Saturday, March 5, 2016

"በዛቻና በማስፈራራት የባከኑት የፓትርያርክ አቡነ ማትያስ ሦስት ዓመታት"


እነሆ የኢትዮጵያ በራሷ መመራት ከጀመረች 57 ዓመት ሊሞላት ጥቂት ወራት ቀራት፡፡ በእነዚህ 57 ዓመታት ውስጥ አሁን በመንበሩ ላይ ያሉትን ሳይጨምር 5 ፓትርያርኮችን አስተናግዳለች፡፡ እነዚህ አባቶች በዘመናቸው በቤተ ክርስቲያንና በምድሪቱ ላይ የራሳቸውን አሻራ አሳርፈው አልፈዋል፡፡

አቡነ ማትያስ ስድስተኛው የቤተ ክርስቲያናችን ፓትርያርክ ሲሆኑ ከቀናት በኋላም ሦስተኛ ዓመት በዓለ ሢመታቸውን ያከብራሉ፡፡ እኔም “መቼም ክፉም ይሁን ደግ ታሪክ ነውና መጻፍ አለበት”የሚለውን የአባታችንን ቃል መነሻ በማድረግ ለበዓለ ሢመታቸው መታሰቢያ ይህንን መጣጥፍ አዘጋጀሁ፡፡ (በትምህርተ ጥቅስ ውስጥ ያለው ቃል አቡነ ማትያስ ራሳቸው በኢትኦጵ መጽሔት ላይ ስለ አቡነ ጳውሎስ ጉዳይ ሲጽፉ የተጠቀሙት ነው፡፡) መቼም የቤተ ክህነቱ ሹማምንት የቅዱስ ሲኖዶስን ልዕልና እና የሐሳብን ልዕልና አጥብቀው ቢጋፉም፣ አንጻራዊ ነጻነቴን ማለትም ቢያንስ የቤተ ክህነቱ ሠራተኛና የየትኛውም ማኅበር አባል አለመሆኔን ተጠቅሜ ፣ ጥቂት ልተንፍስ፡፡
ከዚያ በፊት ይችን፡-
በአንድ አባት ዘመነ ፕትርክና ነው አሉ፡፡ በቤተ ክህነቱ ብልሹ አሠራር ክፉኛ የተማረሩ ምእመን ፓትርያርኩ ባሉበት ስብሰባ ላይ ስለ ሙስናውም፣ ስለ ዘረኝነቱም፣ ስለ ኑፋቄውም እውነት እውነቱን በድፍረት ሲያወሩ የተደናገጡት ፓትርያርክ አጠገባቸው ወዳሉት አማካሪያቸው ዞር ብለው፣ “(ብሔራቸውን መሰለኝ) ይህ ሰው ከየት ነው? የትስ ነው የሚሠራው?”ብለው ጠየቁ፡፡ አማካሪያቸውም “ከእኛ ነው፡፡ ግን የቤተ ክህነት ሠራተኛ አይደለም፡፡”ብለው መለሱላቸው፡፡ እሳቸውም “….እህ! ለዚያ ነዋ!... በል ቀጥል የልብህን ተናገር፡፡”አሉ ይባላል፡፡ ወደ ነገሬ፡፡


አቡነ ማትያስ-ቅድመ ፕትርክና
በአብዮቱ ዋዜማ የአሁኑ ፓትርያርክ የቀድሞው አባ ተክለ ማርያም አስራት ከሚለው ስማቸው ጋር ነበር ወደ ሀገሪቷ መዲና የመጡት፡፡ ሲመጡም በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል በቀዳሽነት አገልግለዋል፡፡ ከሦስት ዓመታት ቆይታ በኋላ የመናኙ የአቡነ ተክለ ሃይማትን ወደ ፕትርክና መምጣት ተከትልው በ1968 ዓ.ም የፓትርያርኩ አቡነ ቀሲስና ምክትል ልዩ ጸሐፊ ሆነው ተሹመዋል፡፡ ለዚህ ሹመት ያበቃቸው ወታደራዊው ደርግ በወቅቱ ይከተለው የነበረው ርዕዮተ ዓለም እና የአባ ተክለ ማርያም ተክለ ቁመናና የፊት ገጽታ ነው፡፡

