Saturday, December 13, 2014

በዋልድባ የሥኳር ልማት አካባቢ የአንበጣ መንጋ ተከሰተ

  • እኛ አፈር ጠባቂዎች ነን፥ ቦታው የመድኃኒዓለም ነው፡፡ ስለዚህ እርሱ ይጠብቀዋል ከእኛ የሚጠበቀው የዘውትር መወድስ፣ ፀሎት እና ልመና ብቻ ነው የገዳሙ አባቶች
  • ሁለት ታላላቅ ሊቀ አበው ሳምንት በፊት ወደ ማይጸብሪ ፖሊስ ተወስደው ታስረው ተፈትተዋል፡፡
  • ወታደሮች ዛሬም ድረስ ከገዳሙ አለቀቁም፡፡
  • በመስከረም ወር ላይ በችግኝ ማፍያ አካባቢ የተነሳውን የአንበጣ መንጋ ለማጥፋት በሚል መንግሥት የረጨው መድኒት በርካታ የወልቃይት አውራጃ ነዋሪዎችን ከብቶች ጅቶባቸዋል፡፡
  • መንግሥት አሁንም 3900 የሚሆኑ አባወሮችን ከመዘጋ ወልቃይት እንደሚያስነሳ እየተነገረ ነው፡፡

 አንድ አድርገን ታኅሳስ 4 2007 ዓ.ም

በወልቃይት ተከስቶ የነበረው የአንበጣ መንጋ ይህን ይመስል ነበር

(‹‹ዋልድባን እንታደግ ፤ Save Waldda ››)፡- በዋልድባ ከሳምንት በፊት ከማይጸብሪ ፖሊስ ጣቢያ የመጡ ታጣቂዎች  ወደ ገዳሙ ዘልቀው በመግባት ሁለት ሊቃነ አበውን አስረው ወደ ማይጸብሪ አውራጃ ፖሊስ ጣባያ በመውሰድ በእስር ቤት አሳድረው መልቀቃቸው ታውቋል፡፡ በሁኔታው ያዘኑ በርካታ መነኮሳት ምን በድለው ነው? ምን ጥፋት ተገኝቶባቸው ነው? በማለት ጥያቄ ቢያነሱም መልስ ሊያገኙ አልቻሉምዓመት ከመንፈቅ በፊት በአቶ ሲሳይ መሬሳ የሚመራው የአውራጃው አስተዳደር በአበንታንት ዋልድባ ገዳም ያለውን የነበረውን የአበውን ትውፊት ወደጎን ብለው፥ በጉልበታቸው እና በሥልጣናቸው በመጠቀም የእግዚአብሔርን ቦታ እና ቤተመቅደስ የሚያስተዳድሩትን አባቶች በማን አለብኝነት በመምረጥ 1ኛ/ አባ ገብረዋሕድ መምሕር የአበረንታንት መድኃኒዓለም ገዳም አበመኔት እና  2ኛ/ አባ ገብረሕይወት መስፍን (የቀድሞ ታጋይ) እቃ ቤት አድርጎ ከሾሟቸው በኃላ ችግሮች እየበዙ እና እየጠነከሩ መምጣት መጀመራቸውን ለማወቅ ተችሏል። በተለይ የቀድሞው ታጋይ እያንዳንዷን በገዳሙ ውስጥ የሚደረጉትን እና የሚታሰቡትን በሙሉ በመቅረጸ ድምጽ በተደገፈ ማስረጃ ለመንግሥት በማቀበል፥ “ጸረ ልማት” ወይም “ጸረ ሰላም” ናቸው ብለው የሚሏቸውን መናንያን፣ መነኮሳት እንዲሁም ባሕታውያን  በፈለጉ ጊዜ ወደ እስር እንዲጋዙ፣ ድብደባ፣ እና ለስደት እንዲዳረጉ እያደረጉ ይገኛሉ


ይህ ሁሉ መከራ እና ግፍ የሚፈጸምባቸው ፍቅረ ክርስቶስ ይዟቸው ይህን ጣፋጭ ዓለም ትተው እራሳቸውን ከዓለም ደብቀው በጸሎት፣ በስግደት ባሉበት ቦታ መጥተው እንዲህ ያለ ግፍ ሲፈጽሙባቸው ማየት ያሳዝናል። በፍልሰት ከሚኖሩበት ተጎትተው ለእስር የበቁት ሁለ አባቶችም ደረሰባቸው መከራ የተሰጣቸውም ምክንያት “ከቤተ ጣዕመ አባቶች ጋር በአንድነት አትሰሩም፣ መስቀላቸውንም አትስሙም በፍልሰት መቀመጥ አትችሉም” የሚል ነበር፡፡(በማይጸብሪ ፖሊስ ጣቢያ  የነበሩት ሁለት ሊቃነ አበው አባ ገብረ ኪዳን እና አባ ገብረ መስቀል ይባላሉ)

