Sunday, March 11, 2018

ድንጋይ በድንጋይ ላይ



በዲ/ን ብርሃኑ አድማስ አንለይ


ሐዋርያት ከጌታችን ጋር በደቀ መዝሙርነት በነበሩበት ዘመን ምንም ያህል ኃይልና ተአምራት የማድረግ ነገር ቢሰጣቸውም ከሌላው ሕዝብ ጋር ሲኖሩ ቀድመው የወሰዱት ጠባይ ገና አልለቀቃቸውም ነበር፡፡ ለዚህ ምሳሌ ሊሆኑን ከሚችሉት ብዙ ማስረጃዎች አንዱ ዛሬ ደብረ ዘይት እያልን በምናከብረው በዓል ላይ በሚነበብልን ወንጌል የተገለጸው ምስክር ሊሆን ይችላል፡፡ ምንም እንኳ አምላክነቱን አምነውና አውቀው ቢከተሉትም ብዙ ጊዜ ግን እነርሱን የሚያስደንቃቸው ነገር እርሱንም የሚያስደንቀው፣ ለእነርሱ የተለየ የሚመስላቸው ነገርም ለእርሱም የተለየ የሚሆን ይመስላቸው ነበር፡፡ ለዚህም ነበር ቤተ መቅደሱን እያደነቁ እርሱም የሚደነቅ መስሏቸው የነገሩት፡፡

ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ቤተ መቅደስ ከተናገራቸው መካከል ድንጋይ በድንጋይ ላይ ሳይፈርስ አይቀርም የሚለውና በበዓለ ደብረ ዘይት የሚነገረው ይህ አስደናቂ ትምህርት አንዱና ዋነኛው ነው፡፡ ይህም ማለት ለቤተ መቅደስ መሥሪያነት በመደራረብ ከታነጹትና ድንጋይ ከመባል ቤተ መቅደስ ወደ መባል ከደረሱት ውሰጥ እንደገና ተመልሰው አንዱም ሳይቀር ይነሡና ቤቱም ቤተ መቅደስ ከመባል ወጥቶ ቦታው ሜዳ ምድረ በዳ፣ ድንጋዮቹም ተመልሰው ድንጋይ ከመባል አይተርፉም ማለት ነው፡፡በርግጥ ቤተ መቅደሱ ቤተ መቅደስ መሆኑ የሚቀረው እግዚአብሔር የተለየው ጊዜ ነው፡፡ እርሱም በትምህርቱ ወቅት ራሱን ቤተ መቅደስ ብሎ ከመጥራቱ በቀር ይህን እነርሱ የሚመኩበትን ቤተ መቅደስ ቤተ መቅደስ ብሎ አልጠራውም፤ ምክንያቱም አይሁድ ቤተ መቅደስ ከመባል በግብር እያስወጡት ነበርና፡፡