አቡነ ቴዎፍሎስን ጨምሮ በርካታ ሰዎችን በግፍ የገደለው የደርግ አገዛዝ ለንጉሣውያኑ ከነበረው ጥላቻ በመነሣት ከነገሥታቱ ጋር ግንኙነት የነበራቸውን ጳጳሳት በሞት፣ በእስር፣ በጡረታና በስደት ከቤተ ክህነቱ ሲያስወግድ በምትኩ ከነገሥታቱ ጋር ፈጽሞ ግንኙነት የላቸውም ብሎ ያመነባቸውን መናኙን አባት አቡነ ተክለ ሃይማኖትን ወደ ፕትርክናው አምጥቷል፡፡ በወጀብና በአውሎ ነፋስ ውስጥ መንገድ ያለው እግዚአብሔር በዚህ የደርግ የከፋ ሂደት እኒያን የመሰሉ ቅዱስ አባትን ለምድራችን አበርክቶልናል፡፡

የአቡነ ተክለ ሃይማኖት ፍጹም መናኝነት ለደርግ ምቾት አልሰጠውም፡፡ በባዶ እግራቸው መሄድ፣ የላመ የጣመ አለመብላት፣ በወርቅ የተንቆጠቆጠ ልብስ አለመልበስና፣ በአጠቃላይ ወቅቱ ለሚፈቅደው መንግሥታዊ ሥነ ሥርዓት (ፕሮቶኮል) አለመገዛት፣ የአብዮቱን ልጆች ረፍት ነሳቸው፤ ለዚህም መፍትሔ ያደረጉት ባለ ግርማ ሞገስ የሆኑ አባትን በረዳትነት መመደብ ነበር፡፡ በዘመናዊ ትምህርት እስከ 12ኛ ክፍል ድረስ ተምረዋል የሚባሉት የአሁኑ ፓትርያርክ አባ ማትያስ፣ በተክለ ቁመናቸው ማራኪነትና በጺማቸው ውበት ለዚህ ተመራጭ ሆነው መቅረባቸው ይነገራል፡፡

በደርግ መንግሥት መወደድን ያገኙት አባ ተክለ ማርያም አስራት፣ በ1969 ዓ.ም ከሌሎች መልእክትኞች ጋር በመሆን ወደ ጎንደር ተጉዘው ለኢዲዩ ድጋፍ እየሰጠ የነበረውን የቤጌምድር ደገኛ አርፎ እንዲቀመጥና ለደርግ እንዲገዛ ሊያስጠነቅቁ ተልከው ነበር፤ ስለ ጉዞው ዓላማ ብርሃኑ አስረስ፤ “ማን ይናገር የነበረ …የታሕሣሡ ግርግርና መዘዙ”በሚለው መጽሐፋቸው ላይ አንዲህ ይላሉ፡- “ጉዳዩ ኢዲዩ (EDU) የተባለ መንግሥትን የሚቃወም ኃይል በበጌምድርና ስሜን ጠቅላይ ግዛት ተነሥቶ ቆላውን ይዟል፡፡ ወደ ደጋውም እየወጣ ነው፡፡ ደገኛው ከቆለኛው ጋር እንዳይተባበር መምከርና ማቆም አለባችሁ፡፡ ይህ ባይሆን ግን ደገኛው ከቆለኛው ጋር ከተባበረ መንግሥት ሥልጣኑን በዋዛ አይለቅም፡፡ ያለ የሌለ ጉልበቱን ተጠቅሞ መንግሥቱን ለማቆየት ይሞክራል፡፡ ….ከደርግ አባላት ጋር ሄዳችሁ መክራችሁ ነገሩን እንድታቀኑ ነው የተፈለጋችሁት…” (ገጽ 401)

ይህ በሆነ በሁለተኛ ዓመቱ በ1971 ከዶ/ር ክነፈ ርግብ ጋር ጥብቅ የሆነ ግንኙነት የነበራቸው አባ ተክለ ማርያም አስራት አቡነ ማትያስ በመባል የኢየሩሳሌም ሊቀ ጳጳስ በመሆን ተሹመው እስከ 1974 ዓ.ም ድረስ ለሦስት ዓመታት አገልግለዋል፡፡ (ክነፈ ርግብ በኮሎኔል አጥናፉ አባተ ተቋቁሞ የነበረውን “የጠቅላይ ቤተ ክህነት ጊዜያዊ የሽግግር ጉባኤ”በሊቀ መንበርነት የመሩ ናቸው፤ ጉባኤው በድኅረ አብዮት ቤተ ክህነት ላይ በርካታ ውሳኔዎችን ወስኗል፡፡)

