Sunday, February 5, 2023

ድርድር የሚባለውን ነገር መሸሽ ግትርነት ሊሆን ይችላል?


ኦርቶዶክሳዊ ያልሆኑት ሁሉ ነገራችን በውል እንዲረዱት የቀረበ ትሑት ማብራሪያ።

  (ብርሃኑ  አድማስ አንለይ)

ብዙዎች በቅንነት ድርድር ምን ችግር አለው? መንፈሳዊ ሰዎች እንዴት ይህን እንቢ ሊል ይችላል? መነጋገር ምንድን ነው ችግሩ? እነዚህ እና ተመሳሳይ አሳቦችን አለመቀበል እንዴት እነካለሁ የሚል የአለመደፈር ስሜት የሚመስላቸው ሰዎች እንዳሉ ከአንዳንድ አስተያየቶች መረዳት ችያለሁ። ስለዚህ ድርድርን መቀበል ለምን አስቸጋሪ እንደሆነ ለመረዳት ጉዳዩ ምን እንደሆነ ማስረዳት እፈልጋለሁ።

ቤተ ክርስቲያናችን ተጥሷል ብላ ውግዘት ለመፈጸም ምክንያት የሆናት የትኞቹም ጥንታውያን አብያተ ክርስቲያናት የሚጠቀሙበት መንፈሳዊ ሕግ መጣሱ ነው። ይህ ሕግ አማኞች በልቡናቸው የሚያምኑትን ረቂቅ እምነት በተግባር በሥርዓተ አምልኮት የሚፈጽሙበት መንፈሳዊ ሥርዓት ማለት ነው። ይህ ሕግ ምን ምን እንደሚያካትት በዝርዝር ማስረዳት ባይቻልም ምን እንደሆነ ለመረዳት እንዲያግዘን ትንሽ ልዘርዝርለት ። ለምሳሌ የጾም ወቅቶችን ፣ ቀኖቹን እና ሰዓቱን የሚመለከተው፣ ቅዳሴ መቼ እንዴት በእነማን እንደሚቀደስ ፤ የክርስቶስ ዐበይት በዓላት እነማን እንደሆኑና እንዴት እንደሚከበሩ፣ ሥርዓተ አምልኮት የሚመሩ እና ቤተ ክርስቲያንን በማስተማርም ሆነ በማስተዳደር የሚያገልግሉ ካህናት እንዴት እንደሚሾሙ እና እንዴት እንደሚሻሩ፣ በስሐተት እና በኃጢአት የወደቁ ሰዎች እንዴት እንደሚመለሱ፤ ይህንን የመሳሰሉትን ብዙ የሥርዓተ አምልኮት ነገሮች በዝርዝር የያዘ መንፈሳዊ ሕግ ነው። 

ሰሞኑን የገጠመን ኤጲስቆጶሳትን መሾም እና በሀገረ ስብክት መመደብ የተመለከተውን ዋና የሥርዓተ አምልኮታችን ምሰሶ የሆነውን አስተምህሮ እና ቀኖና የተመለከተ ጥሰት ነው። ይህ ሲያጋጥም ምን እንደሚደረግ እና እንዴት እንደሚፈታ ሁሉ ደግሞ አሁንም ሥርዓቱ አስቀድሞ ደንግጎ እና አስቀድሞም አውግዞ ተቀምጧል። በየዘመኑ የሚደረገው ያንን መፈጸም እና ማስፈጸም ብቻ ነው።

ታዲይ ይህ ነገር ለድርድር እንደማይገባ በዚሁ የቀኖና መጻሕፍት ከተደነገጉት ውስጥ አንድ ሁለቱን ምሳሌ አድርጌ ላስረዳ። ለምሳሌ ያህል አጽዋማትን የተመለከተውን ላንሳ። ለምሳሌ አንድ ሊቀ ጳጳስ ብድግ ብሎ ዐርብ እና ረቡዕን መጾም አይገባም። ዐቢይ ጾምንም ለሃምሳ አምስት ቀናት ሳይሆን ለዐሥራ አምስት ቀናት ይበቃናል። ትንሣኤንም እሑድን ጠብቀን ማድረግ አይጠበቅብንም። ወቅቱንም ብንፈልግ በመስከረም ካልሆነም በጥር እንዳመችነቱ ማድረግ እንችላለን። ዋናው ዐቢይ ጾምን መጾማችን ብቻ ነው የሚበቃው። ይህን ቢያደርግ ይህን ያለው ሊቀ ጳጳስ በአጭሩ ሌላ እምነት መሥርቷል ማለት ይቻላል። ይህን ያደረገ ጊዜ በራሱ ፈቃድ ከነባሩ ኦርቶዶክስ ራሱን ለይቷል። የቀኖና መጽሐፋችን ደግሞ ይህን የሚያደርገውን ገና ቀድሞ አውግዞታል። የአሁኑ ሲኖዶስ ደግሞ ይሰበሰብና ይህን ለማስጠበቅ የተሾመው ጳጳስ ራሱ ስለሻረው ያን የቀደሙ አባቶች የፈጸሙት ውግዘት በተግባር ይፈጸምብሃል ይልና ከቅድስት ቤተ ክርስቲያን ኅብረት ይለየዋል፣ ሥልጣኑን እና መዓርጉንም ይቀማዋል። 

