የአንድ ምዕመን አስተያየት
(አንድ አድርገን ሰኔ 30 2006 ዓ.ም )፡- መስቀል ለእኛ ለምናምንበት ድህነትን ያገኘንበት፤ ተለያይተው የነበሩትን እግዚአብሔርና ሰዎችን እንዲሁም ሰዎችና ሰዎችን አንድ ያደረገና ያስታረቀ ለሰው ልጆች ሰላምን፤ ፍቅርን፤ እርቅን፤ አንድነትን ፤ ጽድቅን ያደለ ሁሌም ከልባችን የማይጠፋ ውለታ የተዋለበት ነው፡፡ ይሁንና ጌታ በመስቀሉ ያደለንን ነጻ ስጦታ ገፍተን በማወቅም ሆነ ባለማወቅ በተቃራኒው ጠብንና መለያየትን እያስፋፋን ወደ ከፋ ደረጃ እየሄድን እንገኛለን፡፡
ቤተ ክርስቲያን ባለፉት ዘመናት ብዙ ፈተናዎችና አደጋዎችን አልፋለች፡፡ ይህም ሊሆን የቻለው በእግዚአብሔር እርዳታ አባቶቻቸንንና ምእመኖቿ በጋራ ባደረጉት ከፍተኛ ተጋድሎ የተነሳ ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን ብዙ የምንታወቅበት ነገር ምንም አይነት ልዩነት ቢኖረን ሀገርንና ሃይማኖትን ሊነካ የውጭ ጠላት ሲመጣ ተባብረን አሳፍረን በመመለሳችን ነው፡፡ ይህ የውስጥ አንድነት ለጥንካሬያችን መሰረቱ ነው፡፡