንደደረሱ ለማወቅ ተችሏል፡፡ እነሱ እንደሚሉት ከሆነ ከገዳም ገዳም የሚዞሩት በረከት ለማግኝት በሚል ምክንያት ሲሆን በገዳሞች ውስጥ የሚያካሂዱት ነገር ግን የዚህ ተገላቢጦች መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡


በሄዱበት ቦታ ሁላ ተቃውሞ እያስተናገዱ የሚገኙት እነዚህ ሰዎች ተቃውሞው ችለው ሃይማኖታዊ አስተምህሮአቸውን በተቃውሞ ድምጽ ውስጥም እያካሄዱ ይገኛሉ ፡፡ ቤተክርስቲያኒቱ ግን በእነዚህ ሰዎች ላይ በግለሰብ ደረጃ ካሆነ በቀር እንደ ተቋም የተቃውሞ ድምጿን ስታሰማ አልታየም ፡፡ አሁን እነዚህን ሰዎች በሕግ የቤተክርስቲያኒቱ ምዕመን ላይ እያደረሱት ያለው ጫና ከግምት ውስጥ በማስገባት ቅዱስ ሲኖዶስ ጉዳዩን ተመልክቶ አፋጣኝ እርምጃ ካወሰደባቸው ነገ ምን እንደሚፈጠር ለመገመት አይከብድም፡፡

‹‹አንድ አድርገን›› ሕገ-መንግሥቱ ያስቀመጠው ማንም ሰው የራሱን ሃይማኖት የማቋቋም እና አስተምህሮቱን የማካሄድ መብትን ትደግፋለች ፡፡ ነገር ግን ይህ መደረግ ያለበት ራስ ችሎ እንጂ በሌላው ላይ ተንጠልጥሎ መሆን መቻል የለበትም፡፡ እነዚህ ሰዎች በህጋዊው መንገድ ከፌደራል ጉዳዮች ደብዳቤ አስገብተው የአማኞቻቸውን ቁጥር ፤ መተዳደሪያ ደንባቸውን አሳውቀው የእምነት ተቋም መመስረት ይችላሉ፡፡



‹‹ተዋሕዶ›› ነን ባዮች ለምን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት ተከታዮች ላይ ብቻ እንደመዥገር መጣበቅ ፈለጉ? ‹‹ይህ ነገር ይታሰብበት›› መልዕክታችን ነው፡፡ እኛ ኃላፊነታችንን ተወጥተናል ሁሉም ባለበት አህጉረ ስብከትና አጥቢያ ቤተክርስቲያን እነዚህን ሰላማችንን ሊነሱን የተነሱ ተረፈ አይሁዳዊያን በግልጽ ሊቃወማቸው ይገባል፡፡

እነ ጀማነሽ ድብደባ እየተፈፀመብን ነው አሉ

(አዲስ አድማስ)፡-  “የማህበረ ስላሴ ዘደቂቀ ኤልያስ” ማህበር አባላት፤ በተናጥል እና በጋራ በምናራምደው እምነት ምክንያት ህገመንግስቱ የሰጠን መብት ተጥሶ ድብደባ፣ ወከባና እንግልት እየተፈፀመብን ነው፤በአባላቶቻችን ላይም ክስ እየተመሰረተ ነው ሲሉ አማረሩ፡፡ አርቲስት ጀማነሽ ሠለሞን አባል የሆነችበት ማህበረ ስላሴ ዘደቂቀ ኤልያስ “ኤልያስ መጥቷል፣ ሰንበት ቅዳሜ ነው፣ አርማችን ቀስተደመና ነው” የሚሉና መሠል ሃይማኖታዊ ሃሳቦችን የሚያራምድ ሲሆን አባላቱ ሃይማኖታዊ አስተምህሮአቸውን በተለያዩ መንገዶች ለሰዎች ለማስተማር ሲሞክሩ ለህይወታቸው አስጊ የሆኑ ጥቃቶች እየተፈፀሙባቸው እንደሆነና በአቃቤ ህግ ክስ እንደቀረበባቸው ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡፡ ከአዲስ አበባ 65 ኪ.ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው አሌልቱ ከተማ አቡነ ተክለሃይማኖት ፅላልሽ ገዳም አጥቢያ ነዋሪና የገዳሙ አገልጋይ እንደሆኑ የገለፁት ወ/ሮ ቀለመወርቅ ጀማነህ፤ የማህበረ ስላሴ አባልና አገልጋይ በመሆናቸው ብቻ በቤተሰቦቻቸው ላይ ውክቢያ፣ እንግልትና ድብደባ እንደተፈፀመባቸው ተናግረዋል፡፡

