- ኢትዮጵያ እና ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ሃይማኖት ተለያይተው አያውቁም፡፡
- ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን ኢትዮጵያ ከነበራት የቀድሞ ስፋትዋ ቢያንስ አሁን ባለችበት ቅርጽና ይዘት እንድትቆይ በማድረግ ባለውለታ ናት እንጂ ሀገር ያደኸየች አይደለችም፡፡
- ድርሳንና ገድላትን የሚነቅፏቸው ከርዕይ ያልደረሱ ጣዕመ ጸጋ ያልቀመሱ ዐይኑ ግንባር ሆኖ እንደተፈጠረው የጤሜዎስ ልጅ በርጤሜዎስ ግንባር የሆነ ዐይነ ነፍሳቸው በክርስቶስ ጣት ያልተዳሰሰ በመለኮት ምራቅ ያልራሰ ሰዎች ናቸው፡፡
- …. ከባለቤቱ የእግር ሰላም አንዲት ጠብታ እንዳይቀርባት በፍቃዷ ከግብጽ ጳጳሳትን ስታስመጣ ኖራለች፡፡ ያስገደዳት አልነበረም የአባቶቻቸውን ቃል ውሉድ በፍቅር ሲጠብቁት ኑረዋል እንጂ ከግብጻውያን ያገኝችው ትምህርት የለም፡፡
(አንድ አድርገን ሰኔ
9 2006 ዓ.ም)፡-
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ
ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ከሃይማኖቷ ፤ አስተምህሮዋ እና ቀኖና ውጪ የሆኑ ድርጊቶች በመስፋፋት ላይ ይገኛሉ፡፡ ይህን ድርጊት በሚመለከት
መምህር ተስፋዬ ሸዋዬን እንደ አንድ የእምነቱ ተከታይ ግለሰብ ያላቸውን ሃይማኖታዊ አስተያየት ለፎከስ መጽሔት ሰጥተው ነበር፡፡
የዚህንም ቃለ መጠይቅ ምላሽ እንደሚመለከተው አቅርበነዋል፡፡
ፎከስ፡- የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነት መቼ እና እንዴት ተጀመረ?
መምህር ተስፋዬ፡- ኢትዮጵያ ሀገረ እግዚአብሔር የምትባልበት ምክንያት በሦስቱም ሕግጋት ታውቀው ስለነበረ ነው፡፡ እነዚሁ
ሕገ ልቡና ፤ ሕገ ኦሪት እና ሕገ ወንጌል ናቸው፡፡ ሕገ ኦሪት ስትሰራ ኢትዮጵያዊቷ ከሙሴ ጋር ነበረች፡፡
ከእርሷ ወገን የምትቆጠር ንግሥት ሳባም ከሰሎሞን ጋር የነበረውን ጥበበ እግዚአብሔር ለማየት ወደ ኢየሩሳሌም እንደሄደች ከዚያም
ልጇ ሕገ እግዚአብሔር በራሱ በእሳት ጣት የተጻፈበትን ጽላት በዘመኗ እንዳመጣ የሚያገለግሉ ካህናትም አብረው እንደመጡ ተደጋግሞ
የነገለጸ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት በአጸደ ነፍስ ሳለች ባለቤቱ ያላቸውን ባልሰሙ ትውልድ ላይ የመፍረድ ስልጣን የሰጣት ናት፡፡
ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የወልደ እግዚአብሔር ሰው መሆን በኢትዮጵያ ሲጠበቅ
ቆይቷል፡፡ አዳምንና ልጆቹን ከፍዳና ከመርገም ከዘላለም ኩነኔ ሊታደግ በሁለት ወገን ዘላለማዊት ድንግል ከሆነች ከእመቤታችን ከቅድስት
ድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷ ነፍስ ነስቶ በመዋሕድ እንደኛው ሰው ሥጋም ሆኖ በተወለደ በሁለተኛው ዓመቱ ከአዳም በፊት የገነት
በር ለተከፈተለት በቀኙ ለተሰቀለው ሰው ቃል ኪዳን በመግባት በግብጽ
በኩል ወደ ኢትዮጵያ በመጣ ጊዜ መልኩን ዐይታ በሕጻን አንደበቱ ያስተማራትን ትምህርት የሠራላትን ገቢረ ተዓምራት አስተውላና ተረድታ
የባሕርይ አምላክነቱን አምና በክብር አስተናግዳዋለች፡፡ መንፈስ ቅዱስ በጽርሀ ፅዮን በወረደ ጊዜ ለመገኝቷ አቡነ ዘበሰማያት በቋንቋዋ በግዕዝ ተጽፎ መገኝቱ ምስክር ነው፡፡ ከዚያን
ጊዜ ጀምሮ ኢትዮጵያ እና ኦርቶዶክሳዊት
ተዋሕዶ ሃይማኖት ተለያይተው አያውቁም፡፡