ይህ ከሆነ በኋላ አሁን እንደሚባለው መንግሥት መጥቶ ይህ ምን ችግር አለው፣ በንግግር ይፈታል ቢል አባቶች እና አማኞች የምንለው ይህ ለድርድር አይቀርብም ነው። ምክንያቱም ዐርብ እና ረቡዕን የመሻር ወይም እንዲሻሩም ሆነ እንዲቀጥሉ የመደራደር ሥልጣን ያለው አካል የለም። ዐቢይ ጾምን በ55 ቀናት እና በ15 ቀናት መካከል ተደራድሮ 30 ወይም 45 ቀናት ብቻ የማድረግ ሥልጣን ያለው የለም። ትንሣኤን ከእሑድ ውጭ በሌላ ቀናት ቀርቶ የሚያዚያ ጨረቃ ሙሉ ከመሆኗ በፊት ባለው ሌላ እሑድ ውስጥ እንኳ ያደረገ ቢኖር ከሥልጣኑ ይሻር ነው የሚለው ቀኖናው። የመሰላችሁን ፍረዱበት እንኳን አይልም። ይህም ማለት ፍርዱ ያለቀ የደቀቀ ሆኖ በየዘመኑ የሚኖረው ሲኖዶስ ሥልጣኑ ያንን ተገባራዊ ማድረግ ብቻ ነው። 

ለሌሎቻቸሁ ድርድር አይቻልም የሚለው ያልገባቸሁ ክህነት መሾም ልክ እንደ መንግሥት ሥልጣን ስለመሰላችሁ በድርድር የሚያልቅ መስሏችሁ ሊሆን ይችላል። ነገሩ ልክ እላይ የገለጽኩት ዓይነት ብቻ ነው። ልክ ይህ ገብቷቸው ወይም በብዙዎች ዘንድ ይህ መሆኑ አለመታወቁን ጥላ አድርገው መሒዳቸውን ትተው አጥፈተናል ሲሉ ጥለውት ከወጡት ኦርቶዶክስነት ይመለሳሉ። ያኔ ነው መነጋገር የሚቻለው። ሀሳቡን ግልጽ አድርጌው ከሆነ ጉዳዩ ይህ መሆኑን እንድትረዱት እፈልጋለሁ። ልክ እንደሌላ መዋቅር አይደለም ያልነው ለዚህ ነው። ይህ የግትርነት ሳይሆን የእምነት ሕግን የመፈጸም እና ያለመፈጸም ጉዳይ ነው ማለት ነው። 

በአጭር ቋንቋ ኦርቶዶክስ እና ሄትሮዶክስ የመሆን ጉዳይ ነው። በእነዚህ መካከል ድርድር መደረግ ይችላል ማለት በፕሮቴስታንት እና በእስልምና መካከልም ይቻላል እንደማለት ያለ መሆኑን በውል መረዳት ተገቢ ነው።