የአቡነ ማትያስ የኢየሩሳሌም ቆይታ በመወገዝ ነበር የተፈጸመው፡፡ በአቡነ ተክለ ሃይማኖት የሚመራው የወቅቱ ሲኖዶስ አቡነ ማትያስ ላይ በተደጋጋሚ የቀረበን አቤቱታ ለማጣራት ጥሪ ቢያድርግላቸውም፣ ወደ ኢትዮጵያ ለመምጣት ስላልፈቀዱ፤ ቤተ ክርስቲያኒቱ በታሪኳ (ከኮፕት ቤተ ክርስቲያን ነጻ ከወጣች በኋላ) የመጀመሪያውን ውግዘት በአቡነ ማትያስ ላይ አካሄደች፡፡ (Widu፡ ገጽ 366)፡፡ በስማቸው ሌላ ጳጳስ ሾመች፤ አሁንም በቤተ ክርስቲያኒቱ ሁለት አቡነ ማትያሶች ይገኛሉ፡፡ የተወገዙት የአሁኑ ፓትርያትክ አቡነ ማትያስም ጓዛቸውን ሸክፈው ወደ ሰሜን አሜሪካ ተጓዙ፡፡

የአቡነ ማትያስ መወገዝ በሲኖዶስ ይነሣ አይነሣ የሚለውን ለማረጋገጥ የጽሑፍም ሆነ የሰው ማስረጃ ባላገኝም፤ ለበዓለ ሢመታቸው የታተመ “የብፁዕ አቡነ ማትያስ አጭር የሕይወት ታሪክ” የሚል መጽሐፍ ግን እንዲህ ይላል፡- - “ከ3 ዓመታት የኢየሩሳሌም ቆይታ በኋላ በነበረው ወቅታዊ ችግር ምክንያት በ1974 ዓ.ም በስደት መልክ ወደ አሜሪካን ሀገር ተሻግረው ለ10 ዓመታት ያህል ለስደተኞች ኢትዮጵያውያን መንፈሳዊ አገልግሎት ሲሰጡ ከቆዩ በኋላ እርቀ ሰላም ወርዶ በ1984 ዓ.ም ቅዱስ ሲኖዶስ ጠርቶ ወደ አዲስ አበባ በማስመጣት የአሜሪካንን ሀገረ ስብከት አጽድቆላቸው ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ በአሜሪካን አህጉረ ስብከት እየተዘዋወሩ ለ15 ዓመታት ያህል ሐዋርያዊ አገልግሎታቸውን ሲያበረክቱ ቆዩ፡፡” (ገጽ 9)

የ15 ዓመታት የአሜሪካ ቆታቸው መንገራገጮች የበዙበት፤ ከአምስተኛው ፕትርያርክ ጋር ስምም እንዳልነበሩ፤ አብዝተውም በተለያዩ ሚዲያዎች ይሞግቷቸው እንደነበረ የተለያዩ መረጃዎች ይናገራሉ፡፡ አቡነ ማትያስ በአንድ ወቅት ለ”ኢትኦጵ”መጽሔት በላኩት ጽሑፍ ላይ አምስተኛው ፓትርያርክ ለሲኖዶሱ “ክብር የሌላቸው”፤ “ለሲኖዶሱ የማይታዘዙ”፤ “በሲኖዶስ ስም የሚያጭበረብሩ”፤ “የሰው ሀሳብ የማይቀበሉ”፤ “ተርእዮ (እዩኝ እዩኝ) ያለባቸው” በሚሉ ጉዳዮች ከስሰዋቸው የነበረ ሲሆን፤ ከአቡነ ተክለ ሃይማኖት ያላነሰ መወገዝም አድርሰውብኛል ብለው ሀሳባቸውን እንዲህ አስፍረዋል፡፡ “… የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቀኖና፣ አንድ ጳጳስ በሕይወት እያለ ሌላ ጳጳስ በስሙ አይጠራበትም ነበር፡፡ ሟቹ ተክለ ሃይማኖት አረመኔውን ደርግን ለምን አወገዝህ ብለው በሕይወት እያለሁ ከቀኖና ቤተ ክርስቲያን ውጭ የእኔውን ስም ሌላ ሰው ሰየሙበት፡፡ አሁን ደግሞ ፓትርያርክ ጳውሎስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ከፈጸሙት ድርጊት ባላነሰ ሁኔታ ማትያስ ወዳለበት አካባቢ ሌላ ማትያስ መላካቸው ሆነ ብለው ለማደናገር የፈጸሙት ተግባር መሆኑን ለማንም ምስጢር አይሆንም…፡፡” (ገጽ 240)

