(አንድ አድርገን ህዳር 4
2008 ዓ.ም)፡- ከድርቅ እና ከርሀብ ጋር የተቆራኝ ታሪካችን አሁንም በእኛው ዘመን ተከስቶ ማየት እጅግ ያሳዝናል ፤ ቀድሞ የነበሩት
ሁለት ክፉ ጊዜያት በእኛ ዘመን ራሳቸውን ሊደግሙ በመንገድ ላይ ይገኛሉ ፤ የ66 እና የ77 ርሃብ ተብሎ በታሪክ የምናውቀው ጊዜ
ራሱን ሊደግም እያኮበኮበ ይገኛል ፤ ከ15 ሚሊየን በላይ ወገን የርሃብ ደመና አደምኖበታል ፤ መንግሥት 8.2 ሚሊየን ሕዝብ አደጋ
እንደተጋረጠበት እማኝነቱን ሰጥቷል ፤ አሁን እጅግ አስቸጋሪውን ነገር
መንግሥት ‹‹ርሃቡን ከአቅሜ በላይ አይደለም›› በማለት በሚያስተላልፈው ዜና ብዙዎች ብዙ ረድኤት ሰጭዎችን እና በሀገር ውስጥ ያሉትን
ሰዎች እያዘናጋ ይገኛል ፤ መርዳት የምንችልበት እውቀት ፤ ጉልበት እና ገንዘብ እያለን መንግሥት በርሃብ የተጎዱ ዜጎችን ራሴ እደርስላችኋለሁ
ብሎ መነሳቱ ተጎጂዎቹ ዘንድ እርዳታ በሌላ እሳቤ እና መንገድ እንዳይደርስ አንቅፋት የሆነ ይመስለናል ፡፡ ነገሩ እንዲህ ሆኖ ሳለ
አልጀዚራ እና ቢቢሲ ከመንግሥት ፍቃድ አግኝተው በተለያዩ ቦታዎች ላይ ደርሰው ያቀረቡት ዘገባ ዝናብ እጥረቱ ወደ ድርቅ ፤ ድርቁም
ወደ ርሃብ መሸጋገሩን ፤ እንስሳት በየቦታው በርሃብ ምክንያት እያለቁ
መሆኑን ፤ ሰዎችም እየተጎዱ የሚበሉትና የሚጠጡት እስከማጣት እንደደረሱ አመላክተውናል፡፡
አሁን ትልቁ ጥያቄ በምን መንገድ
የተጎዱ ዜጎች ጋር እንድረስ? የሚለው ነው ፤ ከቀናት በፊት ከዚህ
በፊት በግል ጋዜጦች ላይ የምናውቃቸው ሰዎች ተሰባስበው ለተጎዱ ወገኖች ዘንድ ለመድረስ የባንክ አካውንት ከፍተው እየተንቀሳቀሱ
ይገኛሉ ፤ ይህ አይነት አካሄድ ይበል የሚያስብል ነው ፤ ለሌሎችም በየአካባቢው ለሚገኙ ሰዎች መነሳሳት የሚፈጥር ሆኖ አግኝተነዋል፡፡
በ‹‹አንድ አድርገን›› blog በቅርብ የምናውቃቸውን ሰዎች በማሰባሰብ አሁን የተከሰተውን ችግር ጥልቀት ለመረዳት እና ሕዝቡም
እንዲውቀው ለማድረግ ያስችለን ዘንድ አምስት ሰዎችን ያካተተ ቡድን ወደተለያዩ የሀገሪቱ ክፍል ለመሄድና ጉዳቱን ለመመልከት
እቅድ የያዝን መሆኑን ለመግለጽ እንወዳለን ፤ የመጀመሪያው ጉዞ ከሳምንት በኋላ ከህዳር 11 - ሕዳር 19 ለስምንት ቀን ወደ
ሰሜኑ የሀገራችን ክፍል ጉዞ የምናደርግ መሆኑን በየቦታው
ያየነውን የታዘብነውን ፤ በድምጽና በምስል ይዘን የምንቀርብ መሆኑን ለመግለጽ እንወዳለን፡፡
ለራሳችን ራሳችን እንድረስ ….