Wednesday, January 25, 2023

እግዚአብሔር ይመስገን !!


********************
ከቀኖናና ከህግ ውጪ በተደረገው ሲመት ከተሾሙት መካከል መጋቤ ብሉይ ወ ሐዲሳት ቆሞስ አባ ጸጋዘአብ አዱኛ በመንበረ ፀባዖት ቅ/ሥላሴ ካቴድራል የብሉያትና የሐዲሳት ትርጓሜ ጉባዔ ቤት መምህር  የነበሩ ሲሆን ከገቡበት  አገር የማፍረስ አደገኛ ሴራ ተልዕኮ ከያዘው ቡድን ራሳቸውን አግልለው በዚህ ሰዓት ቤተክርስቲያንን ይቅርታ ለመጠየቅ ቅዱስ ሲኖዶስ ጽሕፈት ቤት ተገኝተው ለብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ (ዶ/ር) የይቅርታ ደብዳቤ አስገብተዋል።

#አንድ_ሲኖዶስ ...የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን
                          ቅዱስ ሲኖዶስ 

#አንድ_መንበር ...(መንበረ ተክለሃይማኖት)

#አንድ_ፓትሪያርክ ...ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ !!!

#_ኩላዊት_እንጂ_ክልላዊት_ቤተክርስቲያን_የለችንም !!!

🙏ቅድስት ቤተክርስቲያኒቱ ለ3 ቀናት የሚቆይ ጸሎት አወጀች‼️


👉 በዛሬው ዕለት የተካሄደው የቅዱስ ሲኖዶስ የመክፈቻ ጸሎት በመንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ቅድስት ማርያም ገዳም ከተጠናቀቀነ በኋላ ሁሉም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ምእመናን ከዛሬ ጥር 17 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ ለሚቀጥሉት ሦስት ቀናት የጸሎትና የሱባኤ ጊዜ እንዲሆን አዋጅ መታወጁን ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ (ዶ/ር) የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ እና የኒዮርክ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ገልጸዋል።

የቅዱስ ሲኖዶስ የመክፈቻ ጸሎት በመንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ቅድስት ማርያም ገዳም መከናወን ጀመረ፡፡


የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ በማያውቀውና ሕገ ቤተ ክርስቲያንን ባልጠበቀ መንገድ የተሰጠውን ሕገ ወጥ "ሢመተ ኤጲስ ቆጶሳት" በማስመልከት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት በአስተላለፉት ጥሪ ለሚደረገው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ዛሬ ረቡዕ ጥር 17 ቀን 2015 ዓ.ም መንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም የመክፈቻ ጸሎት ማድረግ ተጀምሯል፡፡

የጸሎት መርሐ ግብሩ ላይ ቅዱስ ፓትርያርኩ እንዲሁም ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት የመምሪያ ኃላፊዎች በተገኙበት በመከናወን ላይ ነው፡፡

©የማኅበረ ቅዱሳን ብሮድካስት አገልግሎት

አስቸኳይ የቅዱስ ሲኖዶስ መልእክት፤


+++++++++++++++++++++++++++++++++++++
ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊና የኒውዮርክ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በመላው ዓለም ለሚገኙ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳሳት ባስተላሐፉት መልዕክት እንደገለጹት በየትኛውም የዓለማችን ክፍል የሚገኙ አበው ሊቃነ ጳጳሳት በቤተክርስቲያናችን ላይ በተፈጸመው የቀኖና ጥሰትና ሕገ ወጥ ድርጊት ዙሪያ ለመወያየት በየትኛውም የዓለማችን ክፍል የሚገኙ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት ወደ አገራቸው እንዲገቡ ጥሪ መተላለፉን አስታውሰው  በአየር ትራንስፖርቱ ዘርፍ በጉዞአቸው ላይ ችግር እንዳይገጥማቸው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት ቅድሚያ እንዲሰጣቸው ከቤተክርስቲያናችን በቀረበው ጥሪ መሰረት አየር መንገዱ ፍጹም ፈቃደኛና ተባባሪ መሆኑን አረጋግጧል ብለዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድም የቤተክርስቲያንን ጥሪ ተቀብሎ ፈቃደኛነቱን በመግለጹ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ልባዊ ምስጋናዋን እያቀረበች በየትኛውም የዓለማችን ክፍል የምትገኙ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት አየር መንገዱ የሰጠውን እድል በመጠቀም ወደ አገራችሁ በመምጣት ቤተክርስቲያናችን በረጅም ዘመን አገልግሎቷና በታሪኳ ገጥሟት የማያውቀውን ችግር በጋራ ሆነን እንፍታ በማለት መልእክታቸውን  አስተላልፈዋል።

