ጥቅምት ፲፩ ቀን ፳፻ ፲ወ፭ ዓ.ም አዲስአበባ -ኢትዮጵያ
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ በዓመት ሁለት ጊዜ እንደሚያካሂድ ይታወሳል፡፡ይኸውም በወርኃ ጥቅምትና ግንቦት ነው፡፡ በእነዚህ ወራት በመንፈስ ቅዱስ መሪነት ምልዓተ ጉባኤውን በማካሔድ በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ሁለንታዊ ጉዳዩች ወይም መንፈሳዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ አገልግሎቶች ላይ በመምከር ልዩ ልዩ ውሳኔዎችን እንደሚያስተላልፍ ይታወቃል።
ቅዱስ ሲኖዶስ የሚያካሒዳቸው እነዚህ ጉባኤያት በተረጋጋ፣ በሰከነና በተሳካ መልኩ መካሔድ ይችላሉ ዘንድ የሚመለከታቸው አካላት ሁሉ አስፈላጊውን ትብብርና ድጋፍ ማድረግ ይኖርባቸዋል። በተለይም በተለምዶ ጉባኤው በሚካሔድበት ወቅት ልዩ ልዩ አቤቱታዎችን ሕጋዊውን አሠራር ባልጠበቀ መልኩ በግልና በቡድን በመሆን በቅዱስ ሲኖዶስ ጽሕፈት ቤት፣ በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽሕፈት ቤትና በብፁዓን አባቶች ማረፊያ ቤት በመገኘት ማቅረብ ሕጋዊነት የሌለው ተግባር ከመሆኑም በላይ የቅዱስ ሲኖዶስን ጉባኤን የሚያውክ ነው፡፡ በዚህም የተነሣ ፍጹም ተቀባይነትን የሌለው ተግባር መሆኑን ሁሉም ሊያውቀው ይገባል፡፡አቤቱታና ጥያቄዎች ካሉም በሕጋዊው የቤተ ክርስቲያናችን አሠራር መሠረት መዋቅራዊ አሠራርን በጠበቀ መልኩ ማቅረብ ተቀባይነት ያለውና ሕጋዊ አሠራር ነው፡፡ በመሆኑም ማንኛውም ሕጋዊ አቤቱታና ጥያቄ ያለው ግለስብም ይሁን ተቋም ይህንን አሠራር መሠረት በማድረግ ጥያቄና አቤቱታውን ማቅረብ ይችላል። ይህም የሚሆነው ግን የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ የሚካሔድበትን ወቅት ጠብቆ መሆን የለበትም።