- ‹‹የራበውን ሰው ለዛሬ ዓሳ አብላው፣ ለሕይወት ዘመኑ እንዲጠቅመው ግን ዓሳ ማጥመድ አስተምረው፤›› የሚባለው የቻይናውያን ታዋቂ አባባል ማስታወስ እንደ ግለሰብም፣ እንደ አገርም ጠቃሚ ነው፡፡
- ሆዱን በሆዱ ይዞ የሚኖር ሕዝብ ውስጥ በአደባባይ የሚደረግ የታይታ ልገሳ ኃፍረት ይፈጥራል
- ዕርዳታ ተቀባዮች ከአቅም በላይ ሆኖባቸው በአደባባይ ልገሳ ይቀበላሉ እንጂ፣ ከኢትዮጵያዊ ኩራታቸውና ማንነታቸው ጋር የሚጋጩ ስሜቶች ይታዩባቸዋል
ሕዝባችን እንደ እምነቱ፣ ባህሉና ልማዱ የተለያዩ በዓላትን ያከብራል፡፡ በዓላት እጅግ የተከበሩና የሚወደዱ በመሆናቸውም በሕዝባችን ውስጥ የመረዳዳት ባህሉና መስተጋብሩ የዚያኑ ያህል ትልቅ ክብረት አለው፡፡ ወትሮም የተቸገረን ባለ አቅም መርዳትና በበዓላት ወቅት አብሮ መብላት፣ መጠጣትና መደሰት ዘመናትን የተሸጋገረ የሕዝባችን ፀጋ ነው፡፡ ይህ ወደር የማይገኝለት የጋራ እሴት በዘር፣ በሃይማኖት፣ በአመለካከትና በመሳሰሉት ልዩነቶች ሳይገደብ የቀጠለ አኩሪ ተግባር ነው፡፡ ከመጠን ያለፈ ጨዋነት፣ ሥነ ምግባርና ርህራሔ የሚታይበት ይህ የሕዝባችን የመረዳዳት ባህል የኢትዮጵያዊነት የአንድነትና የጥንካሬ መንፈስ ማሳያም ነው፡፡ ዛሬ አቅም ያለው የተቸገረን ሲረዳ፣ በሌላ ጊዜ ደግሞ በተራው በሌሎች ይረዳል፡፡ መስጠትና መቀበል የበላይነትና የበታችነት ማሳያ ሳይሆን፣ ይልቁንም ማኅበራዊ ኃላፊነትን መወጫ ቱባ ባህል ነው፡፡ በቀደመው ትውልድም ሆነ አሁን ባለው ዘንድ የሚከበር ተምሳሌታዊ መስተጋብር ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ አብሮነት መኩሪያ ነው፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ይህ እሴት እየተሸረሸረ ነው፡፡ መነጋገር ይገባል፡፡