(አንድ አድርገን ግንቦት 23
2005 ዓ.ም)፡- ‹‹ ከምሽቱ 1፤30 ላይ አንድ ሞቅ ያለው የተበሳጨ ጀብራሬ አቡነ ጴጥሮስ ሃውልት ላይ ሽንቱን እየሸና ‹አንተ ድንጋይ ጓደኞችህ ተመችቷቸው
በማርቼዲስ ሲንሸራሸሩ ይህው አንተ ድንጋይ ሆነህ ቀረህ ድንጋይ አሸናብሃለሁ › ሲል በልጅነት ደም ፍላት ዘልዬ ከጀብራሬው
ጋር ግብ ግብ ገጠምኩኝ ፡፡ ድንጋይ አይደለም፡ ‹ድንጋይ ነው› በሚል
በቡጢም ተቃመስን ፡፡ ከስብሰባው የተበተኑ ሰራተኞች ገላገሉንና እየተበሳጨሁ
ቤቴ ገባሁ፡፡ ሌሊቱን አልተኛሁም፡፡ ጴጥሮስ ሕያው ነህ ለማለት ፤
ጴጥሮስ ድንጋይ አይደለም ለማለት ይመስለኛል ‹ጴጥሮስ ያችን ሰዓት› ስጭር አደርኩ ›› ጸጋዬ ገብረ መድህን
ሃሙስ ሚያዚያ 24 ቀን 2004
ዓ.ም ጠዋት ሳተና የሆኑ ወጣቶችና ጎልማሶች የአቡነ ጴጥሮስን ሃውልት
ልክ እንደ አስቸጋሪ ኮርማ በገመድ ጠልፈው አንዳች የሚያህል ክሬነር አስረው ከነበረበት ለመንቀል ደፋ ቀና ይላሉ፡፡
አላፊ አግዳሚው ወጪ ወራጁ እንደ ዘበት እያየ ያልፋል፡፡ ከፊሉም ሞባይሉን አውጥቶ
ፎቶ ሊያነሳ እና ሊቀርጽ ይሞክራል፡፡ ‹‹የሰውየው›› (ሁነኛ ሰው) ሃውልት (የእኛ የእውነተኝነት) ዋቢ ከውስጥ በአቡጀዲ ተጠቅልሎ
፤ ከውጭ በጣውላ ተጠፍንጎ ፤ በብረት ዘንግ ተደግፎ ሊነቀል ትዕዛዝ ይጠብቃል፡፡