Friday, August 18, 2017

ምሥጢረ ደብረ ታቦር


 ዲያቆን መልአኩ እዘዘው
በዚህ መሆን ለእኛ መልካም ነው፤ ብትወድስ፥ በዚህ ሦስት ዳስ አንዱን ለአንተ አንዱንም ለሙሴ አንዱንም ለኤልያስ እንሥራ

እርሱም ገና ሲናገር፥ እነሆ፥ ብሩህ ደመና ጋረዳቸው፥ እነሆም፥ ከደመናው። በእርሱ ደስ የሚለ
የምወደው ልጄ ይህ ነው፤ እርሱን ስሙት የሚል ድምፅ መጣ። ደቀ መዛሙርቱም ሰምተው በፊታቸው ወደቁ እጅግም ፈርተው ነበር። ኢየሱስም ቀርቦ ዳሰሳቸውና። ተነሡ አትፍሩም አላቸው።ዓይናቸውንም አቅንተው ሲያዩ ከኢየሱስ ብቻ በቀር ማንንም አላዩም። የማቴዎስ ወንጌል 171-8
በቂሳርያ ጌታችን ለደቀመዛሙርቱ ለሰዎች የሰውን ልጅ ማን ይሉታል ብሎ ጠይቋቸው አንዳንዶች ከነቢያት አንዱ ነህ ይሉሃል፣ አንዳንዶች ሙሴ ነህ ይሉሃል፣ ሌሎች ደግሞ ኤልያስ ነህ ይሉሃል እያሉ መለሱለት ጌታችንም መልሶ እናንተስ ማን ትሉኛላችሁ ብሎ ሲጠይቃቸው የሐዋርያት አፈጉባዔ ሊቀ ሐዋርያት /ጴጥሮስአንተ ክርስቶስ የሕያው እግዚአብሔር አብ የባሕርይ ልጅ ነህብሎ በመመስከሩ ጌታምየዮና ልጅ ስምዖን ሆይ በሰማይ ያለው አባቴ እንጂ ሥጋና ደም ይህን አልገለጠልህምና ብፁዕ ነህ…› ተብሏል፡፡


ይህ በሆነ በሰባተኛው ቀን ሦስቱን ደቀ መዛሙርት ጴጥሮስ፣ ዮሐንስና ያዕቆብን ይዞ ወደ ታቦር ተራራ ወጣ፡፡ በዚያም እንደ ዮርዳኖስ ወንዝ መድኃኔዓለም ክብረ መንግስቱን ብርሃነ መለኮቱን ገልጧል ፡፡ከዘጠኙ ዐበይት በዓላት አንዱ የሆነው በዓለ ደብረታቦር የዚህ ታሪክ መታሰቢያ ነው ፡፡ 
ታቦር ተራራ ከገሊላ ባሕር በስተምዕራብ 17 ኪሎሜትር ርቀት ላይ ከናዝሬት ከተማ በስተምስራቅ ከዮርዳኖስ ወንዝ በስተምዕራብ አቅጣጫ ሲገኝ ከባሕር ጠለል በላይ 572 ሜትር ነው ፡፡ከላይ ወደታች ሲታይ ታቦር ተራራ ቅርጹ የተገለበጠ የሻይ ስኒ ይመስላል ይላሉ ፡፡

ምሥጢረ መንግሥቱን ለምን በታቦር ተራራ ገለጸው ?
መድኃኔዓለም ሌሎች ተራሮች እያሉ ክብሩን ለመግለጥ ስለምን ደብረ ታቦርን መረጠ ቢሉ ትንቢቱንና ምሳሌውን ለመፈጸም ነው፡፡
ትንቢት

ታቦር ወአርሞንኤም በስመ ዚአከ ይትፌሥሑ ወይሰብሑ በስምከ ” 