አቡነ አብርሃም ዛሬም ታሪክ ሰሩ


“እናንተ እዚህ አራት ኪሎ ተቀምጣችሁ፤ ሌላው ቦሌ ሆኖ መንግሥት መስርቻለሁ ቢል ዝም ብላችሁ ትቀበላላችሁ፣ በሽምግልና እንፍታው ትላላችሁ?”
||| 

በዛሬው ዕለት መደበኛ የቋሚ ሲኖዶስ ስብሰባ በሚደረግበት ወቅት የመከላከያ ሚንሰቴሩ አብርሃም በላይ እና የሃይማኖት ተቋማት አባቶች ቀጠሮ ሳያስይዙ ድንገተኛ በሆነ መልኩ በመንበረ ፓትርያርክ ጽ/ቤት በመሄድ አቡነ አብርሃምን ተጭነው የሹመቱን ጉዳይ ለማሳመን እና ጉዳዩ በሽምግልና ይፈታ ብለው ቢጠይቁም ሌሎችም የቋሚ ሲኖዶስ አባላት በሽምግልና ስም የመጡትን ሃሳባቸውን ውድቅ አድርገው ዳግም በዚህ መልኩ መምጣት እንደሌለባቸው አሳስበው መልሰዋቸዋል፡፡ 

አቡነ አብረሃም፡- 
“ይሄ ጉዳይ የሃይማኖት፣ የቀኖና፣ የሥርዓተ ቤተክርስቲያን እና የህግ የበላይነት ጉዳይ ነው፡፡ ስለዚህ በእርቅ የሚፈታ አይደለም፡፡” ብለው ቁርጥ አርገው ሲናገሩ፡፡ 

ሌሎቹም ጳጳሳት ለመከላከያ ሚንስቴሩ ለአብርሃም በላይ “እናንተ እዚህ አራት ኪሎ ተቀምጣችሁ፤ ሌላው ቦሌ ሆኖ መንግሥት መስርቻለሁ ቢል ዝም ብላችሁ ትቀበላላችሁ፣ በሽምግልና እንፍታው ትላላችሁ?” ብለው ምላሽ በማሳጣት ሽምግልና የመጡትን ሁሉም በአንድ አቋም ምላሽ አሳጥተው መልሰዋቸዋል፡፡

Tuesday, January 24, 2023

የቤተ ክህነታችን ሦስቱ አርእስተ ኃጣውዕ፤

Written by Dn. Birhanu Admass Anleye

የተፈጸመው ድርጊት ለብዙዎቻችን እጅግ አሳዛኝ፣ አስደንጋጭ፣ አዋራጅ እና ቅስም ሰባሪም ነው። ይልቁንም ደግሞ አንዳንድ እጅግ የምናከብራቸው እና የምንወድዳቸው ብቻ ሳይሆን የምናምናቸውም አባቶች ጭምር መካተታቸው የበለጠ እንድናዝን አድርጎናል። ይህም የዕውቀታችንን ውሱንነት ብቻ ሳይሆን መታመን መጥፋቷን፣ ፈተና እና ችግር እንኳ ቢኖር እርሱን ተቋቁሞ ማለፍ የመቻል አቅም መሳሳቱን፣ ፍቅረ ሲመትም ክንፍ አውጥቶ መብረሩን ይፋ አድርጎ አስጥቶታል።

