- እንኳን ከዘመን ዘመን (ለዚህ ለ2007 ዓ.ም. ከዘመነ ማርቆስ ወደ ዘመነ ሉቃስ) በሰላም አሸጋገረን፡፡
በዲ/ን ብርሃኑ አድማስ
አንድ አድርገን መስከረም 18 2007 ዓ.ም
ሁለት ዓይነት ጊዜ እንዳለ ቅዱሳት መጻሕፍት ይናገራሉ፡፡ አንደኛውና ይህ ዛሬ "እንኳን ከዘመን ዘመን... " የምንባባልበትና ፍጥረትና ድርጊቱ በቅደም ተከተል የሚሰነዱበት ጊዜ ነው፡፡ ይህንን ጊዜ ከዚህ በኋላ "የፍጥረት ጊዜ" ወይም ታሪካዊ (Historical time) ጊዜ የምንለው ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ከሥነፍጥረትም በፊት በፍጥረትም ጊዜ ከፍጥረት ማለፍም በኋላ የሚኖረውና በፈጣሪ ሕልውና የሚለካው (አስተውሉ እርሱ ራሱ ይለካል እንጂ የፈጣሪን ድርጊት የሚለካ አይደለም) ከአሁን በኋላ "ዘላለማዊ ጊዜ" ወይም እንደኛ ሊቃውንት "ዮም" የምንለው ሌሎቹ በእንግሊዝኛ "የተቀደሰ ወይም ዘላለማዊ ጊዜ" (Sacred time)የሚሉት ጊዜ ነው፡፡ ዮም የግእዝ ቃል ሲሆን ትርጓሜውም ዛሬ ማለት ነው፡፡ ይህ ሁለተኛው ጊዜ በእኛ ሊቃውንት ዘንድ "ዮም" የሚባልበት ምክንያት ከመዝሙረ ዳዊት "እግዚአብሔር ይቤለኒ ወልድየ አንተ፤ ወአነ ዮም ወለድኩከ" ፤ እግዚአብሔር አንተ ልጄ ነህ፤ እኔ ዛሬ ወለድሁህ (መዝ 2፤7)የሚለውን ጥቅስ መነሻ አድርገው ትርጓሜውን ሲያብራሩ እግዚአብሔር ስለ ራሱ የገለጸው የጊዜ መጠሪያ ዮም ወይም ዛሬ መሆኑን ስለሚያመሰጥሩ ነው፡፡ ይህም ማለት በእግዚአብሔር ዘንድ ትናንት እና ነገ፤ አምናና ከርሞ፤ ጥንትና መጪው ጊዜ ወይም ከዚህ ዘመን በኋላ የሚባል ነገር የለም ማለት ነው፡፡