Monday, December 31, 2012

ለእርቀ ሰላም የመጡትን ተወካይ በመንግስት የደህንነት ሰዎች አማካኝነት ወደ መጡበት እንዲመለሱ ተደረገ

(አንድ አድርገን ታህሳስ 23 2005 ዓ.ም)፡- የእርቀ ሰላሙ ኮሚቴዎች እርቁ ዳር እንዲደርስ ጊዜያቸውንና ጉልበታቸውን በመሰዋት ከፍተኛ እንቅስቃሴ እያደረጉ መሆኑ ይታወቃል ፤ ቤተክርስቲያን ከነበረችበት መከፋፈል ወደ አንድ እንድትመጣ በሁለቱም ሲኖዶሶች መካከል በመሆን የንግግር መንፈሱ እንዲጀመርና በአባቶች መካከል ያለው ያለመነጋገር እና ያለመወያት መንፈስ እንዲርቅ አድርገዋል፡፡  ከቀናት በፊት ከአሜሪካ የእርቀ ሰላም ኮሚቴውን በመወከል አዲስ አበባ የመጡት ሊቀ ካህናት ኃ/ሥላሴ አለማየሁ በመንግስት የደህንነት ሰዎች አማካኝነት ወደ መጡበት እንዲመለሱ ተደርጓል ፡፡ ከቀናት በፊት የፌደራል ጉዳዮች የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ለፋና ብሮድካስት በሰጡት አስተያየት “መንግሥት በኦርቶዶክስ ተዋህዶ ፓትርያርክ ምርጫ እና እርቀ ሰላሙ ላይ እጁን አላስገባል ፤ በየ ድረ-ገፅ የሚወራው ወሬ ሀሰት ነው ፤ ሕገ መንግሥቱ መንግሥትና እምነትን ስላለያየ መንግስት በእምነቶች ላይ ጣልቃ አይገባል” በማለት ተናግረዋል ፡፡ የቅዱስ ሲኖዶስ ጸሀፊም “መንግስት በመካከላችን ጣልቃ አልገባም ፤ ጭራሹን አልደረሰብንም ፤ የሚወራው ወሬ ሀሰት ነው” በማለት አስረድተዋል፡፡ አቡነ ሕዝቅኤል ለእርቀ ሰላም የመጡት አባት በማን አማካኝነት ከሀገር እንዲወጡ ስለመደረጉ ተጠይቀው ለአሜሪካ ድምጽ በሰጡት መልስ “ መምጣታቸውን እናውቃለን ፤ በአካልም አግኝቼ አናግሬአቸው ነበር ፤ በምን ምክንያት እንደተመለሱ ግን የማውቀው ነገር የለም ፤ ነገ ስለምንሰበሰብ ቅዱስ ሲኖዶስ ይነጋገርበት ይሆናል” ብለዋል፡፡ አሁን ግን እየተደረገ እና እየተወራ ያለው ነገር ምዕመኑን ይባስ ግራ መጋባት ውስጥ እየከተተው ይገኛል፡፡ አባቶቻችን መንግስት ጣልቃ አልገባም ብለው በአደባባይ ሲናገሩ ፤ መንግስት ደግሞ ለእርቀ ሰላሙ የመጡትን አባት ወደ መጡበት ወደ አሜሪካ እንዲመለሱ ቲኬት ቆርጦ እንደሰጣቸው ለማወቅ ተችሏል፡፡ መንግሥት የቀጣይ ፓትርያርኩን ምርጫ በቅርበት ሆኖ የሚከታተል ኮሚቴ በፌደራል ጉዳዮች ሚኒስቴር አማካኝነት እንዳቋቋመ ከወር በፊት መጻፋችን ይታወቃል፡፡ ( ይህን ይጫኑ )አሁን በግልጽ እየታየ ያለው ነገር ቢኖር መንግሥት ከአሜሪካ በሚመጡት አባቶች ወይም በእርቀ ሰላሙ ላይ ፍላጎት እንደሌለው ነው ፤ ይህ የእርቀ ሰላም ጉዳይ ያለ መንግሥት መልካም ፍቃድ ጫፍ የማይደርስበት ሁኔታ እየተስተዋለ ነው ፤  የውጭ ጫናዎች እንዳሉ ሆነው አባቶች ያላቸውን አቅም አሰባስበው የውስጥ ስምምነታቸውን አጠንክረው በአንድ አቋም እና በአንድ ሀሳብ ለቤተክርስቲያኒቱ የተሻለው ሁሉ ቢያደርጉ መልካም ነው እንላለን፡፡ እድሜም ይገፋል ፤ ስልጣንም  ያልፋል ፤ ሞትም ይፈጥናል  ትውልድ ግን ይቀጥላል ፤ በትውልዱ የምትወቀሱበት ስራ እንዳትሰሩ እግዚአብሔር ይርዳችሁ፡፡