መጽሔቱ ለጽሑፋቸው “አትምጡ ስንላቸው መጥተው እኛንም በገማ እንቁላል እስደበደቡን” የሚል ርዕስ ሰጥቶት ነበር፡፡ አቡነ ማትያስ ከ1999 ዓ.ም ጀምሮ ፓትርያርክ እስከሆኑበት ዓመት ድረስ ለስድስት ዓመታት በውግዘት ወደ ተሰናበቷት ኢየሩሳሌም በመሄድ ሊቀ ጳጳስ ሆነው አግልግለዋል፡፡

አቡነ ማትያስ ድኅረ ፕትርክና
ገና ከምርጫው ዋዜማ ጀምሮ “ኢትዮጵያዊ ሳይሆኑ አሜሪካዊ ነዎት” በሚል ዜግነታዊ ጉዳይ ከአንዳንድ አባቶች ጋር ውዝግብ ውስጥ የገቡት አቡነ ማትያስ፤ የካቲት 21 ቀን 2005 ዓ.ም ስድስተኛው ፓትርያርክ ሆነው በጠቅላይ ቤተ ክህነት አዳራሽ ተመረጡ፡፡ በጊዜው መንበሩን ይረከባሉ ተብለው በብዙዎች ቅድመ ግምት የተሰጣቸው በበርካታ ምእመናን ዘንድ ተወዳጅ የሆኑት ሌላ አባት ነበሩ፡፡ በተቃራኒው ግን ምክንያቱ ብዙም ግልጽ ባልሆነና ይፋ ባልወጣ ጉዳይ እኚህ አባት እጩ ሆነው ሳይቀርቡ ቀሩ፡፡ የእኚህ አባት እጩ ሆኖ ያለመቅረብና የአቡነ ማትያስ የዜግነት ጉዳይ በምርጫው ሂደት ላይ የራሱን አሉታዊ ጥላ ከማሳረፉ በላይ፣ የምርጫውን ተአማኒነት ጥያቄ ውስጥ ከቶት ነበር፡፡ ቢሆንም ግን ድምጽ ከሰጠው 806 ሰው፣ 500 ድምጽ “አግኝተው” አዲስ አጀንዳን ይዘው በአዋጅ ወደ መንበሩ መጡ፡፡

ወቅቱ ቤተ ክህነቱ በክፉ ዘረኝነት፣ በሙስና፣ በኑፋቄና በአጠቃላይ በብዙ ችግሮች የተዘፈቀበት ስለሆነ፤ ምእመኑ ይህንን ችግር የሚቀርፍ ጠንካራ መንፈሳ አባት አጥብቆ ይሻ ነበር፡፡ ይህንን ዘርፈ ብዙ ችግር ያወቁ የመሰሉት ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ፤ ገና ከመነሻቸው ሙስናና ሙሰኞች ላይ ጠንከር ያለ ማስፈራሪያ በመሰንዘር ወደ ሕዝበ ክርስቲያኑ ልብ ውስጥ ገቡ፡፡ በተገኘው መድረክ ሁሉ በሙሰኞች እና በመልካም አስተዳደር ችግር ፈጣሪዎች ላይ የማያዳግም እርምጃ ለመውሰድ የእርዱኝ ጥያቄን አቀረቡ፡፡ ብዙዎች የሐሳባቸው ደጋፊ በመሆን ሊረዷቸው ቃል ገቡ፡፡