በዋልድባ ገዳም ከሦስት ዓመት በፊት የወልቃይት ሥኳር ፋብሪካ ፕሮጀክት ከተጀመረ ወዲህ በርካታ የመንግሥት ታጣቂ ወታደሮች በገዳሙ አካባቢ መታየት ጀምረው ነበር፥ አሁንም ድረስ  በገዳሙ የተለያዩ አካባቢዎች በርካታ ታጣቂዎች ሰፍረው ይገኛሉ፣ከአንድ አመት በፊትም የጃናሞራና የወልቃይት አርሶ አደሮች በገዳሙ ላይ እየደረሰ ያለውን ችግር ለመንግሥት ተወካዮች ቢያሳስቡ እናንተ ጸረ ልማቶች ተብለው ሲወነጀሉ ጥቂት የማይባሉ የአካባቢው አርሶ አደሮች ሸተው ጫካ መግባታቸው ይታወቃል፡፡

ወደ አራት ዓመት ሊሞላው ጥቂት ወራት የቀሩት የወልቃይት ስኳር ፋብሪካ ግንባታ ጋር ተያይዞ የዛሬማ ወንዝን ገድቦ ወደ 40 ሄክታር የሚገመት መሬት ከአበረንታንት መድኃኒዓለም ገዳም ቀምቶ ሊገደብ የታሰበው ግድብ እስከ አሁኗ  ደቂቃ ድረስ ትልቅ ግድብ ቀርቶ ጥቂት ውሃን እንኳን ሊያቁር የሚችል ነገር መስራት ለመቻላቸው መንግሥትንም ሆነ ለስራው ቅርበት ያላቸውን ሰዎች ነገሩ ራስ ምታት እንደሆነባቸው ለማወቅ ተችሏል  ፣ በርካታ ባሕታውያንም ገና ከጅምሩ ሲናገሩ እንደነበሩት “በመድኃኒዓለም ቦታ ላይ ማንም ምንም አይሰራም እግዚአብሔር ተዋጊ ነው ስሙም እግዚአብሔር ነው በማለት ላይ ይገኛሉ። 


በቦታውም ባሳለፍነው መስከረም ወር አካባቢ የተከሰተው የአንበጣ መንጋ ብዙ ውድመትን ማድረሱ ታውቋል።በወቅቱ የስኳር ልማት ኮርፖሬሽኑ ከታሊማ ወንዝ በተጠለፈ ውሃነን በመገደበብ  ወደ 30 ሄክታር የሚሆን መሬት ላይ የሸንኮራ ችግኝ በመማፈፍለላተት ሙከራ ላይ ነበር። ከጥቂት ወራት በፊት በግንቦት እና ሰኔ አካባቢ በአንዳንድ የአካባቢው ገበሬ መኅበር ታይቶ የነበረው የአንበጣ መንጋ ጊዜውን ጠብቆ በመስከረም እህል በሚያፈራበት ወቅት በመምጣት በ30 ሄክታር ላይ የተፈላውን የሸንኮራ ችግኝ ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል፤ መንግሥትም በምላሹ በአካባቢው ላይ በርካታ ሰዎችን በማሰማራት መድኅኒት በመርጨት  የአንበጣ መንጋውን ለማጥፋት ሙከራ ቢያደረግም በአካባው ላይ ከመጠን ያለፈ መድኃኒት በመጠቀሙ የአካባቢው አርሶ አደሮችን ከብቶች ላይ በግጦሽ ስፍራዎቻቸው ላይ ባደረሰው ጉዳት በርካታ ከብቶች በመድኃኒቱ ምክንያት በየቦታ ወድቀው መገኝታቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡ የአካባቢው አርሶ አደርም ደጋግመው አቤቱታቸውን ለሚመለከተው አካል ቢያሰሙም ሰሚ ጆሮ ሳያገኙ መቅረታቸው ታውቋል