Thursday, December 27, 2012

የአቶ ስብሀት ነጋ ቅዥት





  • “ስብሓት ነጋ ቤተ ክርስቲያን ልትበታተን እንደምትችል አስጠንቀቁ!!”  ሀራዘተዋህዶ


(አንድ አድርገን ታህሳስ 18 2005 ዓ.ም)፡- “ስብሀት ነጋ ቤተክርስቲያን እንደምትበታተን አስጠነቀቁ” በማለት አንድ ጽሁፍ ሀራ ዘተዋህዶ ላይ አነበብን ፤ አቦይ ስብሀት  ቤተክርስቲያኒቱ ሃገራዊ ግዴታዋን ስትወጣ የነበረች፣ ለወደፊቱ ታላቅ ሚና ሊኖራት የሚችል ስለኾነች አሁን የት አለች ብለን እናስብ በማለት የአቡነ ጳውሎስ ሞት በኋላ በቤተክህነት አዳራሽ በተቀመጠው ደብተር ላይ ጽፈዋል ፤ ሰውየው አንዳንድ ጊዜ እንደ ነብይ ያደርጋቸዋል ፤ አንዳንዴ ደግሞ በትህምክት ባህር ውስጥ የሰመጡ ትህምክተኛ ሆነው ሳለ “ትምክተኞች” ብለው መናገር ይዳዳቸዋል ፤ አንዳንዴም አይምሮውን ያጣ ሰው ይመስል የሚናገሩትን ነገር አያውቁትም ፤ ሌላም ጊዜ ደግሞ አንደበታቸው ከጭንቅላታቸው የቀደመ አዛውንት ሆነው ያገኙቸዋል ፤ አልፎ አልፎም ፕሮፈሰር መስፍን እንዳሉት “ቂል የያዘው ሰይፍ” አይነት ሃሳብ በማንሳት የማህበረሰብ መነጋገሪያ ሆነው ያገኟቸዋል፡፡ ትልቅ አዛውንት ብለው እንዳያከብሯቸው የወረደ እና የዘቀጠ በ21ኛው ክፍለ ዘመን መነሳት የሌለበት ሃሳብ ሲያነሱ ያገኟቸዋል ፤ ቀላል ብለው እንዳይንቋቸው ደግሞ አምላክ እድሜ ሰጥቶ ሁለት ጸጉር እንዲያወጡ አድርጓቸዋል ፤ ታዲያ እኝን ሰው ምን እንበላቸው ?

Tuesday, December 25, 2012

የዋልድባ አካባቢ እየታረሰ ነው


(አንድ አድርገን ታህሳስ 16 2004 ዓ.ም)፡- የእርቀ ሰላሙ ጉዳይ የዋልድባን ጉዳይ ወደ ኋላ እንዲል አድርጎታል ፤ ምዕመኑ “እርቀ ሰላሙ ካልቀደመ ፓትርያርክ ምርጫው መደረግ የለበትም” ሲል አባቶች ደግሞ የአራት ቁጥርና የስድስት ቁጥር ነገር አስጨንቋቸዋል ፡፡  ከቀናት በፊት ከስኳር ኮርፖሬሽን ያገኝንው የፎቶ መረጃ ቦታው ላይ ምን እየተሰራ እንደሆነ ጥሩ አመላካች ሆኖ አግኝተነዋል ፤ ይህ የምታዩት ፎቶ ከስሩ ይህ ጽሁፍ ሰፍሮበት ይገኛል  “The Gorge of Zarema River where the MayDay Dam will be in place at Wolkayite” ይላል ፡፡

