ይህ የአንድ ሰው ሀሳብ ነው ፤ የማንም አቋም አይደለም
(አንድ አድርገን ሚያዚያ 17 ፤ 2004 ዓ.ም )፡- መቼስ በባለፈው
የክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችን ንግግር ያልተናደደ ቢኖር ማህበረ ቅዱሳንን የማያውቅ ያለበለዚያ በተቃራኒ የቆመ ሰው ብቻ ነው ፤ ማህበሩ
ወጥ የሆነ ተጠያቂነትና ግልጽነት ያለው ማህበር ነው ፤ እንደ ጠላት ተደብቆ ስራውን የሚሰራ መንፈሳዊ ተቋም አይደለም ፤ በርካታ
በመቶ ሺዎች የሚቆጠር አባላት ያለው ፤ በተቻለው እና አቅሙ በፈቀደ መጠን ቤተክርስትያንን ለመርዳት ፤ የተዘጉትን ለማስከፈት ፤
የሰባኪ ወንጌል ችግር ያለባቸውን መምህር በመመደብ ፤ ለገዳማትና የተቸገሩ አብያተክርስትያናት ፕሮጀክት በመቅረጽ በቋሚነት የሚረዳ
፤ ምዕመኑ በመንፈሳዊ ህይወቱ ጠንካራ እንዲሆን የቤተክርስትያኒቱን መንፈሳዊ ትምህርት ከማስተማሩም በላይ በርካታ አሁን ዘርዝሬ
የማልጨርሳቸውን ዘርፈ ብዙ ስራዎችን እያከናወነ የሚገኝ መንፈሳዊ ተቋም ነው ፤ ከወራት በፊት ዲ/ን ዳንኤል ክብረት በማህበሩ ላይ
ያለው ተቃውሞ ባነሳበት ጊዜ የብዙዎች መነጋገሪያ ርዕስ መሆኑ የቅርብ ጊዜ ትውስታችን ነው ፤ ይህን የመሰለ አስቸጋሪ ሁኔታም ቢፈጠር
ችግሮችን በመነጋገር መፍትሄ በመስጠት በችግር ጊዜ ጥንካሬውን አሳይቷል ፤ መንፈሳዊ ህይወትና ወንጌሉ እንደሚያዘውም በወንድሞች
መካከል የተፈጠረውን ቅራኔ ይቅር በማስባባል ያጠፋው ይቅርታ እንዲል ፤ የተበደለውም ይቅርታውን እንዲቀበል አድርጓል ፤ እኛም በሁኔታዎቹ
ብናዝንም በስተመጨረሻ ደስ ብሎናል ፤ ፈተና ተቋሙን በሚያናጋ መልኩ ከግለሰብ ሊነሳ ይችላል ፤ ከማህበሩን ከተቃራኒ መንገድ የቆሙ
ሰዎች ሊነሳ ይችላል ፤ ከቤተክህነቱም ሊነሳ ይችላል ፤ ከመንግስትም ሊነሳ ይችላል ፤ እንደ ባለፈው ሳምንት ደግሞ ከጠቅላይ ሚኒስትሩም ሊነሳ ይችላል ፤ ነገር
ግን ፈተና በየጊዜው መፈጠሩ ሊያስገርመን አይገባም ፤በዮሐንስ ወንጌል 16፤33 ‹‹በእኔ ሳላችሁ ሰላም እንዲሆንላችሁ ይህን ተናግሬአችኋለሁ።
በዓለም ሳላችሁ መከራ አለባችሁ፤ ነገር ግን አይዞአችሁ፤ እኔ ዓለምን አሸንፌዋለሁ።›› ተብሎ ተጽፏል ፡፡ ስለዚህ መከራም ይሁን
ፈተና በጌታችን በመድሀኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ እናልፈዋለን እንጂ የሚመጣውን ፈተና ፈርተን ወደ ኋላ አንልም ፤ በፊትም ፈተና
ነበር ፤ ዛሬም አለ ፤ ነገም የህይወትን መስዋእትነት የሚጠይቅ ፈተና ሊመጣ ይችላል ፤ ግን ሁሉም እንደ አመጣጡ ያልፋል፡፡