ታቦርና አርሞንኤም በስምህ አምነው በተደረገላቸው ነገር ደስ ይላቸዋል፣ ስምህን ያመሰግናሉ፣ ለስምህም ምስጋና ያቀርባሉ፡፡መዝ 8812
ምሳሌ
ባርቅ ሲሳራን ድል አድርጎበታል መሳፍንት 46 ይኸውም ታሪኩ እንዲህ ነው፡፡‹… የእስራኤል ልጆች በእግዚአብሔር ፊት እንደገና ክፉ ሥራ ሠሩ፡፡ እግዚአብሔርም በአሶር በነገሠው በከነዓን ንጉሥ በኢያቡስ እጅ አሳልፎ ሰጣቸው የሠራዊቱም አለቃ በአሕዛብ አሪሶት የተመረጠው ሲሣራ ነበርዘጠኝ መቶ የብረት ሰረገሎች ነበሩትና የእስራኤልንም ልጆች ሃያ ዓመት ያስጨንቃቸው ነበር›/መሳ 4.1-3/
ሁሌም ቢሆን የሰውን በደል ዐይቶ እንደወጣችሁ ግቡት፣ እንደገባችኋት ውጧት የማይልና ‹… ከፈተናው ጋር መውጫውን ደግሞ ያደርግላችኋልየተባለለት እግዚአብሔር ከዚህ ቀንበር የሚላቀቁበትን መላ ራሱ አመለከታቸው፡፡ /1ቆሮ. 10-13/፡፡
እስራኤላውያን ወደ ፈጣሪያቸው በጮኹ ጊዜ የለፊዶት ሚስት የሆነችውንና እስራኤልን በነቢይነትና ዳኝነት ታገለግል የነበረችው ነቢይቱን ዲቦራን ተጠቅሞ የማሸነፊያ መላውን አመለከታቸው፡፡ ነቢይቱ ዲቦራ ትንቢት ከመናገር አልፋ የእስራኤልን ንጉሥ ባርቅ ከእኔ ጋር ወደ ጦርነቱ ውጪ ብሎ ባስጨነቃት ጊዜ በጦር አዝማችነትም ተሳተፈች፡፡

እግዚአብሔር በነቢይቱ በዲቦራ በኩል ለእስራኤል ንጉሥሔደህ ወደ ታቦር ተራራ ውጡ…› ብሎ አዞት ነበርና ንጉሡ ዐሥር ሺሕ ብረት ለበስ ያልሆነ እግረኛ ሠራዊት ይዞ ደብረ ታቦርን ተማምኖ በተራራው ላይ መሸገ ጦርነቱ ሳይጀመር አለቀ፡፡ ምክንያቱምእግዚአብሔርም ሲሣራን ሰረገሎቹንም ሁሉ ሠራዊቱንም ሁሉ ከባርቅ ፊት በሰይፍ ስለት አስደነገጣቸው፡፡ ሲሣራም ከሰረገላው ወርዶ በእግሩ ሸሸ…› /መሳ. 4.15/

እስራኤል በእግዚአብሔር አጋዥነት በታቦር ተራራ ላይ የሃያ ዓመት የግፍና የሰቀቀን አገዛዝ ቀንበራቸውን ከትከሻቸው አሽቀንጥረው በምትኩ የድል ካባን ደረቡ ‹… በጦርነት ኃይለኞች ሆኑ የባዕድ ጭፍሮችንም አባረሩተብሎም ጀግንነታቸው ተጻፈላቸው፡፡ የታቦር ተራራ ያኔ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ባለውለታቸው ነበር፡፡ /ዕብ. 11.32-34/
ጌታም በልበ ሐዋርያት ያለ ሰይጣንን ድል ያደርግበታልና ማለትም በልባቸው ጥርጥርን እና ፍቅረ ሢመትን( የሥልጣን ፍቅር) ያሳደረ ዲያብሎስን ድል ነስቶላቸዋል ፡፡ከዚህም በመነሳት ነው በዓለ ደብረታቦር የደቀመዛሙርት ተማሪዎች በዓል ነው የሚባለው ፡፡

ለምን 3ቱን ሐዋርያት ( ጴጥሮስ ፤ዮሐንስ እና ያዕቆብን) ብቻ ይዞ ወደ ተራራ ወጣ፡-
ለፍቅሩ ስለሚሳሱ ነው፡፡ ይህም በዕብራይስጡ ኬፋ በግሪኩ ጴጥሮስ ፤በግዕዙ ኰኲሕ( ዐለት)
ተባለው የዮና ልጅ ስምዖን ጌታ እሞታለሁ እያለ ጌታችን ሲናገር አይሁንብህ በማለቱ ከባሕርይ አባቱ ከአብ እርሱን ስሙት የሚል መለኮታዊ ድምጽ ሰምቷል፡፡ዮሐንስና ያዕቆብ ጌታን ምድራዊ መሲህ አድርጎ በማሰብ ቀኝ ጌትነትን እና ግራ ጌትነትን በእናታቸው በኩል የማይገባ ልመና አቀረቡ ዮሐንስና ያዕቆብ እኔ የምጠጣውን ጽዋ ትጠጣላችሁ? ሲባሉ አዎ ብለው መለሱ በዚህም ከባሕርይ አባቱ እርሱን ስሙት የሚል ድምጽ ሰሙ፡፡