በርግጥ የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ በቀር ይህን መሰል ጥፋቶች እንደማይቀሩም የመጣንበት መንገድ አመላካች ነበር። ጌታችን በወንጌል “አልቦ ዕፅ ሠናይ ዘይፈሪ ፍሬ እኩየ፣ ወአልቦ ዕፅ እኩይ ዘይፈሪ ፍሬ ሠናየ” ሲል እንደገለጸው የመጣንበት የሲመት መንገድ የዚህ ዓይነት ፍሬ ላይ ሊያደርሰን እንደሚችል ብዙዎች ተናግረው ነበር፤ ይታወቃልም። የመጣንበት የሲመት ባህልም እንበለው መንገድ እጅግ ብዙ ጉድለቶች እና ውሱንነቶች እንደነበሩበት ቢያንስ አሁን እንኳ ዝም ልንል አንችልም። ዛፉ መልካም ከሆነ ፍሬው መጥፎ ሊሆን አይችልም የሚለውን የጠቀስኩት ለዚህ ነው። እውነቱን ለመናገር ከልክ ያለፈ ይሉኝታ እና ምን አገባኝ ብዙ ጥፋቶችን እያከተተለ እንዳመጣብን ለመረዳት አይቸግርም። ከዚህ በኋላ ግን እንታገስህ ብንለው ራሱ ችግሩ አይታገሰንም። እንቻልህም ብንለው ሞልቶ ፈስሷል እና አንችልም። መጠን የለሽ የጎጠኝነት፣ የተንኮል፣ የበቀለኝነት፣ የሌብነት፣ የጉቦ እና የቡድነኝነት ዛፋችን ያፈራውን ፍሬ ነው ዛሬ የተመለከትነው። ቅዱስ ጳውሎስ ሐዋርያ “ዘዘርዐ ሰብእ የአርር” – ‘ሰው የዘራውን ያጭዳል' እንዳለ በገላትያ መልእክቱ ያጨድነው በዘመናት የዘራነውን መሆኑን ልንክድ አንችልም። በዚህ ጉዳይ አብረን ንስሐ ገብተን መታረም እንችላለን ብዬም አላምንም። ፈጽሞ ሲያጠፋን ግን ከዚህ በላይ ዝም ብለን ልናየው የሚገባን አይመስለኝም። ልምምጥም ሆነ ልመናም የሚያስፈልገው አይመስለኝም። የሚያስፈልገው ወደ ሕግ እና ሥርዓት ቀጥ ብሎ መግባት ብቻ ይመስለኛል። ይበቃል! በእውነት ይበቃል። ከዚህ በላይ ምን ልንሆን እንችላለን? ሹመትም ሆነ ምደባ በሕግ እና በሥርዓት ብቻ መፈጸም አለበት ። ይህ እስካልሆነ ድረስ ችግሩ ይቀጥላል ብቻ ሳይሆን እንደጠፉት ሀገሮች እና ዛሬ እንዲህ ነበሩ እየተባለ እንደሚነግርላቸው እኛም እንጠፋለን። ዐፅመ ሐዋርያት እና ሰማዕታት ከተከማቹባት፣ ሦስቱ ዐለም አቀፍ ጉባኤዎች ከተካሔዱባት፣ እኛ ከምንቀድሳቸው ዐሥራ አራት ፍሬ ቅዳሴዎች ውስጥ ከስምንት ያላነሡት ካመጣንባት፣ ዮሐንስ አፈወርቅ፣ ባስልዮስ ዘቂሳርያ፣ ጎሮጎርዮስ ዘእንዚናዙ፣ ጎርጎርዮስ ዘኑሲስ ካስተማሩባት እና ከገለገሉባት የቁስጥንጥንያ መንበር ሙሉ በሙሉ መጥፋት መማር ካልቻልን ከምን ልንማር እንችላለን በእውነት? እንደ እኔ ሕመማችንን በአግባቡ ካልታከምነው እንደ ጋንግሪትም በድን ያደረገውን ቆርጠን ካልጣልነው ሙሉ በሙሉ መጥፋታችን የሚቀር አይመስለኝም። ስለዚህ ከይሉኝታ መጋረጃ ወጥተን ነገር ግን ደግሞ ሕግ እና ሥርዐት ጠብቀን በችግሮቻችን ላይ መዝመት መጀመር አለብን ብዬ አምናለሁ።  ምን ምን ችግሮቻችን ላይ ቆራጥ እርምጃዎች መውሰድ እንችላለን? ለዛሬው እንደ አርእስተ ኃጣውዕ ያሰብኳቸውን ሦስቱን አነሣለሁ። 

