ከላይፍ መጽሄት የተወሰደ
(ቅጽ 7 ቁጥር 99 … ጥር
2005 እትም)
- “ቤተክርስቲያናችን ከግብጽ ባርነት ወጥታ ራሷን ችላ እየተራመደች በመሆኗ ከእነሱ የምትዋሰው ነገር የላትም፡፡” ብጹእ አቡነ ሕዝቅኤል
- “አቡነ መርቆሪዎስ ሳይወዳደሩ በቀድሞ የፕትርክና ስልጣናቸው ይቀጥሉ ማለትም መንፈሳዊው ህግ አይደግፈውም” ብጹእ አቡነ ሕዝቅኤል
- የቅ/ሲኖዶሱን ውሳኔ የተቃወሙት ዋና ጸሐፊው ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል የሥልጣን መልቀቂያ ደብዳቤ አቀረቡ ....... Haratewahedo
- “ራሴን ከቅዱስ ሲኖዶስ አግልዬ ብሆን ኖሮ እዚህ አታገኙኝም ነበር፡፡” ብጹእ አቡነ ሕዝቅኤል
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን
ቅዱስ ሲኖዶስ ለቀናት ያደረገው ስብሰባ በመጠናቀቅ ባሳለፍነው ሳምንት ባወጣው መግለጫ አሜሪካን ሀገር የሚገኝው ሲኖዶስ ያቀረበውን
ጥያቄ ለመቀበል ሕገ ቤተክርስቲያን እንደማይፈቅድለት በመግለጽ ስድስተኛውን
የቤተርክርስቲያን ፓትርያርክ ለመምረጥ መወሰኑን ማስታወቁ አይዘነጋም፡፡ የላይፍ መጽሄት አዘጋጆች ከመግለጫው በኋላ ወደ ሲኖዶስ
ዋና ጸሀፊ አቡነ ሕዝቅኤል ቢሮ በማምራት አቡኑን ማብራሪያ ጠይቀዋል፡፡ አቡነ ሕዝቅኤል የስራ ጫና ውስጥ የነበሩ ቢሆንም መጠነኛ ጊዜ መስዕዋት በማድረግ ጥያቄዎቻችንን በመቀበል ተገቢ ነው ያሉንን
ምላሽ ