- ሀገራችን ካለ እናንተ
ጸሎት ውጪ ሰላሟም ልማቷም ሊረጋገጥ አይችልም
- ዛሬ በኢትዮጵያ ወገኖቻችን
ላይ ተገንብቶ የኖረው የመጀመሪያው የጥላቻ ግንብ ዋንኛው ምሰሶ በይፋ ተንዷል
(አንድ አድርገን ሐምሌ 19 2010 ዓ.ም)፡- ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር
አብይ አሕመድ በእርቀ ሰላም ጉባኤ ላይ የተናገሩትን እንዲህ አቅርበነዋል
‹‹በጣም ደስ ብሎኛል እንኳን ደስ አላችሁ ፤ ኢትዮጵያ ከዚች ታላቅ ቤተ ክርስቲያ ውጪ አትታሰብም ፤ እርቁ እንዲመጣ ያስፈለገበት ምክንያት ኦርቶዶክስ ሀገር ስለሆነው ነው ፤ ታላቅ ታሪክ ፣ ዝና እና ክብር ያላት ቤተክርስቲያን ናት ፤ እዚህ ሰላም ሲሆን ሁላችንም ሰላም እንሆናለን ፤ እዚህ ሰላም ሲጠፋ ደግሞ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪነት እያንዳንዳችንን ይነካናል ፤ አንድነቷ ከተጠበቀ ሌሎችን መርዳት ትችላለች ፤ የታሪክና የትውፊት ባለቤት የሆነች ቤተ ክርስቲያን ራሷ አንድነቷን በማጣቷ እሷ እያለች ሌሎች እኛን ሲያግዙን ኖረዋል ፤ የእሷ አንድነት ከምስራቅ አፍሪካ አልፎ ለአፍሪካ ትልቅ ዜና ፣ ትልቅ ብስራት እንደሆነ ይሰማኛል ፣ በተግባርም የምናየው ይሄንኑ ነው ፤ በህብረት ውስጥ የሚገኝ ትርፍ ፣ ሥምና ዝና አጥተናል ፤ ኦርቶዶክስ አንድ ሆና ቢሆን ኖሮ የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ጉዳይ እርቀ ሰላም እስከ አሁን ባልዘገየ ነበር፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ሰው ከራሱ እንዲጣላ ፣ ከጎረቤትና ከሃይማኖቱ እንዲጣላ ፤ የሃይማኖት አባቶችን እንዳያከብር ፤ ሲገሰጽ እንዳይመከር ያደረገው አንዱ ነገር በዚች ታላቅ እና ቅድስት ቤተክርስቲያ ያጋጠመው ጸብ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ እኛ አንድ ስንሆን ለክርስትና እምነት ብቻ ሳይሆን ለእስልምናና ኢትዮጵያ ውስጥ ላሉ ዜጎች በሙሉ ክብር ፣ አንድነትና ሰላም የሆነ ዜና መስማት እጅጉን የሚያስደስት ነገር ስለሆነ ዛሬ ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ምዕመናት ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያ ሙስሊሞችም እንኳን ደስ አላችሁ ማለት እፈልጋለሁ፡፡