1) ባዕድ እጅ 

አቡነ ቴዎፍሎስን ለማውረድ ደርግ አንድ ኮሚቴ አቋቁሞ ነበር ይባላል። ኮሚቴው የተሐድሶ ኮሚቴ ይባል ነበር አሉ። ለዚህ ኮሚቴ በሰብሳቢነት የተሾሙት ደግሞ አንድ እጃቸው አርትፊሻል ነበረ። ታዲያ ብዙ የቤተ ክህነት ሊቃውንትን በደብዳቤ እያስገደዱ ወደ ኮሚቴው ሲያስገቡ መልአከ ብርሃናት ተስፋ ወርቅነህ የሚባሉት ሊቅ በእኒህ ሰብሳቢ የተፈረመ ደብዳቤ ሲደርሳቸው አዝነው ቤተ ክርስቲያን ባዕድ እጅ ገብቶባታል የምትሆነውን እንጃ ብለው ነበር፤ ቅኔም ተቅኝተውበት ነበር ይባላል። 
 
ይህች ባዕድ እጅ ከዚያ ዘመን አንሥቶ እስካሁን ድረስ ትበጠብጣለች። ምንም እንኳ በየዋሕ ምእመናን፣ በጉባኤ ቤት መምህራን፣ በስውራን ቅዱሳን እና በየቦታው ባሉ ደጋግ ካህናት እና አገልጋዮች መኖር ምክንያት ረድኤተ እግዚአብሔር ስላልተለየን ፈጽመን ባንጠፋም በየዘመናቱ እየወረድን፣ እየተዋረድን እዚህ መድረሳችን ግን ከማንም የተሰወረ አይደለም። 

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ወደ መንበረ ፕትርክናው ከመምጣታቸው በፊት ጥሩ የምርጫ ሕግ እንዲኖረን እና በመጨረሻም በድምፅ ከተመረጡት ሦስት አባቶች መካከል ፓትርያርክ የሚሆነው በጸሎት እና በዕጣ ይለይ የሚለውን ረቂቅ ለማስቀረት ይህች ባዕድ እጅ ብዙ ሚና ተጫውታለች ። በተለይ አንተን ነው ፓትያርክ የምናደርግህ እያሉ ፖለቲከኞቹ ያባበሏቸው እና ቅዠት ውስጥ የከተቷቸው ሰዎች እና ደጋፊዎቻቸው ያለ ይሉኝታ ተቃወሙት ። አሁንም ድረስ ልባቸው ተላላ የሆኑና ከዚያ የማይማሩ ሰዎችን ስናይ እጅግ እንገረማለን፣ እናዝናለንም። በእውነት ልብን ያደማል። እስከመቼስ ሲደበቅ ይኖራል? 

ይህች ባዕድ እጅ ከባድ የምትሆነው ደግሞ ሁሌም ቤተ ክህነት ውስጥ ባለ እና እጁ በተቆረጠችበት ሰው በተቆረጠችበት እጁ ምትክ በባለሞያዎች እውነተኛ እጅ መስላ የምትቀጠል በመሆኗ ነበር። ይህች እጅ እስካሁን ታቦካለች፣ ትጋግራለች፣ ትሾማለች ፣ ትሽራለች ። ተላላ ልቦችን እያባበለች ወደ ጥፋት ገደሏ ትከታለች። እከብር ባይ ልቡናዎችን በሕልም ዐለም ይዛ ትጠፋለች፣ በምናባዊ ሹመት ታሳብዳለች ። ዛሬ በማኅበራዊ ሚዲያ እንዳየሁት ዛሬ ከተሾሙት ውስጥ ከመሾማቸው በፊት እንደ ጳጳስ ለብሰው ፎቶ የሚነሡ ነበሩበት ፤ ይገርማል፣ ያሳዝናል። ይህች እጅ የቅባት ጳጳሳትን በጥንቃቄ አዋልዳለች ።  መንበረ ሰላማ የጵጵስና መንበረ ተክለ ሃይማኖት ደግም የእጨጌነት እንጂ የፓትርያርክ አለመሆኑን እንኳ የማያውቁ ሰዎችን አሰባስባ በትግራይም ታገሣለች ። ይህች ባዕድ እጅ አሁንም የልዩነት ገደላችን ትቆፍራለች፣ ታሰፋለች፣ ታስፋፋለች ።  በእነዚህ ዘመናትም በሕጉ እና በተግባሩ መካከል ያለውን ገደል አስፍታ አስፍታ በአብርሃምና በነዌ መካከል ያለውን ገደል አድርጋዋለች ። በእውነት ያሳዝናል። 