Monday, December 24, 2012

የብጹዕ አቡነ ሕዝቅኤል ወቅታዊ ቃለ መጠይቅ



ዕንቁ ፡- ብፁዕ አባታችን ስለ እድገትና ትምህርትዎ በአጠቃላይ ስለ ራስዎ ይንገሩን ?
ብጹእ አቡነ ሕዝቅኤል፡- የቀድሞ ስሜ መልአከ ምህረት አባ መኮንን ሀብተማርያም ይባላል፡፡ከአባቴ መሪጌታ መኮን ኃይሉና ከእናቴ ወ/ሮ አታላይ ደርሰህ ግንቦት 7 ቀን 1948 ዓ.ም በደበቡብ ወሎ አማራ ሳይንት ልዩ ስሙ ደብረ ብርሃን ለንጓጥ ሥላሴ በተባለው ቦታ ተወለድኩ፡፡ ከሙሉጌታ አበበ እሸቴ ከፊደል እስከ ዳዊት በተወለድኩበት ደብር ከተማርኩ በኋላ በዚያው በአማራ ሳይንት ደራው መድኃኒዓለም ከመሪ ጌታ አፈወርቅ ሳህሉ ቁም ዜማ አቋቋም ፤ ቦረና ቅዱስ ቂርቆስ ደብር ከመጋቤ ምስጥር ደስታ ብዙነህ ቅኔ ከነ አገባቡ ተምሬአለሁ፡፡
ከብጹዕ አቡነ ገብርኤል በ1956 ዓ.ም የዲቁና ማዕረግ ተቀብያለሁ፡፡ ከዚያ ጎጃም መርጡ ለማርያም ከየኔታ ኢሳያስ ቅኔ ከነ አገባቡ ፤ ከመምህር ሀብተ ኢየሱስ መጽሐፈ ነገስት ትርጓሜና የቅኔ መንዶችን ፤ ደብረ መድሃኒት መድኃኒዓለም ከየኔታ አስካል የቅኔ መንገዶችን ከነ አገባቡ ፤ ብቸና ቅዱስ ጊዮርጊስ ከየኔታ ፍሰሐ ወልደሚካኤል ምስጢርና የቅኔ ሙያን አዳብሬያለሁ፡፡ ከየኔታ ፍስሀ ወልደ ሚካኤል በ1969 ዓ.ም በቅኔ መምህርነት ተመርቄአለሁ፡፡

Saturday, December 22, 2012

ማኅበረቅዱሳን ቅዱስ ሲኖዶስ ፮ኛውን ፓትርያርያክ ለመምረጥ የወሰነውን ውሳኔ በድጋሜ እንዲያጤነው ጠየቀ





  •   ቤተክርስቲያን ስድስት ቦታ ብትከፈል አያገባኝም።” አቡነ ቀሌምንጦስ
  •  “ወነአምን በአሐቲ ቤተክርስቲያን” ማኅበረቅዱሳን
  •  ቅዱስ ሲኖዶስ ለእርቀ ሰላሙ ቅድሚያ የማይሰጥ ከሆነ ራሳችንን እናገላለን” በአሜሪካ የኢትዮጵያ አብያተክርስቲያናት ምእመናን
  •  ሀራ ተዋህዶ የተሰኘው የጡመራ መድረክ “ማኅበረቅዱሳን አቋሙን ለወጠ።” የሚለው መሰረተ ቢስ ወሬ ግብ ምን እንደሆነ እያነጋገረ ነው።
  •  “መንግሥት በካርድ ነው የሚመርጠው ፣ ስለዚህ መንግሥት ኃጥያተኛ ነው? እኛ ማን ሆነን ነው በዕጣ ካልሆነ የምንለው? ከመንግሥት እኛ እንበልጣለን?” አቡነ ጎርጎርዮስ