በይሁዳ ምክንያት ነው ኢሳ 26.13 ‹ኃጥእ ሰው የእግዚአብሔርን ክብር እንዳያይ ያርቁታልእንዲል እርሱን ጥሎ አስራ አንዱን ወደ ተራራ ይዞ ቢወጣ ከምሥጢር ቢለየኝ በሞቱ ገባሁበት እንዳይል፡፡ ያም ባይሆን ስምንቱ ደቀ መዛሙርት ለምን ይከለከላሉ ቢሉ አልተከለከሉም በርዕሰ ደብር (በተራራው አናት) ለሦስቱ ደቀ መዛሙርት የተገለጸው ምስጢር በእግረ ደብር (በተራራው ግርጌ) ለነበሩት ስምንቱ ደቀ መዛሙርት ተገልጦላቸዋል፡፡ ይህም በደብረሲና ለሰባው ሊቃናት የተገለጠ ምሥጢር በከተማ ለነበሩት ለኤልዳድና ሙዳድ እንደተገለጠ ማለት ነው፡፡ ዘኁልቊ 1126

ኤልያስና ሙሴን ለምን አመጣቸው?
- በአንድ ወቅት ነቢዩ ሙሴ እግዚአብሔርን ‹‹ወለእመሰ ረከብኩ ሞገሰ በኀቤከ አስተርእየኒ ገሐደ ሊተ ወአእምር ወእርአይከ ከመ ይኩነኒ ርኪበ ሞገሰ በቅድሜከ ዮም››  በአንተ ዘንድ ባለሟልነትን ማግኘቴ እውነት ከሆነስ ፊት ለፊት ተገልጸህልኝ ልይህና በአንተ ዘንድ ባለሟልነትን ማግኘቴን ልወቀውሲል ጠይቆት ነበር፡፡ እግዚአብሔርም ‹… ትሬኢ ድኅሬየ ወገጽየሰ ኢያስተርኢ ለከ፣ ጀርባዬን ታያለህ ፊቴን ግን አታይምብሎት ነበር፡፡ /ዘጸ. 33.13 እና 23/

የዚህ ኃይለ ቃል ትርጓሜና ሐተታ በደብረ ታቦር ተፈጸመ፡፡ እንዲህ ማለቱ በአምስት ሺሕ አምስት መቶ ዘመን ሰው ሆኜ ሥጋ ለብሼ ኋላ በደብረ ታቦር እስክገለጽልህ ድረስ አንተ በመቃብር ተወስነህ ትኖራለህ ማለቱ ነበር፡፡ ይህን ማለቱ እንደሆነ የታወቀው ግን በደብረ ታቦር ሙሴን ከብሔረ ሙታን አምጥቶ ባቆመው ጊዜ ነበር፡፡

- ልዑል እግዚአብሔር ነቢዩ ኤልያስንአንተሰ ትከውነኒ ስምዓ በደኃሪ መዋዕል፣ አንተ በኋለኛው ዘመን ምስክር ትሆነኛለህብሎት ነበርና ይኸውም ኃይለ ቃል ኤልያስ ከብሔረ ሕያዋን መጥቶየእኔን የኤልያስን ጌታ ማን ኤልያስ ነው ይልሃል እግዚአ ኤልያስ፤ አምላከ ኤልያስ ይበሉህ እንጂሲል በደብረ ታቦር ተፈጸመ፡፡ ታያለህ የተባለው ሙሴም አየ፣ ትመሰክራለህ የተባለው ኤልያስም መሰከረ፡፡
- በፊልጶስ ቂሳርያ ጌታ ሐዋርያትንሰዎች የሰውን ልጅ ማን እንደሆነ ይሉታል?› ብሎ በጠየቃቸው ጥያቄ ሲመልሱ ሙሴ ነው ይሉሃል እንዲሁም የኃይል ስራህን ተመልክተው ኤልያስ ነህ ይሉሃል ብለው ነበርና ሙሴን ከመቃብር ኤልያስን ከብሔረ ሕያዋን አምጥቶ እግዚአ ሙሴ አምላከ ሙሴ እግዚአ ኤልያስ አምላከ ኤልያስ መሆኑን ለማስመስከር፡፡


ታቦር ተራራ የወንጌል ምሳሌ 
1.
ተራራ ሲወጡት ያደክማል፣ ከወጡት በኋላ ግን ጭንጫውን፣ ግጫውን ሲያሳይ ደስ ያሰኛል፡፡ ወንጌልም ሲማሯት ትከብዳለች በኋላ ግን ጽድቅን እና ኃጢአትን ለይታ ስታሳውቅ ደስ ታሰኛለች፡፡

ታቦር ተራራ የቤተክርስቲያን ምሳሌ 
1.           በታቦር ተራራ ከብሉይ ኪዳን ነቢያት ኤልያስና ሙሴን፣ ከሐዲስ ኪዳን ሦስቱን ሐዋርያት እንደተገኙ በቤተክርስቲያን ብሉይ ከሐዲስ እንዲነገር ለማጠየቅ ሐዋርያት የሰበኩት ወንጌል አስቀድመው ነቢያት በምሳሌና በትንቢት የተናገሩት እንደሆነ ሲያስረዳ ነው ፡፡ ነቢያት በቀየሱ ሐዋርያት ገሰገሱ እንዲልበሐዋርያት በነቢያት መሠረት ላይ ታንጻችኋልኤፌ 220
2.           በታቦር ተራራ ከመዓስባን (ባለትዳር) ሙሴን ከደናግል ደግሞ ኤልያስ እንደተገኙ በቤተክርስቲያን በድንግልና የሚኖሩ መናንያን መነኮሳትም፣ በሕግ በሥርዓት የሚኖሩ ባለትዳሮችም ይገኛሉና፡፡