ይህች እጅ ግን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መወገድ አለባት ። የምትወገደው ደግሞ እኛ ቆርጠን ስንነሣ ነው። ግብጾች አሁን ያላቸውን የምርጫ ሕግ ያወጡትን እና ብዙ ተደራራቢ የቆየ ችግራቸውን የፈቱት ሁሉም ምእመን በተሳተፈበት ሁለት ዐመት ተኩል በፈጀ ውይይት እና በመጨረሻም ሕግ አውጥተው በመፈጸም ነው። ቫቲካንም የፖፕ ምርጫውን በተዘጋ ቤት እና በጢስ ብቻ እንዲታወቅ አድርጋ በሯን የቆለፈችው ይህችን የባዕድ እጅ ላለማስገባት ነበር። ሌሎች አብያተክርስቲያንም ይህችን እጅ ቆርጠው ጥለው ቀኖናዊነታቸውን ለማስከበር በቅተዋል። እኛ ጋር ግን አሁንም ድረስ በየድስቱ እየገባች ታማስላለች ። እስከመቼ ግን እንዲህ ልንቀጥል እንችላለን? ይህች ባዕድ እጅ መሰብሰብ ይኖርባታል። 

2) የምእመናን ድርሻ የረሳ ኢቀኖናዊ ሲመት

በቀኖናችን በሚሾምበት ሀገረ ስብከት ያሉት ምእመናን ያለተቀበሉት ሰው በጵጵስና እንዳይሾም የተከለከለ ነው። እኛ ሀገር ግን ያለው የተገላቢጦሽ ነው ማለት ይቻላል። ሌላው ቀርቶ ከላይ ያነሣናትን ባዕድ እጅ ጉልበት የሰጣት ይሔው የክርስቶስን በጎች ምእመናንን ፈጽሞ የረሳ እና የተወ ኢቀኖናዊ ሹመት ነው ማለት ይቻላል። ይህ ኢቀኖናዊ ድርጊት ቢያንስ ከዚህ በኋላ በፍጹም ሊኖር አይገባውም። ይህ ቀደም ብሎ ተጀምሮ ቢሆን ኖሮ እንዲህ በአንድ ሌሊት 25 ሰው ተሹሞ ሊያድር አይችልም ነበር። ምንም እንኳ ብቸኛ ምክንያቱ ይህ አለመኖሩ ባይሆንም ይህ ጉዳይ እስካሁን ለደረስንበት ውስብስብ ችግር አስተዋጽዖው ከፍተኛ መሆኑ ይታየኛል። ምክንያቱም በዘር የተሾመ በዘር ይሾማል። በፖለቲካም የተሾመ በፖለቲካ ይሾማል። በኮታ የገባ ኮታዬ ከዚህ በላይ ነው ብሎ ማሰቡ አይቀሬ ነው። በአንዱ ተገፍቻለሁ የሚለውም ወደ ሌላው ይጠጋል።
 
3) ጎጠኝነት

በአሜሪካን ሀገር እምነታቸውን ወደ ምሥራቅ ኦርቶዶክስነት የቀየሩ አንድ አሜሪካዊ አባት በአሜሪካ የሚኖሩ የተለያዩ የምሥራቅ ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያንን የአስተዳደር ሁኔታ ይተቻሉ። የሚተቹት አንድ ኦርቶዶክስ ከሆንን እና በአንድ ሀገር ከኖርን ለምንድን ነው የግሪክ፣ የሩሲያ ፣ የሰርቢያ፣ የሮማኒያ፣ ... እየተባባልን የምንለያየው? ለምን በአንድ መንበር እና አስተዳደር ውስጥ አንሆንም የሚለውን ሀሳባቸውን ለማስረዳት ያነሡት ጥያቄ አለ። አትናቴዎስ አሁን ቢመጣ የትኛው ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ነው የሚሔደው? ዮሐንስ አፈወርቅ፣ ባስልዮስ፣ ጎርጎርዮስ፣ ኤፍሬም፣ ... ቢመጡ የትነው የሚሔዱት? እኛስ ማንኛውን ነው የምንጋብዘው ወይም የምንቀበለው የሚለውን ጥያቄ በማንሣት በተለያየ ሀገር እንኳ መከፋፈል እንደሌለባቸው ይሞግታሉ። 