(አንድ አድርገን ታህሳስ 13 2005 ዓ.ም)፡- ባለፉት ሃያ ዓመታት ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን መንፈሳዊና ማኅበራዊ አገልግሎት በማበርከት በቅዱስ ሲኖዶስ እና በምእመናን ዘንድ ታማኚነት ያተረፈው ማኅበረ ቅዱሳን ከአቡነ ጳውሎስ እረፍት በኋላ የቤተክርስቲያን አንድነት ቅድሚያ በመስጠት ቅዱስ ሲኖዶስ ለእርቀ ሰላም ቅድሚያ ሰጥቶ እንዲወያይ ለጥቅምቱ ቅዱስ ሲኖዶስ ስብሰባ በደብዳቤ ማሳወቁ፣ በህትመትና ኤሌክትሮኒክስ ልሳኖቹ ማሳወቁ እንዲሁም የማኅበሩ አመራሮች አባቶችንና ምእመናን መደበኛ በሆኑና ባልሆኑ መንገዶች በማወያየት የበኩሉን ድርሻ ለመወጣት መጣራቸው ይታወቃል።

ቅ/ሲኖዶስ የሠየመው የፓትርያሪክ አስመራጭ ኮሚቴ ዓለም አቀፍ ተቃውሞ ቀስቅሷል

from :- Addis Admass

  • ‹‹ዕርቀ ሰላሙ ይቅደም›› የሚሉ ጳጳሳት የሲኖዶሱን ውሳኔ አንቀበለውም ብለዋል
  • የላሊበላው ውዝግብ ወደ አላስፈላጊ ግጭት እንዳያመራ ተሰግቷል
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የስድስተኛውን ፓትርያሪክ ምርጫ ዝግጅት የሚመራና እስከ ጥር መጨረሻ ዕጩዎችን የሚያቀርብ አስመራጭ ኮሚቴ መሠየሙ በቤተ ክርስቲያኒቱ ካህናትና ምእመናን ዘንድ ዓለም አቀፍ ተቃውሞ መቀስቀሱ ተገለጸ። ‹‹የቤተ ክርስቲያን ጉዳይ ያገባኛል›› በሚል መርሕ በዋናነት በማኅበራዊ ሚዲያዎችና ብሎጎች እየተገለጸ ያለው ይኸው ተቃውሞ፤ የቤተ ክርስቲያን ሰላምና አንድነት የሚረጋገጥበት የዕርቁ ጉባኤ ‹‹የአባቶች ጉዳይ ብቻ አይደለም፤ ምእመናኑን ያገለለ ሊኾን አይገባም›› በሚል የካህናቱና ምእመናኑ ድምፅ እንዲደመጥ የሚወተውት ነው፡፡