ለዚህ እንቅስቃሴ ይረዷቸው ዘንድ በራሳቸው በፓትርያርኩ አቅራቢነት የጅማ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ አቡነ እስጢፋኖስን ወደ መዲናዋ በማምጣትና የአዲስ አበባን ሀገረ ስብከት እንደመነሻ በማድረግ የአስተዳደሩንና የሙስናውን ችግር ይፈታል ያሉትን መዋቅራዊ ጥናት እንዲጠና አስወሰኑ፡፡ ጥናቱም ሀገሪቷ ውስጥ አሉ በሚባሉ ኦርቶዶክሳውያን ልሂቃን ቀንና ሌሊት ተሠርቶ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለውይይት ቀረበ፡፡ የቀረበው ጥናት የመፍትሔ አቅጣጫዎችን ያስቀመጠና ለተግባራቂነት የተዘጋጀ ከመሆኑ በላይ፤ ፕትርያርኩን ጨምሮ በከፍተኛ የመንግሥት አካላት ሳይቀር የተደነቀና የተወደሰ ነበር፡፡ ግን በጥናቱ ተጎጂ በሚሆኑ በኃላፊነት ላይ ባሉ ሙሰኛ ሹማምንት፣ የቤተ ክርስቲያኒቱን ውድቀት በሚሹ ዘረኞችና በተሐድሶ መናፍቃን በተቀነባበረ ዘዴ ከሽፎ ቀረ፡፡ አጥኝዎቹም ሞራላቸው ክፉኛ ተነካ፡፡ የጥናት ቡድኑን በኃላፊነት ሲመሩ የነበሩት አቡነ እስጢፋኖስም በይፋ ከፓትርያርኩ ጋር መሥራት እንደማይችሉ ተናግረው ወደ ጅማ ሀገረ ስብከት ተመለሱ፤ ከፊሎቹ የጥናት ቡድኑ አባላት ደግሞ፤ በስድስተኛው ፓትርያርክ ዘመን የቤተ ክህነቱን ግቢ ጨርሶ እንደማይረግጡት ምለው ወደየሥራቸው ሄዱ፡፡ ፓትርያርኩ ጥናቱን ያከሸፉበት ምክንያት በጥናት ቡድኑ ውስጥ የማኅበረ ቅዱሳን አባላት መኖራቸው እንደሆነ በተለያዩ ሚዲያዎች ተነገረ፡፡

ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ በሁለተኛው ዓመት በዓለ ሢመታቸው ማግስት ከሙስናና ከመልካም አስተዳደር በመቀጠል ሁለተኛውን የዛቻ ምዕራፍ በማኅበረ ቅዱሳን ላይ ከፈቱ፡፡ ባይሳካላቸውም እንኳ “ሙስናና ብልሹ አሠራርን ላጥፋ አግዙኝ” ያሉት አባት፣ አሁንም “ማኅበረ ቅዱሳንን ላጥፋ እባካችሁ እርዱኝ” ማለት ጀመሩ፡፡ ኅብረታቸውንም በፊት አጠፋዋለሁ ብለው ከዛቱበት ክፉ ተግባር አራማጆች (ከሙሰኞቹና ከተሐድሶዎቹ) ጋር በማድርግ እስከ ሕይወታቸው ፍጻሜ ድረስ ማኅበረ ቅዱሳንን እዋጋዋለሁ፤ አጠፋለሁ ብለዋል ሲል ሐራ-ተዋሕዶ የተሰኘው ድረ-ገጽ ዘግቦት ነበር፡፡

አቡነ ማትያስ በዚህ ብቻ አላበቁም፤ በቤተ ክርስቲያኒቱ ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ፤ ለመንበሩም በማይመጥን ከፍተኛ የሆነ የሕግ ጥሰትና የተዋረድ ችግር ያለበት፤ ማኅበሩን ለክፉ አሳልፎ የሚሰጥ ደብዳቤን በምድሪቱ ላይ በተኑ (ይህን ደብዳቤ ሳይ የንጉሥ አርጤክስስንና የእስራኤላዊቷ አስቴርን የሰመረ ግንኙነት ያለወቀው ሐማ፣ በእስራኤላውያን ላይ የበተነውን የሞት ደብዳቤ አስታወሰኝ፡፡ ሙሉ ታሪኩን እዚህ መጥቀስ ጊዜ ቢወስድም፣ የደብዳቤው መጨረሻ ግን ሐማ በጠላቶቹ ላይ የደገሰው ሞት ለእሱ ፍጻሜ እንደሆነው ነው)፡፡