ግለሰቧ እንደሚሉት መስከረም 24 ቀን 2006 ዓ.ም የገዳሙ የሃይማኖት አባቶች፤ ቤተሰቦቻቸውን ሰብስበው “ልጃችሁ ሃይማኖታችንን እያጠፋች ነው” በሚል እንዳነጋገሯቸውና ከዚህ ድርጊት እንድትታቀብ አድርጉ የሚል ማሳሰቢያ እንደተሰጠ ገልፀዋል፡፡ የማህበረ ስላሴ አባላትን ወደ ገዳሙ ለበረከት ሐምሌ 30ቀን 2005 መጋበዛቸውን የሚገልፁት ወ/ሮ ቀለመወርቅ፤ ይህን በመፈፀማቸው “ሃይማኖታችንን የሚያጠፋ ተግባር ፈጽመሻል” ማለት፣ እንደበድብሻለን የሚል ዛቻ እንደደረሰባቸው አስታውሰው፤ ጥቅምት 17 ቀን 2006 ዓ.ም ዛቻው በቤተሰባቸው አባላት ላይ እንደተፈፀመ ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል፡፡

በእለቱ በወላጅ እናታቸው ቤት በተዘጋጀ የመታሰቢያ ዝክር ላይ ተከፍለው ወደመጡበት ሲመለሱ መንገድ ላይ ድብደባ የተፈፀመባቸው የቤተሰባቸው አባላት፤ በአካባቢው ማህበረሰብ እርዳታ እና በፖሊስ ትብብር ወደ ፖሊስ ጣቢያ በመሄድ ክስ ማቅረባቸውንና ጉዳዩም በህግ እየታየ መሆኑን ወ/ሮ ቀለመወርቅ ገልፀዋል፡፡ ከድብደባው ጋር በተያያዘም በድርጊቱ ተሣትፈዋል ተብለው የተጠረጠሩ የሃይማኖት አባቶችም ታስረው መለቀቃቸውን እኚሁ ቅሬታ አቅራቢ አክለው ተናግረዋል፡፡ በጉዳዩ ዙሪያ የገዳሙን የስራ ሃላፊዎች በስልክ ለማነጋገር ያደረግነው ተደጋጋሚ ሙከራ ባይሳካም ጉዳዩን የያዙት የወረዳው ፖሊስ ባልደረባ አቶ ገዙ ወርቁ፤ የተፈፀመው ድርጊት ገና በምርመራ ሂደት ላይ መሆኑን ገልፀውልናል፡፡ የማህበሩ አመራር አባላት ለዝግጅት ክፍላችን ባቀረቡዋቸው የክስ ዝርዝር ሰነዶች እንደተመለከተው፤ ከማህበሩ አመራሮች አንዱ የሆኑት ፕሮፌሰር ይስማቸው አለሙን ጨምሮ በባህርዳር እና በደብረ ብርሃን የሚገኙ አባላቶች አስተምህሮውን በመስበካቸው የወንጀል አንቀጽ ተጠቅሶባቸው ክስ እንደተመሠረተባቸው ተመልክቷል፡፡
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህር በሆኑት ፕ/ር ይስማው ላይ የተመሠረተባቸው ክስ እንደሚያስረዳው፤ ተከሳሹ በ28/07/2005 ዓ.ም ከሌሊቱ 10.00 ሰዓት በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 01 ክልል፤ ልዩ ቦታው ቦሌ ሚካኤል ቤተክርስትያን ውስጥ የቅዳሴ ስነ ሥርዓት እየተካሄደ እያለ ወደ ቤተ መቅደስ በመግባት “ኤልያስ መጥቷል የተዋህዶን ነገር በደንብ መናገር አለብኝ፤ እናንተ በከንቱ ነው የምትደክሙት፤ ኦርቶዶክስ ትክክለኛ ሃይማኖት አይደለም፤ በውስጡ ቅባትና ዘጠኝ መለኮት የሚገለጽበት ነው፡፡ እውነተኛ እና ትክክለኛ ሃይማኖት ተዋህዶ ብቻ ነው፤ ይሄንን እውነታ ለህብረተሰቡ አስተምራለሁ እሰብካለሁ” በማለት ሃይማኖታዊ ስነሥርዓቱ እንዲታወክ እና ረብሻ እንዲፈጠር ያደረገ በመሆኑ፤ በፈፀመው ሃይማኖታዊ ሠላምና ስሜት መንካት ወንጀል ተከሷል ይላል፡፡ በባህርዳር ዙሪያ ወረዳ ጽ/ቤት በአቃቤ ህግ ክስ የተመሠረተባቸው አቶ ጌጤ ሣህሉ ንጋት የተባሉ የማህበሩ አባል በቤተክርስቲያን ላይ የንግግር ወንጀል ፈጽመዋል የሚል ክስ የቀረበባቸው ሲሆን በደብረ ብርሃን ለባሶና ወራና ወረዳ ፍ/ቤትም አቶ አበበ ነጋሽ የተባሉ ግለሰብ፤ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሃይማኖትን በማሽሟጠጥና በማራከስ እንዲሁም የተለያዩ በራሪ ወረቀቶችን በመበተን ፈፀሙ በተባሉት ሃይማኖታዊ ሠላምና ስሜት መንካት ወንጀል መከሰሳቸው ታውቋል፡፡


No comments:

Post a Comment