Friday, May 10, 2013

የአሰበ ተፈሪው አጥማቂ

(ይህ ጽሁፍ በአሰበ ተፈሪ ተከስቶ የነበረውን አጥማቂ ብቻ ይመለከታል)

(አንድ አድርገን ግንቦት 2 2005 ዓ.ም)፡- የዛሬ ሁለት ዓመት አንድ ሰው ከሰሜኑ ክፍል ይነሳና የማጥመቅ ስራውን እያከናወነ  ወደ ምስራቅ ክፍል ሐረር መንገድ አሰበ ተፈሪ ጉዞውን ይቀጥላል፡፡ አሰበ ተፈሪ ሲደርስ የማጥመቅ ጸጋ እንዳለው ለቤተ ክርስቲያን አባቶች እና ለአካባቢው ሊቀ ጳጳስ አስረድቶ ፤ የማጥመቅ አገልግሎት እንዲሰጥ ህጋዊ ፍቃድ አግኝቶ ሰዎችን ሊያጠምቅ ስራውን በይፋ ይጀምራል፡፡ ቅዳሜ እና እሁድ ከቅዳሴ በኋላ ስራውን ሲጀምር ለመጠመቅም ሆነ ለመመልከትም የመጡ ሰዎች እያጓሩ ፤ እየጮሁ ፤ ሌሎች እንደሚያደርጉት መውጣት ጀመሩ ፡፡ መንፈስ ተብዬው ሲለፈልም ‹‹ሟርት ነኝ›› ፤ ‹‹መተት ነኝ›› ፤ እገሌ ነኝ ማለቱን ቀጠለ፡፡ ማነው ያደረገብህ ? ተብሎ ሲጠየቅ ፤ የሚታዘዘው መንፈስ የደብሩን አስተዳዳሪ ፤ ቄሶችን ፤ ዲያቆናትን ፤መምህራንን ስም መጥራት ተያያዘው ፡፡ እዛ ያለው ሰው ግራ ገባው ፤ ግማሹ ‹ይሄ ሰውዬ ትክክለኛ እጥማቂ አይደለም ፤ እነዚህን ዲያቆናትና ፤መምህራንን  እናውቃችዋለን ንፁህ ናቸው›› ሲል ፡፡ ሌላው ክፍል ደግሞ ‹ያው መንፈሱ እኮ ተናገረ ፤ ከዚህ በላይ ምስክር አያሻንም›› ብለው ስማቸው የተጠራውን ቀሳውስ ዲያቆናት ፖሊስ አስጠርተው አፍሰው እስር ቤት ከተቷቸው፡፡ ይህ ሰው መሰል ተግባሩን በተለያዬ ቦታዎች ውስጥ እየዞረ በመስራት መሰል ነገሮች በሶስት ቤተ ክርስትያኖች ላይ ተከሰተ፡፡ ቀሳውስቱ ፤ዲያቆናቱ ሁሉም ዘብጥያ ወረዱ፡፡
ቤተ ክርስቲያን ማን ይቀድስ? ማንስ ቀድሶ ያቁርብ?  ነገሩ በጣም አስቸጋሪ ሆነ የአካባቢው ምእመን እነዚህን ቀሳውስቱንና ዲያቆናቱን ደግመን ማየት አንፈልግም ስላለ የአካባቢው ሀገረ ስብከት አስተዳዳሪ ሊቀ ጳጳስ  መንፈሱ መሰከረባቸው የተባሉትን አባቶች ወደመጡበት ማሰናበት እና አዲስ አገልጋዮችን በማምጣት ሂደት ውስጥ ከአንድ ወር በላይ ቤተክርስትያኑ ተዘጋ ፤ አገልግሎቱም ተስተጓጎለ፡፡ ይህ በእንዲህ እያለ ይህ ሰው ብር መሰብሰቡን ማጥመቁን የከለከለው አካል አልነበረም፡፡ አንዳንድ ቦታ ላይ እሱን ለመጋበዝ እስከ 7000 ሺህ ብር ድረስ ከምዕመናን ይሰበሰብ እና ይጋበዝ ነበር፡፡ እዛው አካባቢ ያሉ አብያተ ክርስቲያናት በጧፍ እጥረት አገልግሎቱ ማከናወን ሲገዳደራቸው እየተመለከቱ ለአንድ ህገ ወጥ አጥማቂ ግን 7000 ብር በቀናት ጊዜ ውስጥ እንዴት መሰብሰብ እንደቻሉ ለተመለከተ ይገረማል

