(አንድ አድርገን ግንቦት 15 2010 ዓ.ም)፡- በኢትዮጵያ
በረሃዎችና አውራጃዎች እየተዘዋወሩ በልዩ ልዩ አምልኮ የነበረውን ሕዝብ የክርስቶስ ወንጌለ መንግሥትን አስተምረውና አጥምቀው የክርስቶስን
መንግሥት እንዲወርሱ ያደረጉት ቅዱስ አባታችን አቡነ ተክለ ሃይማኖት እግዚአብሔር በመራቸው መሠረት የሐዋርያ አሠረ ፍኖት
በመከተል ዘር ልዝራ ፣ ትዳር ልያዝ ሳይሉ ታላላቅ ተዓምራትን ካከናወኑባቸው ቦታዎች ውስጥ በሰሜን ሸዋ ሀገረ ስብከት
ከደብረ ብርሃን አካባቢ የሚገኝው ወይንዬ ተክለ ሃይማኖት ስፍራ አንዱ ነው፡፡ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ወይን ተክለው ለ12 ዓመታት
በቦታው በመቀመጥ ሲጸልዩበት የነበሩበትና በርካታ ተዓምራትን ያከናወኑበት ፤ ጸበል አፍልቀው አህዛብን ሲያጠምቁበት
የነበረውን ቦታ ያዩበታል፡፡ (በገድለ ተክለሃይማኖት ላይ ምድረ ደርደሬ ይለዋል)፡፡
ይህ ቦታ የሚገኝው ከደብረ ብርሃን ከተማ በስተሰሜን ምዕራብ አቅጣጫ በግምት 5 ኪሎ ሜትር
ርቀት ላይ ቀጥ ባለ ገደል ተከቦ ሲሆን እዚህ ቦታ ላይ ጻድቁ አቡነ ህጻኑ ሞአ የተወለዱበትና እንደ በሬ ተጠምደው በማረስ ገድላቸውን
የፈጸሙበት ታላቅ ስፍራ ይገኛል፡፡ በዚሁ ስፍራ ላይ ‹‹እስትንፋስ›› የሚባል ቦታ ከመሬት ሳያቋርጥ በሚወጣው እስትንፋስ አማካኝነት
በርካቶች ከተለያዩ በሽታዎች የዳኑበትና እየዳኑ የሚገኙበት ልዩ ስፍራ ይገኛል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በቦታው ቀድሞ ከኢትዮጵያ ውስጥ ከሚገኙ ትላልቅ
ገዳማት የመጡ አባቶች የሚያገለግሉበትና የሚገለገሉበት ታላቅ ቦታ ፡፡