Thursday, December 20, 2012

በተግባር ተቃውሟችንን እንግለጽ



  • እረኞች ሆይ የበጎቻችሁን ምክር ስሙ

(አንድ አድርገን ታህሳስ 12 2004 ዓ.ም)፡-በአሁኑ ሰዓት ፓትርያርክ ለመሾም የሚደረገውን ጥድፊያ “አንድ አድርገን” አጥብቃ ትቃወማለች ፤ለ20 ዓመት የቆየውን መከፋፈል ወደ ሌላ ደረጃ የሚያሻግር ስራ መስራት ከታሪክ ተወቃሽነት አያድንም ፤ ህዝቡ መጀመሪያ እርቀ ሰላሙን ይቅደም የቤተክርስቲያኒቱን አንድነት ይመለስ ከዚያ የፓትርያርክ ምርጫው ይደረስበታል የሚል አቋም በያዘበት በአሁኑ ወቅት አባቶች የምርጫ ህጉን እንደዚህ አጣድፈው የምርጫ አስፈጻሚ ኮሚቴ ለመሰየም የሚያደርጉት ጉዞ አንድም ለራሳቸው ሁለተኛም ለቤተክርስቲያን ሶስተኛም ለምዕመኑ ጥሩ አካሄድ አለመሆኑን አውቀው የያዙትን አቋም ቢያንስ እስከ እርቀ ሰላሙ ፍጻሜ ድረስ ቢያቆዩት መልካም ነው የሚል አስተያየት አለን ፡፡ ይህን አካሄድ ለመቃወም ፌስቡክ እና ዘመናዊ የኤሌክትሮኒክ ሚዲያዎች በቂዎች ናቸው ብለን አናስብም ፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የኢንተርኔት ተጠቃሚ ከ500ሺህ ባልዘለለበት ሁኔታ ነገሩን በድህረ-ገጾች እና በፌስቡክ ላይ ተደራሽ ከማድረግ በተጨማሪ ምዕመኑ ሁኔታው አውቆ እና ተረድቶ በግልጽ በአካል የሚቃወምበት ሃሳቡን የሚገልጽበት መንገድ ራሱን በማደራጀት ማመቻቸት መቻል አለበት ፡፡ ኢንተርኔት ኢትዮጵያ ውስጥ 2 በመቶ ተደራሽ አለመሆኑን ልናውቅ ይገባል ፤ ይህ ጉዳይ ከምናወራውና ከምናስበው በላይ ከባድ የሆነ ችግር ይዞብን እንደሚመጣ መገመት መቻል አለብን ፡፡ ባለፈው 20 ዓመት እሮሮ ሳይበቃ ወደ አዲስ እሮሮ መሸጋገር መቻል የለብንም ፤ ሌላ የገማ እንቁላል ሲወረወር መመልከት መቻል የለብንም ፤ ቤተክርስቲያን አሁን የሚያስፈልጋት ከፓትርያርክ ምርጫ በፊት አንድነቷ ነው ፡፡ ባለፉት 16 መቶ ክፍለ ዘመናት ከግብጽ በመቶ አስራ አንድ አባቶች አንድነቷ አደጋ ላይ ሳይወድቅ መመራት ችላለች ባለፉት 40 እና 50 ዓመታት በንጉሰ ነገስቱ እና በወቅቱ በነበሩ አባቶቻችን  የጳጳስነት እና የፓትርያርክነት ስልጣን ወደ ኢትዮጵያውያን ከተመለሰ በኋላ በአንድነት የማያስቀጥላት ደረጃ ላይ ደርሳለች፡፡ 

Tuesday, December 18, 2012

ሽጉጥ ያስመዘዘ የሰበካ ጉባኤ ምርጫ




ከዳዊት
(አንድ አድርገን ታህሳስ 9 2005 ዓ.ም)፡- በመንበረ መንግሥት ቅዱስ ገብርኤል  ገዳም (በተለምዶ ግቢ ገብርኤል) እየተባለ የሚጠራው የቤተክርስትያን ቅጥር ውስጥ  በምዕመናን እና በገዳሙ አመራሮች መካከል በተፈጠረው አለመግባባት ድንጋይ መወርወሩንና የገዳሙ ገንዘብ ቤት ኃላፊ የሆኑት መምሬ ንጉሴ የታጠቁት ሽጉጥ መምዘዛቸውን በስፍራው የነበሩ የአይን እማኞች ተናግረዋል፡፡
ምዕመናኑንና የገዳሙን አመራር ለልዩነት የዳረገው ምክንያት የሰበካ ጉባኤ አባላት አመራረጥ ሂደት መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡ እንደ መረጃ ምንጮቻችን በ2003 ዓ.ም ወርሃ መጋቢት በተደረገ ምርጫ ዘጠኝ አባላት ያሉት ሰበካ ጉባኤ የገዳሙንና የሃይማኖቱን ቃለ አዋዲ በጠበቀ መልኩ ወደ ስራ ገብተው ነበር፡፡ ከአዲሱ ሰበካ ጉባኤ በፊት የነበሩት የሰበካ ጉባኤ አባላት የገዳሙን ገንዘብ በመመሳጠር ሲዘርፉ በመቆየታቸው የተነሳ የስራ ዘመናቸውን ሳያጠናቅቁ እንዲሰናበቱ ተደርገው ነበር፡፡