ይህ በእንዲህ እያለ ሰውየው ሌላ ቦታ ላይ ተጋብዞ ለማጥመቅ ሄደ፡፡ እዚያ ቦታ ላይ ደግሞ የተከሰተው ነገር ከአሰበ ተፈሪው የተለየ ነበር፡፡ ቤተ ክርስቲያኗ ባልታወቀ ምክንያት ከዓመታ በፊት ተቃጥላ ነበር ፤ የአካባቢውም ምዕመን በቻለው መጠን የበፈት ይዞታዋን ሳትለቅ እንደገና መስራት ችሎ ነበር ፡፡ ይህ ‹‹አጥማቂ›› ነኝ ባይ እዚች ቤተ ክርስቲያን ላይ እያጠመቀ ሳለ አንዱ መንፈስ የያዘው ሰው ይነሳና መለፍለፍ ይጀምራል፡፡‹‹ቤተ ክርስቲያኗን ያቃጠላት መምህሬ እገሌ ነው›› ብሎ መሰከረ፡፡ ሰው እውነት መስሎት ያን መምህር ካልገደልነው ብሎ ተነሳ፡፡ በመሀል አንድ አባት ይነሱና እረፉ ‹መንፈስን ሁሉ አትመኑ›› ነው የተባለው፡፡ አንተም ማጥመቅህን አቁም ፤ ‹‹በችግር የተያዙትን እስራታቸውን እግዚአብሔር ይፍታ ስንል አንተ ደሞ ሌላ ብጥብጥ አመጣህብን›› ብለው በሰላም ሸኙት፡፡ 
ለቤተ ክርስትያን መቆርቆራች ባልከፋና ጥሩ ሆኖ ሳለ እንዴት እንደምናስብላት አለማወቃችን ደግሞ ሌላ ችግር እየፈጠርን መሆኑን ተገንዝበነው አናውቅም፡፡  አሁንም የአካባቢው ሰው አቃጠለ የተባለውን መምህር ይዘው ለፖሊስ አስረከቡ ፡፡ ፖሊስም እስኪጣራ ብሎ መምህሩን አሰረው ፤ ፖሊስ ምንም አይነት ተጨባጭ ማስረጃ ስላላገኝ መምህሩን ፈትቶ ሀገር ለቆ እንዲሄድ ያሰናብተዋል፡፡ ህዝቡም አይንህን እንዳናይህ ቤተክርስትያናችን አቃጥለህብን  ብለው ‹‹አይንህ ለአፈር›› አሉት፡፡
ይህ ሁሉ እየሆነ ማስተዋል የሚችል ሰው በመጥፋቱ በሌላ ጊዜ ፤ ሌላ ቦታ ላይ ሰውየው መንፈስ ያወጣል ፤ ተዓምረኛ ነው ሲባል የሰሙ ምዕመኖች ይምጣልን ብለው የጠየቃቸውን ብር ከማህበረሰቡ ላይ ፤ ከሀላፊ አግዳሚው ላይ መሰብሰብ ይጀምራሉ ፡፡ አሁንም የዚህ ሰውዬ ማንነት ለማወቅ ሰው አይነ ልቦናው አልበራለትም ነበር  ፤ ራሱ መተተኛ በመተት የተያዘ ሰው እፈታለሁ ፤ ከዲያቢሎስ ቁራኛነት እገላግላችዋለሁ ብሎ ማወራቱን ማጥመቁን ተያይዞታል ፡፡ አባቶች እዚህ ጋር ተሰብስበው መከሩ ፡፡ እንቢ አይመጣብ ቢሉ ‹‹የራሳችሁ ጉድ እንዳይወጣባችሁ›› ነው ይባላሉ ፤ ይምጣ ቢሉ ደግሞ ቤተክርስትያኗን ፈትቶ ፤ ያሉትን ካህናት እንዲባረሩ አድርጎ ምዕመኑን ለሌላ እምነት አሳልፎ ሊሰጥ ነው፡፡ ግራ የሚገባ ነገር ሆነ ፡፡ አባቶች ተሰብስበው መከሩ እንዲህም አሉ ፡- በሚቀጥለው ‹‹ እሁድ ጠዋት መምጣት ይችላል ፤ ነገር ግን እኛ ለሊቱን ሙሉ የገብርኤልን ፤ የሚካኤልን ፤ ሁሉን ድርሳናት እንድገም ፤ ሙሉ ዳዊት ደግመን ጸሎት እናድርግ ፤ መልካ መልኮችን እናድርስ ፤ ከዛ እኛ በማኅበር ሆነን ባደረግንበት ፀበል እሱ መጀመሪያ ይጠመቅ ፤ ከዛ እኛ ሁላችንም እንጠመቃለን ፤ ከዛ ምዕመኑን ያጠምቃለል ›› ብለው ቃለ ጉባኤ ይዘው ተፈራርመው ፤ ወስነው ስብሰባን ዘጉ፡፡ 