ፓትርያርኩ በማኅበረ ቅዱሳን ላይ የያዙት የአጠፋሃለሁ ማስፈራሪያና ዛቻ የማኅበሩን ወቅታዊ ሁኔታ ካለማወቅ የመነጨ ይመስለኛል፡፡ ማኅበረ ቅዱሳን መንፈስ ነው፤ የእነዚያ የቅዱሳን አባቶች መንፈስ፡፡ እሳቸው በውስጤ የለም ብለው ካልካዱ በቀር፣ አባል በሆኑትም ሆነ ባልሆኑት ውስጥ ያለ የአባቶቻችን መንፈስና እውነተኛ የቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ መንገድ ነው፡፡ ምናልባት ጊዜው ፈቅዶ እውቅናውን መቀማት ይቻል ይሆናል፤ ነገር ግን እሳቸውን ጨምሮ፤ ምንም ዓይነት ምድራዊ ኃይል፣ ውስጣችን ያለውን ማኅበረ ቅዱሳንን ማጥፋት አይችልም፡፡

ማኅበረ ቅዱሳንን ለምን?
የዛሬን አያድርገውና አቡነ ማትያስ ወደ መንበረ ፕትርክናው ከመምጣታቸው በፊት፤ ቀና የሆነ አመለካከትና የዓላማው ደጋፊ ነበሩ፤ ከዚያም በላይ በአደባባይ የማኅበረ ቅዱሳን ምስክር ሆነው ይቀርቡ ነበር፡፡ አቡነ ማትያስ በሙስና አይታሙም ይባላል እንጂ፣ ዛሬ ላይ የአማሳኞቹ ቡድኖች ምርኮኛ ሆነዋል ብየ አምናለሁ፡፡ ፓትርያርኩ በኑፋቄ አይጠረጠሩም፤ ነገር ግን ለተሐድሶዎች ከለላ የሆኑ ይመስለኛል ብየ አስባለሁ፡፡ እርግጥ ነው ማኅበረ ቅዱሳን ይዞት ከተነሳው ዓላማ አንጻር መናፍቃን እንደሚፈታተኑት፤ እውነት ነው ማኅበሩ የቤተ ክርስቲኒቱን ውድቀት ለሚመኙ ሰዎች የጎን ውጋት እንደሆነ፣ የማኅበሩ ህልውና የእነሱን ሞት እንደሚያፋጥነው ሙሰኞቹና መናፍቃኑ ጠንቅቀው ያውቃሉ፡፡ ግን ፓትርያርኩን ምን አደረጋቸው? ለምንስ ፊታቸውን አዞሩበት? ለምንስ ለጠላት አሳልፈው ሊሰጡት ወደዱ?

ይህንን ጽሑፍ ስጽፍ ካነጋገርኳቸው ሰዎች ከፊሎቹ ለዚህ ጥያቄ የፓትርያርኩን ከሦስት አስርት ዓመታት ባላይ ከኢትዮጵያ ርቆ መቆየትና ለቤተ ክህነቱ ፖለቲካ ባዕድ መሆንን እንደምክንያት ሲያቀርቡ፣ ባለፉት ዓመታት ፓትርያርኩ ከአቡነ ተክለ ሃይማኖት ጋር የነበራቸው ግንኙነትና በኋላ የተፈጠረው ልዩነትን፣ ከደርግ መንግሥት ጋር የነበራቸው ፍቅርን እና ዘግይቶ የተከሰተውን ፀብ፤ ማኅበረ ቅዱሳንን ይመለከቱበት የነበረው የስስት ዓይን መቀየሩን ወዘተ በመጥቀስ የአቡነ ማትያስን ምንታዌ ባሕርያት እንደ ምክንያት ያቀርባሉ፡፡ ጥቂቶችም የመናኙ አባት የአቡነ ተክለ ሃይማኖት ውግዘት እርሳቸው አሁን ላሉበት ያለ መረጋጋት ሁኔታ ዳርጓቸዋል ይላሉ፡፡ እኔም ከዚህ በተለየ ሁለት ጉዳዮችን ምክንያት አደርጋለሁ፡፡