ታቦር ተራራ የመንግሥተ ሰማያት ምሳሌ 
1.     ተራራውን ችግር እንዲወጡት መንግሥተ ሰማያትንም በብዙ መከራ የምትገኝ ናትናእስመ በብዙኅ ጻማ ወድካም ኀለወነ ንባአ ለመንግሥተ እግዚአብሔር› ‹ወደ እግዚአብሔር መንግሥት በብዙ መከራ እንገባ ዘንድ ያስፈልገናልሐዋ 1422
2.     በታቦር ተራራ የብሉይ ኪዳን ነቢያት፣ ከሐዲስ ኪዳን ሐዋርያት እንደተገኙ መንግሥተ ሰማያትን ነቢያትም፣ ሐዋርያትም አንድ ሆነው እንደሚወርሷት ያጠይቃል፡፡3.     በታቦር ተራራ ከመዓስባን ሙሴ፣ ከደናግል ደግሞ ኤልያስ እንደተገኙ መንግሥተ ሰማያትን ደናግልም መዓስባንም በአንድ ላይ እንዲወርሷት ያጠይቃል፡፡4.     በታቦር ተራራ ሞተው ከተቀበሩት መካከል ሙሴን አመጣ፣ በብሔረ ሕያዋን ካሉት ደግሞ ኤልያስን አመጣ መንግሥተ ሰማያትንም ሞተው የተቀበሩትም በብሔረ ሕያዋን ያሉትም በአንድነት እንደሚወርሷት ያጠይቃል፡፡

በአጠቃላይ ታቦር ተራራ፡-
1.
 የክርስቶስ የባሕርይ አምላክነት የተመሠከረበት፣
2. የምስጢረ ሥላሴ ትምህርት የተሰጠበት
3. ፈጣሪ ከቅዱሳን ሰዎቹ ጋር የተገኘበት 
4. በልበ ሐዋርያት የነበረ ሰይጣን ድል የተደረገበት 
5. የሐዋርያት በተለይም የሦስቱ ባለሟልነት የተገለጠበት፣
6. አሉባልታና ተራ ወሬ የከሸፈበት፣
7. የቅዱሳንን ክብር ለሚያናንቁ ተራራም እንኳንቅዱስእንደሚባል የተማሩበት፣ 
8. የብሔረ ሕያዋን መኖር የተመሰከበረበት 
9. የትንሣኤ ሙታን ዋስትና የተገለጠበት የክብር ሰገነት፣ የምስጢረ መቅደስ፣ ታላቅ ትምህርት ቤትም ጭምር ነው፡፡

ቅዱስ ጴጥሮስ ጌታ ሆይ በዚህ መኖር ለእኛ መልካም ነው ማለቱ 
1.     የኢየሱስ ክርስቶስ የባሕርይ አምላክነት በሚታመንበት፣ ዋልድ ዋሕድ በምትለው ሃይማኖት መኖር ለእኛ መልካም ነው፡፡
2.      መድኃኔዓለም ከቅዱሳን ወዳጆቹ ጋር በምትገኝበት አንተ እያበላኸን እየፈወስከን፣ ሙሴ ደመና እየጋረደ መና እያወረደ ባሕር እየከፈለ፣ ኤልያስ ሰማይ እየለጐመ እሳት እያዘነመ ዝናም እያቆመ በዚህ መኖር ለእኛ መልካም ነው፡፡
3.     በልበ ሐዋርያት ያደረ ሰይጣን ድል በተደረገበት በታቦር ተራራ ምሳሌ አንድም በወንጌል ሕይወት፣ አንድም በቤተ ክርስቲያን መኖር ለእኛ መልካም ነው፡፡

ፈጣሪያችን እግዚአብሔር እስከመጨረሻዋ ሕቅታ (እስትንፋስ) በታቦር ተራራ በተመሰለች ቤተክርስቲያን በሃይማኖታችን ጸንተን የመንግሥተ ሰማያት ወራሾች የስሙ ቀዳሾች እንድንሆን የእግዚአብሔር ቸርነት የድንግል ማርያም አማላጅነት አይለየን፡፡

1 comment:

  1. Kale Hiywot Yasemanlin Wendimchen. D. Melaku Azeew. Very details and interesting lONG LIVE FOR TEWAHEDO EMINETACHIN.

    ReplyDelete