አጅሬ ለካ ምን እንደተባለ መንፈሱ ይንገረው ማን ይንገረው አልታወቀም፡፡ ቅዳሜ ለእሁድ አጥቢያ በህብረት ሆነው ቃል የገቡትን አድርገው ቢጠብቁት ቢጠብቁት ሊመጣ አልቻለም፡፡ በቃ እሺ ብለው ሌላ ቀጠሮ ያዙለት ፤ አሁንም ሊመጣ አልቻለም ፡፡ የቀረበትን ምክንያት ሲጠይቁት ተልካሻ ነገር ነገራቸው፡፡ ይገርማል !!!! ሰዎች ቀስ እያሉ የሰውየው ማንነት ስለገባቸው ገፍተው ከአካባቢው አባረሩት፡፡ ይህ ሰው ይህን አይነት ስራ ደቡብ አካባቢ ሲሰራ ሌባና አጭበርባሪ መሆኑ ታውቆ በእስር ቤት እንደሚገኝ ከጊዜ በኋላ ሰማ፡፡ እኛ ይህ ሰው በአንድ ቦታ ላይ ብቻ ያደረገውን ብቻ እናውቃለን ፤ በፊት ምን ያህል ቤተ ክርስቲያን ይበትን? ፤ አሁን ምን ይስራ? ፤ በአሁኑ ሰዓት ምንም የምናውቀው ነገር የለም፡፡
እኛ አይናችን ታውሯል ፤ እናያለን አናስተውልም ፤ እንሰማለን አናዳምጥም ፤ በቃ እንደዚህ ነን፡፡ እነሱም እየዞሩ ቤተ ክርስቲያን ያፈርሳሉ ፤ ቤቱን ይፈታሉ ፤ ተከታዮች ያፈራሉ ፤ በሲዲ አድርገው አቀነባብረው ለኛው ይሸጡልናል ፤ እኛም ‹‹ይገርማል›› እያልን እናያለን፡፡ ስራቸው ሳይሆን የሚገርመው እኛ ነን የምንገርመው፡፡
የአካባቢው አባቶች ጠይቀን እንደተረዳነው ፡- ‹‹ይህው እሱ በዚያን ጊዜ አጠምቃለሁ ብሎ ውሀ የረጨባቸው ሰዎች አሁንም ይጥላቸዋል ፤ ምን እንዳሰፈረባቸው እግዚአብሔር ይወቀው ፤ እሱ ሳይመጣ በፊት ጤነኞች ነበሩ ፤ እሱ ካጠመቃቸው በኋላ ግን በሽታ ላይ ጥሏቸው ሄደ ፤ አንዳንዶቹ ቤተክርስትያን እየመጡ እየተጠመቁ እየተሸላቸው ነው ፤ አንዳንዶቹ ግን አሁን በሽተኞች ናቸው››  ብለው ነበር የነገሩን ፡፡ ይህን ሲነግሩን ያለንበት ጊዜ ምን ያህል አስቸጋሪ መሆኑን ነው የተረዳነው፡፡
በቅርብ ጊዜ ደብረ ብርሐን ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን አዲስ አጥማቂ መጥቷል ተብሏል.. እስኪ ነገሩን አጣርተን እንመለሳለን