እኛ ደግሞ በአንድ ሀገር እንኳ ሆነን ቅዱሳኑን ሳይቀር የዚህ እና የዚያ አካባቢ እያልን እናቃልላለን። እጅግ እጅግ ምሳሌ የማይግኝለት ጎጥኝነት ውስጥ መኖራችንን መደበቅ አይቻልም። በዚህ ገምተናል፣ ተግማምተናልም። ባለፉት ሹመቶች እንኳ እገሌ ከዚህ አካባቢ ዘር አለበት እየተባሉ ዕጩ ከሆኑበት ሀገረ ስብከት የተተውትን እንዴት መርሳት ይቻላል። ያ መራራ ሒደት ነው ዛሬ ይህን መራራ ውጤት ያመጣው። ዛፉ መራራ ከሆነ ፍሬውም መራራ ነው የተባለው ነዋ እየሆነ ያለው። እነዚህን ችግሮች ፊት ለፊት መግጠም እና ማሸነፍ እስካልቻልን ድረስ እየተነቃቀፍን፣ እየተማማን፣ እየተጠላላን፣ እየተነዋወርን እንደምንጠፋ ምንም ጥርጥር የለውም።  ይህን ሁሉ ለዚህ ከፍታ ያበቃችው ግን ያች ባዕድ እጅ መሆኗን አምናለሁ።  እነዚህ ለዚህች ባዕድ እጅ ጓንትና መሣሪያ ሆነው የሚያገለግሉ ስለሆነ በፍጥነት ካላሻሻልናቸው ውኃ ሲወስድ እያሳሳቀ ነው እንደሚባለው እየተሳሳቅን እና እየተሳለቅን ልንጠፋ እንችላለን።

ድክመቶቻችን አርመን ከችግሮቻችን ወጥተን ለማየት እንድንችል ልዑል እግዚአብሔር በቸርነቱ ይርዳን፤ አሜን።

"መንግሥት ቤተ ክርስቲያንና አባቶችን የመጠበቅ ኃላፊነቱን ካልተወጣ ልጆቻቸው ለመጠበቅ ተዘጋጅተናል፤ በቂ ዝግጅትም አድርገናል።"የመንፈሳዊ ማኅበራትና የኅብረቶች የጋራ መግለጫ

ዛሬ ጥር 16 ምሽት ማኅበረ ቅዱሳን፣ አገር አቀፍ ሰንበት ትምህርት ቤቶች ኅብረት፣ ምእመናን ኅብረት ፣ ጴጥሮሳውያን የቤተ ክርስቲያን ክብርና መብት አስጠባቂ ኅብረት፣ የወጣቶችና ጎልማሶች ማኅበራት ኅብረት በጋራ በወቅታዊ የቤተ ክርስቲያን ጉዳይ ላይ መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫውም የማኅበራቱ ተወካዮች ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ካጋጠማት ታሪካዊ ክስተት አንጻር  ከመቼውም ጊዜ በላይ የቤተ ክርስቲያንን ክብርና ልዕልና የምናስጠብቅበት እና ከአባቶቻችን ጎን የምንቆምበት ወቅት በመሆኑ በኅብረት መክረን አቅጣጫዎችን አስቀምጠናል ብለዋል።

ማኅበረ ቅዱሳንን ወክለው የተገኙት ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ሙሉጌታ ሥዩም በመግለጫው እንደተናገሩት የቅዱስ ሲኖዶስን ልዕልና ያቃለለ የነገ የሐዋርያዊ አገልግሎትን ያሰናከለ በመሆኑ አባቶቻችን ይህንን ያማከለ ውስኔ እንዲወስኑ እንጠይቃለን ሲሉ ገልጸዋል። አክለውም መንግሥት እጁን ከዚህ ሂደት እንዲያነሳ ይልቁንም የእሱ ግዴታ የሆነውን ጥበቃ እንዳያነሳ ይህ ካልሆነ ግን ኦርቶዶክሳውያን ቤተ ክርስቲያን እስከሰማእትነት ለመታደግ የታመኑ ናቸው ብለዋል። ምእመናንም ሳይደናገጡ በጸሎት እንዲተጉ እና ተመሳሳይ ግንዛቤ እንዲኖራቸውም ጥሪ አስተላልፈዋል።

