Friday, November 14, 2014

‹‹ፈጣሪ አምላክ አገራችንንና ህዝቧን ከጥፋት ይታደግ ዘንድ በጸሎት እንትጋ!!›› የፖለቲካ ፓርቲዎች ለኃይማኖት ተቋማት ያቀረቡት ጥሪ

አንድ አድርገን ህዳር 6 2007 ዓ.ም
አገራችን የክርስትናና እስልምና ኃይማኖቶችን በመቀበል ቀደምት በመሆኗ ብቻ ሳይሆን የኃይማኖቶቹ ተቋማት፣አባቶችና ምዕመናን በመከባበርና መቻቻል አብረው በሠላም በመኖር ለዓለም ህዝብ ተምሳሌት መሆናችን የምንኮራበት ነው፡፡ ለዚህም የቤተ እምነቶቹ አባቶች ለምዕመናኑ ያስተማሩት የሞራልና ሥነ-ምግባር እሴቶችና በአብሮነት ላይ የቆመ የአገር ፍቅር ስሜት፣ እነዚህንም እንዲጠብቋቸውና እንዲያከብሯቸው አርዓያ በመሆን ያደረጉት አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው፡፡
አገራችንና ህዝቧ በተፈጥሮ ሚዛን መዛባት በሚከሰትም ሆነ በአገዛዝ ሥርዓቶች ምክንያት በችግር ውስጥ በሚወድቁበት ጊዜ ሁሉ የእነዚህ ኃይማኖቶች ተቋማትና ምዕመናን መዓቱ እንዲርቅና ምህረቱ እንዲወርድ ፈጣሪያቸውን በጾምና በጸሎት በመለመን/ በመማጸን፣ በሃይማኖታዊ የሞራልና ሥነ ምግባር እሴቶቻቸው መሠረት በመተዛዘን በመረዳዳትና በመተጋገዝ የተገኘውን በመካፈል በአብሮነት ስሜት በርካታ ክፉ ጊዜያትን መሻገራቸው በታሪክ ተመዝግቦ ይገኛል፡፡

ዛሬ ላይ እነዚህ የሞራልና ሥነ-ምግባር እሴቶች እየተናዱ በመሄዳቸው ዜጎች ለማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ምስቅልቅል ተጋልጠዋል፣ የአገር ፍቅር ስሜት በጥያቄ ውስጥ ወድቋል፡፡ በዚህም በመቻቻል ፋንታ ግጭትና መፈናቀል በአራቱም አቅጣጫ ህዝብን ለሥቃይና ሥጋት ዳርጓል፣ የህግ ‹‹አምላክ›› ክብር እያጣ ፍትህ እየተዛባ ነው፣ ወህኒ ቤቶች በታሳሪዎች ተጨናንቀዋል፣ የምግብ ተረጂውና የጎዳና ላይ ተዳዳሪው ዜጋ ቁጥር ተበራክቷል፣በአጠቃላይ የህዝባችን ኑሮና ህይወት፣ የአገራችን ሠላምና መረጋጋት ፈታኝና አሳሳቢ ደረጃ ላይ ናቸው፤ የዜጎች ተስፋ በመናመኑ የህይወት ዋጋ በሚጠይቅ ሁኔታ ውስጥ እየተሰደዱ በባዕድ አገር ለአደጋ እየተጋለጡ ነው፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ ገዢው ፓርቲና ተቃዋሚዎች ተጨባጩን ሁኔታ የሚመለከቱበትና የሚረዱበት መንገድ በሁለት ጫፍ ላይ በመወጠሩ የጋራ መፍትሄ ለማምጣት ያለው ዕድል በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ በመሆኑ ችግሮቹን እያባባሰ ይገኛል፡፡
ስለዚህ፡- በአገራችን ውስጥ በተለያየ ምክንያት በሁለት ጠርዝ ላይ የቆሙ ኃይሎች ወደ ብሄራዊ መግባባትና ዕርቅ እንዲመጡ፣ በህዝብ ውስጥ የሚታየው የሞራልና ሥነምግባር ጉድለት እንዲቃናና የመቻቻልና መተሳሰብ ስሜት እንዲያንሰራራ፣ የዜጎች ሥቃይና ሥጋት ተወግዶ በተስፋ እንዲሞላ፣….፤ በአገራችን መረጋጋትና ዘላቂ ሠላም እንዲሰፍን፣ ቀጣይና ዘላቂ ልማት እውን እንዲሆን፣ አብሮነታችንና አንድነታችን እንዲጠናከር፣ የአገር ፍቅር ስሜት እንዲለመልምና ለሉዓላዊነታችን ያለን ቀናዒነት እንዲጠናከር፣….
በሰንበት ቀናት በጋራ እንዲሁም በየግል የዘወትር ጸሎት ፈጣሪ አምላክን በመለመን ለተያያዝነው አገራዊ ዓላማና የጋራ ጥረት ድጋፋችሁን እንድታደርጉ ለየቤተ እምነት ኃላፊዎች እና ለምዕመናን በሙሉ ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡
ፈጣሪ አምላክ አገራችንንና ህዝቧን ከጥፋት ይታደግ ዘንድ በጸሎት እንትጋ!!

ምንጭ ፡- http://semayawiparty.org/

‹‹No War, No Peace››

ከዓመታት በፊት የኢትዮጵያን ሰብአዊ መብት አከባበር ፤ የፍርድ ቤቶች ነጻነት ፤ በገዥው ፓርቲ እና በተቃዋሚዎች መካከል ያለንና በማኅረሰቡ ውስጥ ያለውን የእርስ በእርስ ተግባቦት ፤ በሕዝቡ እና በገዥዎች መካከል ያለን ክፍተት እና መሰል ጉዳዮችን የተመለከተ አካል ሀገሪቱ ያለችበትን ሁኔታ  በጥቅሉ ሲገልጽ እንዲህ ነበር ያለው ‹‹No War, No Peace in Ethiopia>> ስለዚህ ‹‹No War, No Peace›› የሚያስብል ሁኔታ ላይ የምንገኝ ከሆነ ፈጣሪ አምላክ አገራችንንና ህዝቧን ከጥፋት ይታደግ ዘንድ በጸሎት እንትጋ የሚለው መልዕክት ከሃይማኖት አባቶች ባይመጣ እንኳን ስለ ሀገሪቱ ያገባናል ከሚሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች መምጣቱ መልካም ይመስለናል፡፡ ስርዓቶች ያልፋሉ ፤ መሪዎችም ይሄዳሉ ፤ ትውልድም ይነጉዳል ፤ ሀገር ግን ትቆያለች ......  ይህ ፖለቲካ አይደለም….

No comments:

Post a Comment