Wednesday, May 8, 2013

በቡሌ ሆራ ቅድስት አርሴማ ቤተ ክርስቲያን እንድትፈርስ መታዘዙ ቁጣን ቀሰቀሰ


(ኢትዮ-ምህዳር ጋዜጣ ሚያዚያ 29 2005 ዓ.ም)፡-  በኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ቦረና ዞን ቡሌ ሆራ(ሀገረ ማርያም) ከተማ የምትገኝው ቅድስት አርሴማ ቤተ ክርስቲያን እንድትፈርስ መታዘዙ በአካባቢዋ ቁጣ መቀስቀሱ ታወቀ፡፡ የአካባቢ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያ አማኞች  ለዝግጅት ክፍላችን እንደገለጹት “የከተማዋ ከንቲባ ኃላፊነት በጎደለው እና በማን አለብኝነት ቤተክርስቲያኑን አፍርሰው ቦታውን ለባለሀብት ለመሸጥ መወሰናቸው ለሃይማኖቱም ሆነ ለሕዝቡ ያላቸውን ንቀት ያሳዩበት ነው” ሲሉ አውግዘዋል፡፡የአካባቢው ነዋሪዎች አሁን የወሰዱት አቋም ሲገልጹ ‹‹የከተማው ከንቲባ  በድፍረት ቤተክርስያኑን አፍርሰው እንጨትና ቆርቆሮውን እንድናነሳ አዘዋል ፤ እኛም የእግዚአብሔርን ቤት አናፈርስም ፤ እሳቸው ከፈለጉ በሚፈልጉት ኃይል ሊያፈርሱ ይችላሉ  ፤ ለወረዳው አስተዳደር አመልክተን የወረዳው አስዳዳሪ በቦታው በመገኝት ተመልክተውልናል፡፡ ቤተክርስቲያ እንዳይፈርስ የሚያስችለውን ውሳኔ ይሰጣሉ ብለን ተስፋ እናደርጋለን›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡
አስተያየት ሰጪዎቹ በመጨረሻ እንደተናገሩት በዚሁ ከተማ የቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ያለ ሲሆን ይህን ቤተክርስቲያን  ካለፈው መንግሥት ጀምሮ  በከተማው ማስተር ፕላን መሰረት ፍቃድና ካርታ አለው ፤ ይሁን እንጂ እኚህ የከተማው ከንቲባ ቦታውንና ከቦታው ላይ ያለውን ባሕር ዛፍ አላስረከብንም ብለው ችግር ፈጥረውብን እስከ አሁን ድረስ ችግሩ ባልተፈታበት ሁኔታ እንደገና አሁን ደግሞ ፊታቸውን ወደ ቅድስት አርሴማ ቤተ ክርስቲያን መዞራቸው አግራሞትን ፈጥሮብናል ብለዋል፡፡ የከተማው ከንቲባ አቶ ቡሉ ገመዳ በጉዳዩ ላይ አስተያየት እንዲሰጡ በተንቀሳቃሽ ስልካቸው እና በጽ/ቤታቸው ስልክ ለማግኝት ያደረግነው ሙከራ አልተሳካም፡፡
ኢትዮ-ምኅዳር ጋዜጣ ሚያዚያ 29 ቀን 2005 ዓ.ም