ከመንግሥት ጋርም በቀጣይ ችግሩን እንዲረዳና ቤተ ክርስቲያን የራሷን ችግር በራሷ እንድትፈታ እድል እንዲሰጣት መወያየታቸውን በመግለጽ የዜጎችን ደህንነት ካልጠበቀ ግን ከተጠያቂነት አይድንም ሲሉ ገልጸዋል።

አንድ ያደረገን ድርጊቱ ሕገ ወጥ መሆኑና ሀገርና ቤተ ክርስቲያን የሚንድ በመሆኑ ነው ያሉት ደግሞ አገር አቀፍ ሰንበት ትምህርት ቤቶች ኅብረት ተወካይ አቶ ያሬድ ዮናስ ናቸው። ችግሩን ከማወገዝ ባለፈ ከእኛ የሚጠበቀውን ለማድረግ ተዘጋጅተናል፤በእያንዳንዳችን መዋቅርም ስራዎችን ለመስራትም ተነጋግረናል ብለዋል።

የምእመናን ተወካይ የሆኑት ወ/ሮ ኤልሳ ቤጥ አምዴ በበኩላቸው ውይይት በአንድ ሃሳብና ልብ መከናወኑን ገልጸው ቅዱስ ሲኖዶስ ተደፍሯል፣አባቶች ተደፍረዋል፤ስለዚህም ቤተ ክርስቲያን ካለችበት ችግር ለማውጣት ሁላችንም በቁርጠኝነት ተነስተናል ብለዋል። በውይይታቸውም በቤተ ክርስቲያን ጉዳይ እንደማይደራደሩ አፅንዖት መስጠታቸውን ተናግረዋል።
በቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንና በአባቶች ላይ የተቃጣውን ለመመለስ በአባቶቻችን ጥሪና መመሪያ ተመስርተን ለመሄድ ቃል ገብተናል ያሉት ደግሞ የጴጥሮሳውያን የቤተ ክርስቲያን ክብርና መብት አስጠባቂ ኅብረት ተወካይ አቶ አያልነህ ተሾመ ናቸው። አክለውም ይህ የህልውና ጉዳይ ሀገር የማፍረስ ጉዳይ በመሆኑም ዝግጅት አድርገናል ብለዋል።
የወጣቶችና ጎልማሶች ማኅበራት ኅብረት ተወካይ ወ/ት ፌቨን ዘሪሁን በበኩላቸው ዛሬ በነበረን ውይይት ሁላችንም ከቤተ ክርስቲያን ጎን እንድንሆንና የድርሻችንን ለመወጣት መስማማታቸውን በመግለጽ ለዚህም የአባቶችን መመሪያ እየጠበቁ እንደሆነ ገልጸዋል።
የቅድስት ቤተ ክርስትያንን ወቅታዊ ሁኔታ በተመለከተ በቅዱስ ሲኖዶስ ስብሰባ ተገኝተው ለማስረዳት ዝግጅት መጨረሳቸውንም በመግለጫቸው ገልጸዋል። 
የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊና የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ መንግስት ከለላውን አንስቷል ሲሉ ዛሬ ምሽት መግለጫ መስጠታቸው ይታወሳል።

ከማኅበረ ቅዱሳን ኤፍ ቢ ገጽ

‹‹ኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያንን ህልውና ለመጠበቅና ለፍጹም አንድነቷ ‹አንድ አድርን› blog ወደ ቀደመ ስራዋ የተመለሰች መሆኗን ለማሳወቅ እወዳለን፡፡ ››

 