ከዚህም በተጨማሪ ከዓመት በፊት በልማት ሰበብ በርካታ ነዋሪዎች ቀያቸውን ለቀው በምትኩ ሌላ ቦታ ይሰጣችኃል በማለት የትም ሜዳ ተበትነው እንደሚገኙ ከስፍራው የደረሰን መረጃ ያመለክታል። አሁንም መንግሥት በሚቀጥሉት ጥቂት ወራት ውስጥ 3900 አባወራዎችን ሊያነሳ እና ቦታቸውን ሊወስድ እንደሆነ በሰፊው እየተነገረ ይገኛል። ነዋሪዎችም ከዚህ በፊት ተነስተው የት እንደደረሱ ያልታወቁት በርካታ ነዋሪዎችን እጣ ፈንታ በእነሱም ላይ ሊደርስ እንደሚችል በመገመት በርካቶች በከባድ ስጋት ላይ እንደሚገኙ ለመረዳት ችለናል። የሸንኮራው ጉዳይ አልሳካ ያላቸው የመንግሥት ሰዎች በርካታ የአውራጃውን ነዋሪ ካስነሱ በኃላ ሰሊጥ፣ ነጭ አደንጓሬ፣ እና ጥጥ የመሰሳሰሉትን እያለሙ እንደሚገኙ ከዚሁ ጋር ተያይዞ በመጣ መረጃ ለመረዳት ችለናል። ።

አሁንም የበርካቶች ስጋት እነዚህን ምርቶች በአካባቢው በማምረት ውጤት የሚመጣ ከሆነ  በዚህ ሰበብ ለበርካታ ነዋሪዎች መፈናቀል እና ለዋልድባ ገዳምም ይበልጥ አደጋው ከፍተኛ እንደሆነ ይገመታል። በተለይ በገዳሙ ሞፈር ውሃ በሚባለው አካባቢ በርካታ የእርሻ ቦታዎችን በመውሰድ ለእነዚህ አይነት ሥራዎች እንደሚያደርገው ስለታወቀ ስጋታችን ይበልጥ ጨምሯል በማለት የአካባቢው ነዋሪዎች ይናገራሉ። መናንያኑም በበኩላቸው እንደ ከዚህ ቀደሙ፤ በዋልድባ ምድር ላይ ምንም ነገር ቢመጣ ሊሰሩም ሆነ ሊያደርጉ የሚችሉት ነገር እንደማይኖር ደጋግመው ይናገራሉ። “እኛ አፈር ጠባቂዎች ነን፥ ቦታው የመድኃኒዓለም ነው፡፡ ስለዚህ እርሱ ይጠብቀዋል ከእኛ የዘውትር መወድስ፣ ፀሎት እና ልመና ብቻ ነው የሚፈልገው፥ እኛም ጸሎታችንን ልመናችንን አናቆምም፤ እነሱም በይላቸው ተመክተው የክርስቶስን ቦታ ለመውሰድ በሚያደርጉት ተግዳሮት ቀስ በቀስ እየተቀሰፉ ስራውን እስኪያቆሙ ይቀጥላል ይላሉ ያነጋገርናው አባቶች።

 ቅድስት ሃገራችንን፣ ተዋሕዶ ሃይማኖታችንን በረደኤት ይጠብቅልን
ቸር ያሰማን አሜን

ምንጭ ፡- ከ‹‹ዋልድባን እንታደግ››

2 comments:

  1. ወደ አራት ዓመት ሊሞላው ጥቂት ወራት የቀሩት የወልቃይት ስኳር ፋብሪካ ግንባታ ጋር ተያይዞ የዛሬማ ወንዝን ገድቦ ወደ 40 ሄክታር የሚገመት መሬት ከአበረንታንት መድኃኒዓለም ገዳም ቀምቶ ሊገደብ የታሰበው ግድብ እስከ አሁኗ ደቂቃ ድረስ ትልቅ ግድብ ቀርቶ ጥቂት ውሃን እንኳን ሊያቁር የሚችል ነገር መስራት ባለመቻላቸው መንግሥትንም ሆነ ለስራው ቅርበት ያላቸውን ሰዎች ነገሩ ራስ ምታት እንደሆነባቸው ለማወቅ ተችሏል ፣ በርካታ ባሕታውያንም ገና ከጅምሩ ሲናገሩ እንደነበሩት “በመድኃኒዓለም ቦታ ላይ ማንም ምንም አይሰራም እግዚአብሔር ተዋጊ ነው ስሙም እግዚአብሔር ነው” በማለት ላይ ይገኛሉ።

    ReplyDelete
  2. “በመድኃኒዓለም ቦታ ላይ ማንም ምንም አይሰራም እግዚአብሔር ተዋጊ ነው ስሙም እግዚአብሔር ነው” በማለት ላይ ይገኛሉ።

    ReplyDelete