‹‹የጳጳሱ ቅሌት›› መጽሐፍ ጸሐፊ በ‹‹የጳጳሱ ስኬት›› መጽሐፍ ይቅርታ ጠየቀ


(አንድ አድርገን ታህሳስ 8 2005 ዓ.ም)፡- የቀድሞ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በነበሩት ብጹዕ አቡነ ሳሙኤል ላይ “የጳጳሱ ቅሌት” በሚል ርእስ መጽሐፍ የጻፈውና ‹‹ተከስ ዘሪሁን›› በተባለ ኅቡእ ስም የሚታወቀው ጸሐፊ  “የጳጳሱ ስኬት” በተሰኝ ሌላ መጽሐፍ  ሊቀ ጳጳሱንና  በቀደመ መጽሐፉ ‹‹አለስማቸውና አለግብራው ተጠቅሰዋል›› ያላቸውን ግለሰቦች በመዘርዘር ይቅርታ ጠይቋል፡፡ በ‹‹ጳጳሱ ቅሌት›› መጽሐፍ ውስጥ የተገለጹት ‹‹ሳሙኤል›› ከሊቀ ጳጳሱ ብጹዕ  አቡነ ሳሙኤል ጋር በምንም መልኩ ግንኙነትየሌላቸው ናቸውያለው ጸሐፊው ‹‹ የሊቀ ጳጳሱን ስም ለማጥፋት ዘመኑን በአስተሳሰብና በተግባር በመዋጀት በሰጡት ከፍተኛ አመራር  ለቤተክርስቲያን ያበረከቱት አስተዋጽኦ ለማጠልሸት  ብሎም ቤተክርስቲያኒቱን ለመናፍቃን አሳልፎ ለመስጠት ያሴሩ ናቸው›› ባላቸው ግለሰቦች ፍላጎት በመገዛቱ መጸጸቱንና ሊቀ ጳጳሱን አቡነ ሳሙኤልን ይቅርታ እንደሚጠይቅ ገልጧል፡፡

ቀድሞ ቤተክርስቲያኒቱን ቀኖና ለማፈራረስ እና ምዕመኑን ከመናፍቃን ጋር ለመቀላቀል የረዥም ጊዜ እቅድ ነድፈው  ሲንቀሳቀሱ የነበሩ የውስጥ አርበኞች መኖራቸው ይታወቃል ፤ አሁንም እንዳሉ እሙን ነው ፡፡ የያዙትን አላማ ለማስፈጸምም በርካታ ገንዘብ በመመደብ ብዙ ቅጥረኞችን በስራቸው በማሰራት የምዕመኑ እይታ ላይ ብዥታ ሲፈጥሩ ተስተውሏል ፤ በውጭ እምቢ ያላቸውን አካሄድ ወደ ውስጥ በማስረግ መድረሻቸው እስኪደርሱ ድረስ ማወካቸው ውስጥ ውስጡን መስራታቸው የማይቀር ነገር ነው ፤ ይህም ግለሰብ ራሱ እንደተናገረው “ቤተክርስቲያኒቱን ለመናፍቃን አሳልፎ ለመስጠት ያሴሩ ናቸው” ባለቸው ሰዎች ሆዳው አምላካቸው በሆኑ ሰዎች አማካኝነት ይህን የስም ማጥፋት ስራ መስራት ችሎ ነበር ፤ ወደ አእምሮው ሲመለስ የሰራው ስራ መልካም ያለመሆኑን በመገንዘብ ይቅርታ ሊጠይቅ ችሏል ፤ እኛም ቤተክርስቲያንን ለተሃድሶያውያን እና ለመናፍቃን አሳልፈን ላለመስጠት ሁላችን እንደ  ምዕመን ልንነቃ ያስፈልጋል፡፡
 ቸር ሰንብቱ

Sunday, December 16, 2012

ቅዱስ ሲኖዶስ ተመራጩ ፓትርያርክ ኢትዮጵያዊ ዜጋ ብቻ እንዲሆን ወሰነ




አዲስ አድማስ ጋዜጣ እንዳገኝነው

  • ዜግነትን መቀየር ለትውልድ ካለው አርአያነት አንጻር ከአንድ በላይ ዜግነት ያላቸው ጳጳሳት በምርጫው አይካተቱም፡፡
  • መንፈሳዊ እና ማኅበራዊ አገልግሎትን በመፈጸም በቂ ችሎታና ልምድ ከማካበት አንጻር የገዳም መነኩሴ የሚለው እንዲወጣ ተደርጓል

(አንድ አድርገን ታህሳስ 8 2005 ዓ.ም)፡- በፓትርያርክ ምርጫ ሕግ ረቂቅ ላይ ውይይት እያካሄደ የሚገኝው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ የተመራጩ ፓትርያርክ ዜግነት ኢትዮጵያዊ ብቻ መኾን እንደሚገባው ወሰነ፡፡