Sunday, April 5, 2020

ይህ ጊዜ እንዲያጥር ፀለዩ

 (አንድ አድርገን መጋቢት 27 2012 ዓ.ም )፡-  ትፈልጉኛላችሁ አታገኙኝም !!!  ማስቀደስ የማንችልበት ጊዜ እንዲያጥር ፀለዩ ፤ አብያተ ክርስቲያናት ተዘግተው የሚቆዩበት ጊዜ እንዲያጥር ፀለዩ ፤ ታቦቱን ከመንበሩ ካህኑን ከደብሩ አንዳይለይብን ፀለዩ፡፡

ቤተ መቅደስ በሌሊት ተገኝቼ ሥርዓተ ከመከታተል ይልቅ እንቅልፍ የመረጥኩበትን እነዚያን ዘመናት ሳስብ ነፍሴ በኀዘን ውስጥ ወደቀችብኝ  ዛሬ በጽኑዕ ብንፈልግ ብንናፍቅም መቅደስ ገብተን ያንን ሰማያዊ ሥርዓት እንከታተል ዘንድ የማንችልበት ዘመን ላይ ቆመናልና አቤቱ ይቅር ይለን ዘንድ ፀልዩ።
በመተላለፋችን ምክንያት አብያተ ክርስቲያናት እንዲህ ሆነው ከማየት በላይ ምን ህማም ይበልጣል? የቤተክርስቲያን ቅጥር በመነኮሳት ሳይሆን በፖሊስ ተከበው ምእመናን እንዳይደርሱ ማየትስ ቅጣት አይደለምን? ይህም ጊዜ እንዲያጥር ፀለዩ፡፡
ይህ የበደላችን፣ የመተላለፋችን የደንዳና ልባችን የማንቀላፋታችን የመራቃችን የመሠይጠናችን ውጤት ነው !!! ዛሬ የዓለም መድኃኒት መድንዓለም ክርስቶስ መጋቢት 27 በታላቅ ድምቀት የቃልኪዳኑ ታቦት ወጥቶ ይነግስ ነበረ እኛም ልጆቹ ለመባረክ መባ ጧፍ ዣንጥላ ዘቢብ እና የቤተመቅደስ ንዋይ ይዘን እንመጣ ነበረ። ዝማሬ እልልታ በካህናቱ ወረብ ውዳሴ ቅዳሴ እናሳልፍ ነበረ ነበር *** " ነበር" ኮሮና ምክንያት ሆኗል በድንገት በሮቹ እንዲህ ተዘግተዋል፡፡

ዛሬ ቅዳሴው ከውስጥ ይሰማል ካህናቱ ያለ ልጆቻቸው ይቀድሳሉ ያለ ቆራቢ ያገለግላሉ እኛ እነሱን እነሱም እኛን እንናፍቃለን በቃ አሁን መሸሸጊያና መጠለያችንን በገዛ ኃጢአታችን አጥተነዋል በሩ ተዘግቷል።

የመከራውን ጊዜ ያሳጥርልን 
#አባት ሆይ በርህን አትዝጋብን !!!


#ይናፍቃል_ለካ?



ማለዳ ተነሥቶ ነጠላን አጣፍቶ በቤቱ መገኘት

የቤተክርስቲያን ደጅ ዝቅ ብሎ መሳም በእምነት ማሻሸት
ሰዓታት ኪዳኑን በጥዑመ ዜማ በካህናት መስማት

#ይናፍቃል_ለካ ተቀብሎ ማዜም በአንድነት በኅብረት።
አሐዱ አብ ተብሎ ቅዳሴን ማስቀደስ
በፍቅር በኅብረት ተሰጥዖን መመለስ
በዕጣኑ መዐዛ በመስቀል መቀደስ
ደጀ ሰላም ገብቶ ፀበል ጸዲቅ መቅመስ

#ይናፍቃል_ለካ በካህኑ መስቀል በእጆቹ መዳሰስ።
እያወክ በድፍረት ሳታውቅም በስህተት
እግዚአብሔር ይፍታህ ለሠራኸው ኃጢአት
መባል በካህኑ ከእሥራት መፈታት