Wednesday, September 24, 2014

ቤተክህነት የጥምቀት በዓልን በዓለም ቅርስነት ለማስመዝገብ እንደምትሠራ አስታወቀች

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከሚከበሩት የአደባባይ በዓላት አንዱ የሆነው የጥምቀት በዓል በዓለም ቅርስነት ለማስመዝገብ እንደምትሠራ ቤተ ክህነት አስታወቀች፡፡ 
በጠቅላይ ቤተክህነት፣ የቅርስ ጥበቃና ምዝገባ ቤተ መጻሕፍት ወመዘክር መምሪያ ኃላፊ ቀሲስ ሰሎሞን ቶልቻ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ጥር 11 ቀን በመላው አገሪቱ የሚከበረው የጥምቀት በዓል ከመስቀል በዓል ቀጥሎ ሁለተኛው የዓለም ቅርስ ሆኖ እንዲመዘገብ ሥራ እየተሠራ ነው፡፡ 
ከዋዜማው ጀምሮ እስከ ማግስቱ የሚቆየው የጥምቀት ከተራ በዓል ከመንፈሳዊ በዓልነቱ ባሻገር ባህላዊ ትስስርም ያለው በመሆኑ በዓለም አቀፍ ደረጃ ትኩረት እየሳበ ነው፡፡ 
ለዚህም በዓሉን እንደ መስቀል በዓል ሁሉ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የትምህርት የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) በረቂቅ ባህላዊ ቅርስ (Intangible Cultural Heritage) ለማስመዝገብ የሚመለከታቸው አካላት ትኩረት እንዲሰጡበት የአንትሮፖሎጂና የፎክሎር ባለሙያዎች በየጊዜው የሚያነሱት ነጥብ መሆኑ ይታወቃል፡፡ 
በሌላ በኩል ዘንድሮ የመስቀል ደመራ በዓል በአዲስ አበባና በየክልሉና ዞን ከተሞች በሚገኙት መስቀል አደባባዮች እንደሚከበር የገለጹት ቀሲስ ሰሎሞን ቶልቻ፣ በዓሉ የዓለም ቅርስ ሆኖ በተመዘገበ ከስምንት ወራት በኋላ የሚከበር በመሆኑ ልዩ እንደሚሆን ተናግረዋል፡፡ መስቀል ከሃይማኖቱ ጎን ለጎን ለኢትዮጵያ ብሔረሰቦች የባህል ግንባታ አስተዋጽኦ ማድረጉንም ገልጸዋል፡፡ 

No comments:

Post a Comment