መንግሥት ለምን አስከፋን ካላችሁ? በዚህ ውስጥ ገብቶ ላደራድር፣ እኔ የምሰጠውን ምክርም ስሙ ማለት ቅዱሳን በሠሩት ቀኖና ላይ እኔ የምሰጠው ሀሳብ ሥልጣን ይኑረው ማለት ስለሆነ ይህ ፍጹም ክህደት ነው። ሁለተኛ እነዚህ ሰዎች በቀኖናው መሠረት ተወገዙ እንጂ ሌላ እምነት እንዳይመሥርቱ የከለከላቸው የለም። የጎሣ ኦርቶዶክስ መመሥረትም መብታቸው ነው። ይህን ወደ ኦርቶዶክስ ለማስገባት መሞከር ግን ክህደት ነው፣ የተወገዘ ነው። ሦስተኛ አሁን መንግሥታዊ አካላት እያደረጉት ያሉት ከኦርቶዶክስ ወጥተው አዲስ ለተቋቋሙት ሌላው ቀርቶ ሕጋዊ ሰውነት እንኳ ለሌላቸው የኦርቶዶክስ የሆኑትን መቅደሶች፣ መንበረ ጵጵስናዎች እና ቢሮዎች በጉልበት እየቀሙ እየሰጡ ነው። ይሄ የእኛ የኦርቶዶክሶች ነው፤ እነርሱ እምነታቸውን ሰብከው ካፈሩት ምእመን ልክ እንደ ፕሮቴስታንት የራሳቸውን ይሥሩ ሲል እየገደለ፣ እያሠረ ፣ እየቀማ እየሰጠ ነው። የተጠየቀው ቀላል ጥያቄ ነው። የኦርቶዶክሶችን ለሄትሮዶክሶች ለምን በጉልበት ትሰጣለህ የሚል ቀላል ጥያቄ ነው።

እነዚህን ሰዎች እንደሆኑት ሆነው ተቀብላችሁ አብራችሁ አገልግሉ ማለትም በኦርቶዶክስ መቅደስ ፓስተሩ፣ በመስጊድም ቄሱ ይባርክ ከሚለው ምንም ልዩነት የለውም። ልብሱን ስለለበሱ አሁን ኦርቶዶክስ አድርጋችሁ እንዳትቆጥሩ። ይህን የምንለው እነርሱን በመጥላት እና በመናቅ አይደለም። ይህ እንዳልሆነ የምናመልከው አምላክ እርሱ ልዑል እግዚአብሔር ያውቃል። ይህን የምንለው ጉዳዩ መሠርታዊ የሥርዓተ አምልኮት ጥሰት መሆኑን በገላጭ ምሳሌ እንድትረዱት ብቻ ነው።

እግዚአብሔር ያሳያችሁ!! እንዲህ ያለ በደል በየት ሀገር በማን ላይ ተፈጽሞ ያውቃል? ታዲያ እምነቴን አትንካ፣ የሃይማኖት ተቋሜንም ለማያምኑበት አሳልፈህ አትስጥብኝ። ይልቁንም ሕግ አስከብረህ ከብጥብጥ አድነኝ ስለው በሁሉም በኩል እውነት አለ ማለት ምን ማለት ነው? ግትርነትስ የሚሆነው እንዴት ሆኖ ነው። ጉዳዩ ይሄው ነው። በሕያው እግዚአብሔር ስም እመሰክራለሁ ሌላ ምንም ነገር የለውም። ሀገር ወዳድ፣ እውነት ወዳድ የሆናችሁ ሁሉ ከመተቸታችሁ እና አስተያየት ከመስጠታችሁ በፊት ይህን ነገር በውል ተረድታችሁ እንድታስረዱ በታላቅ ትሕትና እጠይቃለሁ። አስተዋይ ኅሊና ያለው ሁሉ አይቶ ይፍረድ።

በምዕራብ አርሲ ሀገረ ስብከት ሻሸመኔ እስራትና ውክቢያው ቀጥሏል። ሀገረ ስብከቱን በወራሪ ለመመዝበርና ሰብሮሮ ለመቆጣጠረር እየተሞከረ ነው።