Monday, April 29, 2013

ዘሰሙነ ሕማማት




(አንድ አድርገን ሚያዚያ 21 2005 ዓ.ም)፡- ሰሙነ ሕማማት በነብዩ ኢሳያስ ‹‹ነስአ ደዌነ ወፆረ ሕማመነ ፤ በእውነት ደዌአችንን ተቀበለ፤ ሕማማችንንም ተሸከመ ፤ እኛ ግን እንደተመታ ፤ በእግዚአብሔር እንደተቀሰፈ ቆጠርነው፡፡ እርሱ ግን ስለመተላለፋችን ቆሰለ ፤ ስለበደላችን ደቀቀ ፤ የደኅንነታችንም ተግሳጽ በእርሱ ላይ ነበረ ፤ በእርሱም ቁስል እኛ ተፈወስን›› ኢሳያስ 53 ፤4 ተብሎ የተነገረው ቃል ተፈጽሞ ፤ ጌታችን ለድኅነተ ዓለም ሲል በአጭር ቁመት በጠባብ ደረት ተወስኖ የተቀበለውን ጸዋትወ መከራ የሚዘከርበት ሳምንት ነው፡፡ ከሆሳህና ማግስት እስከ ትንሳኤ ያለው የጾመ እግዚእነ መዝጊያ ሳምንት ሰሙነ ሕማማት ይባላል፡፡ 


በማኅበረ ቅዱሳን የሚታተመው የስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ ልዩ የ2004 ዓ.ም እትም ስለ ሰሙነ ሕማማት ፤ ሥርዓተ ሰሙነ ሕማማት ፤ ሃይማኖታዊና ትውፊታዊ ክንዋኔዎች በሰሙነ ሕማማት ፤ ሕማማተ እግዚእነ በልሳነ አበው ፤ በሰሙነ ሕማማት የሚነሱ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው ፤ መጽሐፈ ግብረ ሕማማት እና ፍኖተ መስቀል በሚል አብይ አርዕስቶች የተከፋፈለ ባለ 30 ገጽ ትንሽ መጽሐፍ አሳትሞ ነበር ፡፡ አንድ አድርገን ይህን መጽሐፍ በዚህ ወቅት ማግኝት ላልቻሉ በሀገር ውስጥም ሆነ ከሀገር ውጪ ለሚኖሩ ምዕመናን ወደ ፒዲፍ በመቀየር አቅርባላችኋለች ፡፡ በርካታ እውቀትን ይገኙበታል ያንብቡት…

የሳምንቱ የአንድ አድርገን ስጦታ

አርቲስት ጀማነሽና ግብር አበሮቿ ዘብጥያ ወረዱ


(አንድ አድርገን ሚያዚያ 21 2005 ዓ.ም )፡- ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ራሳቸውን ማህበረ ስላሴ ደቂቀ ኤልያስ የሚል ስም በመስጠት ሲንቀሳቀሱ የነበሩት ሰዎች ባሳለፍነው ሳምንት ውስጥ በተነሳባቸው ተቃውሞ ምክንያት ዘብጥያ ሊወርዱ ችለዋል ፤ አራት ኪሎ አካባቢ በተከራዩት አዳራሽ አማካኝነት ከምሽቱ አንድ ሰዓት እስከ ውድቅት ለሊት ድረስ በሚያካሂዱት ጉባኤ መሳይ ስብሰባ የአካባቢው ማህበረሰብ ስራቸውን በመቃወማቸው  ፤ ሰላማችንን አሳጡን በማለት ለፖሊስ በማመልከታቸውና ይህን ተከትሎ በተነሳው ውዥንብርና ግርግር ፖሊስ አርቲስት ጀማነሽን ፤ አንድን የእምነቱን ፈልሳፊ ሰው እና ቤቱን ለመስብሰቢያ ያከራየውን ሰው እስር ቤት ሊያስገባቸው ችሏል፡፡