የመጀመሪያው ጥሩ ያልሆነ ስሜታቸው ምክንያት በቤተ ክርስቲያንና በማኅበረ ቅዱሳን ታሪካዊ ጠላቶች እየተቀነባበረ የሚቀርብላቸው ማኅበሩ ባልነበረበት ዘመን እንኳ ከዚህ ዓለም ላለፉ አባቶች የሞት ምክንያት በማድረግ ማኅበሩን እንደ ደም አፍሳሽ አድረጎ በማስፈራሪያነት የመጠቀም ሂደት ነው፡፡ ይህ ፓትርያርኩን የማሸማቀቂያ ክስ ግዘፍ የሚነሳው ከዚህ ቀደም የሞቱት አባቶች ለሞታቸው ምክንያት ማኅበሩን መንካታቸው ነው በሚል ወሬና ወሬውንም በተደጋጋሚ ፓትርያርኩ ጆሮ በማድረስ ነው፡፡ ይህ ወሬ ማኀበሩና ፓትርያርኩ ባይነ ሥጋ እየተያዩ እንዳይነጋገሩ ከማድረጉም በላይ ማኅበረ ቅዱሳንን ክፉኛ እንዲፈሩና አጥብቀው እንዲጠሉ አድርጓል፡፡

ሌላኛው ፓትርያርኩ ሙሉ ጊዜያቸውን ማኅበሩን ለማጥፋት እንዲሠሩ ያደረጋቸው ምክንያት፣ ለማኅበረ ቅዱሳን መጠንሰስ ቀዳሚ ተጠቃሽ ለሆኑት ለቅዱሱ አባት ለአቡነ ጎርጎርዮስ ካልእ ሊቀ ጳጳስ ዘሸዋ ያላቸው ለዘመናት ተዳፍኖ የቆየ አሉታዊ አመለካከት ነው፡፡ አቡነ ጎርጎርዮስ እና አቡነ ማትያስ ዘመነኞች ናቸው፤ ሁለቱም በ1971 ዓ.ም ነበር የጰጰሱት፡፡ ለዚህ ጽሑፍ ይረዳኝ ዘንድ ያነጋገርኳቸው አንድ ማኅበረ ቅዱሳንን ለመመስረት ከፍተኛ አስተዋጽዖ ያበረከቱ የዝዋይ ገዳም አባት እንዳጫወቱኝ፣ አቡነ ጎርጎርዮስ በአቡነ ማትያስ ደስተኛ አልነበሩም፤ በወቅቱ አቡነ ማትያስ ከፖለቲካውና ከፖለቲከኞቹ ጋር የነበራቸው ፖለቲካዊ ቅርበት እንደነበርና አቡነ ጎርጎርዮስ በአቡነ ማትያስ መወገዝ ላይ ከፍተኛ ሚና መጫወታቸውን አውግተውኛል፡፡

በአቡነ ጎርጎርዮስ የተጻፈውና በቤተ ክርስቲያኒቱ የጥናት መስክ ላይ ተጠቃሽ የሆነው አሁንም በተደጋጋሚ እየታተመ አገልግሎት እየሰጠ ያለው “የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ”የተሰኘው መጽሐፍ ገጽ 84 ላይም በእነ አቡነ ማትያስ ዘመን የነበሩትን 22 ጳጳሳት ከነሓላፊነታቸው ሲጠቅስ፤ አቡነ ማትያስን ግን በመወገዛቸው ምክንያት አልጠቀሳቸውም፡፡ ይህም አቡነ ማትያስ ጮኽ ብለው የማያወሩትን የውግዘታቸውን ጉዳይ ዘላለም እንድናስታውስ ያደርገዋል፡፡

ሌላው ማኅበሩ የትምህርት ተቋማቱን በአቡነ ጎርጎርዮስ ስም መሰየሙ፤ በተለያዩ ቦታዎችና በኅትመት ውጤቶቹ ላይ ለቤተ ክርስቲያን ካደረጉት አስተዋጽኦ አንጻር ደጉን አባት መዘከሩ በፓትርያርክ አቡነ ማትያስ ዘንድ ካለመወደዱም በላይ፤ ታሕታይ ምስቅልቅል የፈጠረባቸው ይመስላል፡፡

