በዲ/ን ብርሃኑ አድማስ
እንኳን ለእመቤታችን በዓለ ዕርገት አደረሳችሁ፡፡
ዘሰ ይብል አፈቅረከኪ ወኢያፈቅር ተአምርኪ[ትንሣኤኪ ወዕርገትኪ] ክርስቲያናዊ፤
ኢክርስቱን ውእቱ አይሁዳዊ ወሠርፀ እስጢፋ ሐሳዊ፤
አንሰ እቤ በማኅሌተ ሰሎሞን ሰንቃዊ፤
አፈቅሮ ለፍግዕኪ ወለተ ይሁዳ ወሌዊ፤
ከመ መርዓቶ ያፈቅር ጽጌኪ መርዓዊ፡፡
(አንድ አድርገን ነሀሴ 17 2005 ዓ.ም)፡-እንደ ይሁዳ ስሙን የሚቃረን ግብር ሁልጊዜም የሚሠራውና ራሱን ‹‹ አባ ሰላማ ›› ብሎ የሚጠራው የተሐድሶዎች ብሎግ አንድ የሚያስደንቅ ጽሑፍ ሰሞኑን አስነብቦናል፡፡ የሚያስደንቅ ያልኩት ራሴን ባስደነቁኝ ሦስት ምክንያቶች ነው፡፡ የመጀመሪያው ለርእስነትና ሐሳቡን ለማስተላለፍ መሪ አድርጎ የተጠቀመው ጥቅስ መልእክቱ ከነገረ ጉዳዩ ያለውን ርቀትና አንድ ሰው ከካደ በኋላ ጥቅሶችን እስከምን ድረስ ሊያጣምም እንደሚችል ሳስብ አሁንም እደነቃለሁ፡፡ ሁለተኛ ደግሞ ክርስትና ከተመሠረተበትና በይፋ በብዙዎች ተቀባይነት እያገኘ ከመጣበት ከዘመነ ሐዋርያት ጀምሮ ብዙ የዓይን ምስክሮች አይተው ያስተላለፏቸውን ትውፊቶች ሁሉ ምን ያህል እንደሚጠሉ ሳስብ በዚያ ዘመን የነበሩ አይሁድ በአካለ ሥጋ የመመለስ እድል ገጥሟቸው ቢጠየቁ እንኳ ‹‹ እንዴት ከእኛ በላይ ጠላችኋቸው›› ብለው የሚገረሙባቸው ስለሚመስለኝ እደነቃለሁ፡፡ ሦስተኛውና ሁልጊዜም ኢትዮጵያ ውስጥ ባሉ ተሐድሶዎች የምደነቀው ደግሞ ዐፄ ዘርዓ ያዕቆብና ማኅበረ ቅዱሳን ላይ ባላቸው ጥላቻ ነው ፡፡