Tuesday, April 23, 2013

‹‹ተዓምሯን አንቀብርም›› በሚል አርዕስ ታላቅ የቅኔ ምሽት ተካሄደ ፤ ከእሳት የተረፉት ንዋየ ቅድሳትም ለምዕመኑ ለእይታ ቀረቡ

(አንድ አድርገን ሚያዚያ 15 2005 ዓ.ም)፡- በአጉስታ ደብረ ጽዮን ቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያን “ተዓምሯን አንቀብርም”በሚል አርዕስ ታላቅ የቅኔ ምሽት ባሳለፍነው እሁድ ሚያዚያ 13 2005 ዓ.ም የመንፈሳዊ ኮሌጅ መምህራን ፤ ታላላቅ የቅኔ ድጓ እና የአቋቋም ምሁራን በተገኙበት ተካሄደ፡፡ በጊዜው የደብሩ ሰበካ ጉባኤ እና የስብከተ ወንጌል ጽ/ቤቱ አንድ ላይ ሆነው ባዘጋጁት መርሀ ግብር ላይ በርካታ አዲስ አበባ ውስጥ አሉ የሚባሉ በተለያዩ የአገልግሎት ዘርፎች በቤተክርስቲያኒቱ ውስጥ የሚያገለግሉ ሊቃውንት ተገኝተዋል፡፡ የጉባኤው ዋናው ዓላማው ከእሳት ቃጠሎ የተረፉ ንዋየ ቅድሳትን ለምዕመኑ ለማሳየት መሆኑ ለማወቅ ተችሏል፡፡ በጉባኤው ላይ በቦታ ሄደን እንደተመለከትነው ባየነው ነገር እጅግ ተገርመናል ፤ የእግዚአብሔርንም ተዓምር አድንቀናል ፤ ከእሳት ቃጠሎ የተረፉ በቦታው ላይ የተደረገው የእግዚአብሔርን ተዓምር የሚመሰክሩ በርካታ መጻህፍት ፤ ወደ ዘጠኝ የሚጠጉ የእንጨት መስቀሎች ፤ መጎናጸፊያ እና መሰል በርካታ ንዋየ ቅድሳትን ለመመልከት ችለናል፡፡ በጊዜው የተገኝው የጉባኤው ተካፋይ ምዕመን በሁኔታ እጅጉን መገረሙን ሲገልፅ አስተውለናል፡፡ የመርሀ ግብሩ አስተባባሪና የደብሩ የቁጥጥር ክፍል ኃላፊ መጋቢ ስርዓት ያዕቆብ እንደገለጸው የእመቤታችን ተዓምር እዚህው ተቀብሮ መቅረት ስለሌለበት ወደፊት ቦታውን የረገጠ ምዕመን ሁሉ ይመለከተው ዘንድ ግቢው ውስጥ ትንሽ ሙዚየም በሰበካ ጉባኤው አማካኝነት በማሰራት ከእሳት የተረፉትን ንዋየ ቅድሳት በውስጡ ለማስቀመጥ እንደታሰበ ገልጿል፡፡በተጨማሪም በአሁኑ ሰዓት ምዕመኑ በዚህ ሳምንት ውስጥ እስከ ሚያዚያ 21 2005 ዓ.ም ድረስ በቦታው ላይ በመገኝት ተዓምሯን ይመለከት ዘንድ አስጎብኚ በመመደብ በደብሩ ቅጥር ግቢ ውስጥ የማሳየት ተግባር እየተከናወነ ይገኛል ፤ እነዚህን ንዋየ ቅድሳት በቪዲዮ የተቀረጹ ሲሆን በቅርብ ቀንም ቦታው ላይ ድረስ ሄደው መመልከት ላልቻሉት ምዕመናን ለማድረስ መታሰቡን ለማወቅ ችለናል፡፡

የተቀረጸው ቪሲዲ ሲለቀቅ ለተመልካች ለማቅረብ እንሞክራለን

ስለ ሁኔታው የተሻለ መረጃ ለማግኝት እና ለተጨማሪ ጥያቄዎች የደብሩን ቁጥጥር ክፍል ኃላፊ መጋቢ ስርዓት ያዕቆብ በዚህ  ቁጥር ማግኝት ይችላሉ፡፡
0912-629177