+++++++++++++++++++++++++++++++++++++++
ሊቀ ኅሩያን ቀሲስ ብርሃኑ ወልደ ዮሐንስ የምዕራብ አርሲ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ ለኢኦተቤ በስልክ እንደገለጹት ፣ ዛሬ ጥር 26 ቀን 2015 ዓ.ም ጠዋትወደ ምዕራብ አርሲ ሀገረ ስብከት የጸጥታ አካላት በመምጣት የሀገረ ስብከቱን  ሠራተኞችን ከሥራ በማስወጣት ሀገረ ስብከቱን ግቢ  ከሠራተኞች ነጻ እንዳደረገው ገልጸዋል።
ፖሊስ በአርሲ ነገሌ አራት የደብር አስተዳዳሪዎችን ሕገ ወጡን ቡድን ተቀበሉ በማለት ሲያስገድድ ከቅዱስ ሲኖዶስ ጎን ነን በማለታቸው አራት አስተዳዳሪዎች ታስረዋል ብለዋል።
በመንበረ ጵጵስናው አብያተክርስቲያናት በታጠቁ ኃይሎች በፓትሮል በመዞር ምእመናኑን በማስፈራራት ላይ ናቸው ያሉት ዋና ሥራ አስኪያጁ 
ትናንት ምሽት በጸጥታ ኃይሎች የታፈኑት የምዕራብ አርሲ ሀገረ ስብከት ዋና ፀሐፊ ሊቀ ልሳናት ቀሲስ ወንድወሰን ጥላሁንና የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው መምህር ሰሎሞን ዘገየ ከእስር ከተለቀቁ በኋላ ከበላይ ታዘን ነው በማለት በዛሬው ዕለት በድጋሚ  መታሠራቸውን እርሳቸውም ክትትል እየተደረገባቸው እንደሆነና የምዕራብ አርሲ ሀገረ ስብከት ጽሕፈት ቤት ሠራተኞች በመንግሥት የጸጥታ አካላት ወደ ጽሕፈት ቤቱ እንዳይገቡ መከልከላቸውን አስታውቀዋል።
ሁነቱን ለዘረፋ ሊጠቀምበት ያሰፈሰፈ ኃይል አለ የዞኑ መንግሥት ከበላይ የመጣ ትዕዛዝ ነው በሚል በሃይማኖታችን ሊያስገድደን አይገባም ብለዋል። ትላንት አብረናቸው ሥንሰራ የነበሩ የፀጥታ አካላት እናዝናለን ግን ከበላይ ታዘን ነው በማለት ምንም ማድረግ እንደማይችሉ እየገለጹልን ነው ያሉት ሥራ አስኪያጁ በሕገ ወጥነትና በዘረፋ ምእመናንን ማገልገል እንዴት ይቻላል? ሲሉ ጠይቀዋል። እኔም የአካባቢው ተወላጅና በኦሮምኛ ቋንቋ አገልግሎት የምሰጥ ነኝ ጉዳዩ ቤተክርስቲያንን ለሌላ ሃይማኖት መጠቀሚያ ለማድረግ የተሴረ ሴራ ነው ብለዋል። ሁሉም ወረዳዎች ሕገወጡን ሢመት አውግዘው በቅዱስ ሲኖዶሱ ሥር መሆናቸውን ገልጸዋል።
በሻሸመኔ በሕገ ወጡ ሲኖዶስ የተሾመው ግለሰብ የወንጌላውያን አማኝ የሆነችው ዘጸአት አፖስትሊክ ቸርች የኪራይ ስምምነት አለኝ ስትል መግለጫ ያወጣችበት ግለሰብ መሆኑ ይታወሳል።
ሥራ አስኪያጁ የሰጡትን መግለጫ ከቆይታ በኋላ በዩቲዩብ ገጻችን ማግኘት ይቻላል።
EOTC TV
++

ብፁዕ አቡነ ዮሴፍ እና ብፁዕ አቡነ ያዕቆብ በሻሸመኔ ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን በትናንትናው ዕለት በጸጥታ ኃይሎች በተወሰደው እርምጃ የተጎዱ ምእመናንን ጎብኙ።


የሻሸመኔ ኦርቶዶክሳውያን በቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ መሰረት የሕገ ወጡን ቡድን ወደ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን አናስገባም በማለት ቅጽራቸውን ሲጠብቁ ቢውሉም ለሕገ ወጡ ቡድን ከለላ የሰጠው የጸጥታ ኃይል በንጹሃን ላይ እርምጃ መውሰዱ ይታወቃል።

በዚህም ሰማዕትነትን የተቀበሉ ምእመናን እንዳሉ ሁሉ በርካቶች ከፍታኛ እና ቀላል ጉዳት ደርሶባቸው ወደ ሐዋሳ የተለያዩ ሆስፒታሎች ተወስደዋል።

እስካሁን ባለን መረጃም በሐዋሳ ሪፈራል ሆስፒታል 6፣ በያኔት ሆስፒታል፣ በአላቲዮን ሆስፒታል 8 ምእመናን ሕክምና እየተደረገላቸው ይገኛሉ።

የሲዳማ፣ ጌዲዮ፣ አማሮ፣ ቡርጂና ምዕራብ አርሲ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ዮሴፍ እና ብፁዕ አቡነ ያዕቆብ የጆርጂያና አካባቢው ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እነዚህን ምእመናን በሐዋሳ በመገኘት አጽናንተዋል፤ ሀዘናቸውንም ገልጸዋል።
++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++
ምንጭ
የማኅበረ ቅዱሳን ብሮድካስት አገልግሎት