(Addis Admass:- )በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ የፓትርያርኮች መንበር (መንበረ ፕትርክና) በኾነችው ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም፣ በሚሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብና ንብረት በአስተዳደር ሓላፊዎችና ሠራተኞች መመዝበሩን ምንጮች ጠቆሙ፡፡ጥቆማው የቀረበው፣ የገዳሟ ማኅበረ ካህናትና የልማት ኮሚቴ የቤተ ክርስቲያኒቱን የገንዘብና የንብረት አሰባሰብ በተመለከተ ግልጽነትና ተጠያቂነት ያለው አሠራር እንዲዘረጋ የገዳሟ ልማት ኮሚቴ የበላይ ጠባቂ ለኾኑት ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ ባቀረቡት ማመልከቻና ሪፖርት ነው፡፡
የቤተ ክርስቲያኒቱ መተዳደርያ ቃለ ዐዋዲና ደንቡን መሠረት አድርጎ በሀገረ ስብከቱ የተዘጋጀው የገንዘብ ቆጠራ፣ የንብረት አመዘጋገብና አጠባበቅ መመሪያ የካህናቱን፣ የምእመናኑንና የእያንዳንዱን ሠራተኛ የሥራ ድርሻና ተጠያቂነት በግልጽ ማስቀመጡን የጠቀሱት ማኅበረ ካህናቱ÷ የገዳሟን ገንዘብና ንብረት የመቆጣጠርና የመከታተል መብታቸው በአስተዳደሩ ሓላፊዎች ተነፍጓቸው የሙዳየ ምጽዋት ቆጠራና የንብረት ቁጥጥር ለማድረግ ሳይችሉ መቆየታቸውን ገልጸዋል፡፡