ምንጭ ፡- ሪፖርተር ጋዜጣ (10 Feb, 2016)
የፋሺስት ሰለባው አቡነ ሚካኤል ሐውልትም ወደ አደባባዩ እንዲመለስ ፓትርያርኩ ጠየቁ
‹‹እግዚአብሔር ይፍታችሁ፣ እግዚአብሔር ይፍታችሁ ልጆቼ፣ ለጠላታችሁ ለፋሽስት አትገዙ ልጆቼ፣… እንኳን እናንተ መሬቷም እንዳትገዛ ገዝቻለሁ፣… እመብርሃን ብቻዬን ነኝ ትእዛዝሽ ተቆራኘኝ፣… ምሳሌን የቃል ኪዳኔ ምንጭ አርጊያት፣… አንደበቴን የእውነት ብርሃን አርጊያት፣… ልጆቼ በመንፈስ ጀምራችሁ በሥጋ እንዳታልቁ፣ ለሀገራችሁ በመልካም ፍሬ ፈንታ አሜከላ እንዳትሆኗት፣… ለጠላታችሁ፣… አትገዙ፣… እንኳን እናንተ መሬቷም እንዳትገዛ ገዝቻለሁ፣… ልጆቼ እግዚአብሔር ይፍታችሁ፤››
ከስምንት አሠርታት በፊት በፋሺስት ኢጣሊያ ወረራ ጊዜ አራዳ ጊዮርጊስ አካባቢ በፋሺስቶች የጥይት አረር ሰማዕትነት የተቀበሉት ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ ከመገደላቸው በፊት የተናገሩትን፣ ያስተላለፉትን ቃለ ግዝት በዚያው አደባባይ ላይ ከ80 ዓመት በኋላ ያስተጋባው አርቲስት አብራር አብዶ ነበር፡፡ ከሦስት ዓመት በፊት በባቡር መስመር ዝርጋታ ሳቢያ ተነስቶ የነበረው የሰማዕቱ አርበኛ ጳጳስ - ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ ሐውልት ጥር 29 ቀን 2008 ዓ.ም. በቀደመ ስፍራው ተተክሎ ከመገለጡ በፊት ነበር አብራር አብዶ የጸሐፌ ተውኔትና ባለቅኔ ሎሬት ጸጋዬ ገብረ መድኅን ‹‹ጴጥሮስ ያቺን ሰዓት›› ተውኔት አንዱን ቃለ ተውኔት የተወነው፡፡