‹‹በውጭ ሲኖዶስ ሠራን የሚሉት ከአቡነ ጳውሎስ የባሱ ፥ ሃይማኖትን ጭራሽ የቀየሩ፣ ኃይማኖትንም የሚሳደቡና ከእግዚአብሔር መንገድ የወጡ ሰዎች ናቸው››


ከዚህ በፊት የተለያዩ ሰዎችን አስተያየት ብሎጋችን ላይ ምንም አይነት ማስተካከያ ሳናደርግ እንደወረደ ለአንባቢዎች ማቅረባችን ይታወቃል ፤ ከእነዚህ ጸሀፊዎች አንዱ የሆነውን የሰዓሊ አምሳሉ ሶስት ጽሁፎች ይጠቀሳሉ ፤ የሰዓሊ አምሳሉን ፅሁፍ መልስ የሚሆን ጽሁፍ ከሀገር ውጪ ከሚኖር ኃይለሚካኤል ከሚባል አንባቢ ስለደረሰን ጽፉን እንዲህ በማድረግ ለአንባቢያን አቅርበነዋል፡፡

(አንድ አድርገን ሚያዚያ 15 2005 ዓ.ም)፡- ሰዓሊ አምሳሉ ገብረኪዳን አርጋው የተባለ ሰው ባለፈው አንድ ሰውፖለቲከኛ ነው” ሲለው ለካ አውቆት ኖሯል። እኔ እኮ ምንም የእውቀት ችግር እንደነበረበት ባውቅም ከልቡ ለቤተክርስቲያን የሚያስብ ሰው መስሎኝ ነበር። በመጀመሪያ ባለፈው ጊዜ አምሳሉ ፓለቲከኛ ነው ሲል የተቃወምኩትን ሰው ይቅርታ እጠይቃለሁ። ከዛ በተረፈ ግን የአንድ አድርገን ብሎግ አዘጋጆች ከዚህ በታች ያለውን አስተያየት ለአንባቢያን ታደርሱልኝ ዘንድ እጠይቃለሁ።

በአዲስ አበባ 3 ዓመት አገልግሎት ሲሰጥ የነበረው የቅዱስ ሩፋኤል ቤተክርስቲያን ቦታ የኢንደስትሪ ዞን ነው በማለት ፈረሰ



(አንድ አድርገን ሚያዚያ 15 2005 ዓ.ም)፡- በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 11 የሚገኝው የቅዱስ ሩፋኤል ቤተ ክርስቲያን በኢንደስትሪ ዞን ላይ የተሰራ ነው በሚል የወረዳው ዋና ስራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት ለቅዱስ ሲኖዶስ በጻፈው ደብዳቤ 24 ሰዓት ሳይሞላው ማፍረሱን የደብሩ ኃላፊዎች አስወቁ፡፡

ሚያዚያ 9 ቀን 2005 ዓ.ም ከምሽቱ አንድ ሰዓት ሲሆን የወረዳው ዋና ስራ አስፈጻሚ ኤልሳቤት መንግስቱ የደብሩን ኃላፊዎች በጽ/ቤታቸው እንዲገኙ የስልክ ጥሪ በማድረግ ቤተክርስቲያን እዲያፈርሱ የነገሯቸው መሆኑን ያስረዱት የደብሩ ኃላፊዎች ቤተ ክርስቲያን የማፍረስ ስልጣን  የእነሱ አለመሆኑን በመግለጻቸው በማግስቱ ጠዋት 3 ሰዓት ወረዳው ለሲኖዶስ የላከው ደብዳቤ ይዘው ከወረዳው ተወካይ ጋር በሲኖዶስ ተገናኝተው እየተወያዩ ሳለ የወረዳው ዋና ስራ አስፈጻሚ በሶስት መኪና ፖሊስ በመታገዝ በሕገ ወጥ መንገድ እንዲፈርስ ማድረጋቸው የደብሩ ኃላፊዎች  አስታወቁ፡፡