(አንድ አድርገን ጥር  2015 ዓ.ም) ፡- ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን ጥንታዊት፣ ታሪካዊትና ሐዋርያዊት ቤተ ክርስቲያን እንደመሆኗ መጠን  ኢትዮጵያ አሁን ከደረሰችበት  የእድገት ደረጃ ከመድረሷ በፊት ብራና ዳምጣ፣ ቀለም በጥብጣና ፊደል ቀርጻ  ትምህርት ያስጀመረች፣  የፍትሕ ሥርዓቱ በሀገር አቀፍ ደረጃ መዋቅራዊ አደረጃጀት ሳይኖረው ፍርድ እንዳይጓደልና ደሃ እንዳይበደል በማሰብ የፍትሐ-ነገሥት መምህራኖቿን በዳኝነት መድባ የፍትሕ ሥርዓትን የመሠረተች፣ ዜጎችን በሥነ-ምግባርና በግብረ-ገብነት ትምህርት ኮትኩታ በማሳደግ ሀገር ወዳድ ትውልድ በማፍራት መሠረት የጣለች ቤተክርስቲያን ሆና ሳለ ዛሬ ዛሬ በዘመናችን የምናየው እና የምንሰማው ነገር ‹‹ወርቅ ላበደረ ጠጠር›› በመሆኑ …... ፤  ምዕመና  ስለ  አንዲት  ቅድስት  ቤተክርስቲያንን በሚመለከት ዕለት በዕለት  የሚታየዉ ፤ የወደፊት ስጋት ምን እንደኾነ ኹሉም  የእናት ቤተክርስቲያን ልጆች እንዲያውቁት የበኩላቸውንም መፍትሔ እንዲፈልጉ ፤ ሐሳብ እንዲሰጡ  በክርስትናቸው የሚጠበቅባቸውን ሓላፊነት እንዲወጡ ፤ የክርስቶስን መስቀል ለመሸከም  የማይሰቀቅ ክሣደ ኅሊና አንዲኖራቸው  ለስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮዋ መሳካት ፤ ለኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያን ህልውና መጠበቅና ለፍጹም አንድነቷ እንዲነሡ የበኩላችንን ኃላፊነት እንዲወጡ ‹አንድ አድርን›  blog ወደ ቀደመ ስራዋ  የተመለሰች መሆኗን ለማሳወቅ እወዳለን፡፡ 

Please share 

ከቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ

 ከቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ

Friday, October 21, 2022

ከቅዱስ ሲኖዶስ ጽሕፈት ቤት የተሰጠ መግለጫ

 ጥቅምት ፲፩ ቀን ፳፻ ፲ወ፭ . አዲስአበባ -ኢትዮጵያ

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ በዓመት ሁለት ጊዜ እንደሚያካሂድ ይታወሳል፡፡ይኸውም በወርኃ ጥቅምትና ግንቦት ነው፡፡ በእነዚህ ወራት በመንፈስ ቅዱስ መሪነት ምልዓተ ጉባኤውን በማካሔድ በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ሁለንታዊ ጉዳዩች ወይም መንፈሳዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ አገልግሎቶች ላይ በመምከር ልዩ ልዩ ውሳኔዎችን እንደሚያስተላልፍ ይታወቃል።

ቅዱስ ሲኖዶስ የሚያካሒዳቸው እነዚህ ጉባኤያት በተረጋጋ፣ በሰከነና በተሳካ መልኩ መካሔድ ይችላሉ ዘንድ የሚመለከታቸው አካላት ሁሉ አስፈላጊውን ትብብርና ድጋፍ ማድረግ ይኖርባቸዋል። በተለይም በተለምዶ ጉባኤው በሚካሔድበት ወቅት ልዩ ልዩ አቤቱታዎችን ሕጋዊውን አሠራር ባልጠበቀ መልኩ በግልና በቡድን በመሆን በቅዱስ ሲኖዶስ ጽሕፈት ቤት፣ በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽሕፈት ቤትና በብፁዓን አባቶች ማረፊያ ቤት በመገኘት ማቅረብ ሕጋዊነት የሌለው ተግባር ከመሆኑም በላይ የቅዱስ ሲኖዶስን ጉባኤን የሚያውክ ነው፡፡ በዚህም የተነሣ ፍጹም ተቀባይነትን የሌለው ተግባር መሆኑን ሁሉም ሊያውቀው ይገባል፡፡

አቤቱታና ጥያቄዎች ካሉም በሕጋዊው የቤተ ክርስቲያናችን አሠራር መሠረት መዋቅራዊ አሠራርን በጠበቀ መልኩ ማቅረብ ተቀባይነት ያለውና ሕጋዊ አሠራር ነው፡፡ በመሆኑም ማንኛውም ሕጋዊ አቤቱታና ጥያቄ ያለው ግለስብም ይሁን ተቋም ይህንን አሠራር መሠረት በማድረግ ጥያቄና አቤቱታውን ማቅረብ ይችላል። ይህም የሚሆነው ግን የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ የሚካሔድበትን ወቅት ጠብቆ መሆን የለበትም።