ስደመድመው
ቤተ ክርስቲያኒቱ በ57 ዓመታት ታሪኳ ውስጥ እንደዚህ ጊዜ በብዙ የቤት ሥራዎች የተወጠረችበት ወቅት የለም፡፡ በአንጻሩም እንደዚህ በከንቱ የባከኑ ሦስት ዓመታትም አጋጥሟት አያውቅም፡፡

ፓትርያርክ አቡነ ባስልዮስ በሦስት ዓመታት የፕትርክና ጊዜ ውስጥ የስብከተ ወንጌል ድርጅት አቋቁመዋል፤ 17 ሊቃነ ጳጳሳትን ሾመዋል፡፡ ፓትርያርክ አቡነ ቴዎፍሎስ የልማት ኮሚሽንን መሥርተዋል፤ ሰበካ ጉባኤን አቋቁመዋል፤ 7 ሊቃነ ጰጳሳትን ሾመዋል፡፡ መናኙ አባት ፓትርያርክ አቡነ ተክለ ሃይማኖት 28 ጳጳሳትን ሾመዋል፤ ተዘግቶ የነበረውን ሰዋስወ ብርሃን ኮሌጅ አስከፍተዋል፤ ለአብነት መምህራን ደመወዝ እንዲከፈላቸው አድርገዋል፡፡ በአስቸጋሪ ወቅት የነበሩት ፓትርያርክ አቡነ መርቆርዮስ (አባ ዘሊባኖስ) ቢያንስ 6 ጳጳሳትን ሾመዋል፡፡ 

በበርካታ አወዛጋቢ ጉዳዮች የሚታወቁት ፓትርያርክ አቡነ ጳውሎስ እንኳ በሦስት ዓመት ውስጥ በርካታ ጳጳሳትን በመሾም አህጉረ ስብከትን አስፋፍተዋል፡፡ አገልግሎት አቁሞ የነበረውን ቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅን አስከፍተዋል፡፡ ፓትርያርክ አቡነ ጳውሎስ፣ ሲኖዶሳዊ የሕግ ማሕቀፍ በማበጀት ከማኅበረ ቅዱሳን ጋር አብረው ለመሥራት ተስማምተዋል፡፡ የቀደሙት ፓትርያርኮች ይህንና ሌሎች መልካም ተግባራትን በተሾሙ በሦስት ዓመታት ውስጥ ሲፈጽሙ፤ ስድስተኛው ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ ግን ከወረቀት ያለፈ ይህ ነው የሚባል ተግባር የፈጸሙ አይመስለኝም፡፡
የፓትርያርክ አቡነ ማትያስ የሦስት ዓመታት የሥራ ፍሬዎች ከብፁዓን አባቶች ጋር በስምምነት አለመሥራት፣ ያለምንም መንፈሳዊ ፋይዳ አሜሪካ መመላለስ (በሦስት ዓመት ውስጥ ሁለት ጊዜ ሂደዋል)፣ የማኅበረ ቅዱሳንን ጉባኤያት፣ የውይይት መድረኮችና የቴሌቭዥን ፕሮግራምን ማገድ፣ ማኅበሩን ማዕከል ያደረጉ ደንቦችና መመሪያዎችን በማዘጋጀት ከአገልግሎት ማደናቀፍ ወዘተ ናቸው የሚል ግምት አለኝ፡፡

ነገሮች ከቁጥጥር ውጭ ከመሆናቸው በፊት፣ ፓትርያርኩ ያሳለፏቸውን ሦስት ዓመታት በማስተዋል መገምገምና መጭውን የመንፈሳዊ የአገልግሎት ዘመናቸውን ቢያጤኑት እላለሁ፡፡
የማኅበረ ቅዱሳን አምላክም ይርዳቸው፡፡

(ተስፋዬ አ. “አዲስ ገፅ”1ኛ ዓመት ቁ.7 2008)

1 comment:

  1. It is amazing story and i got a lot of awareness from this article. God bless you brother.
    your sister in Christ.

    ReplyDelete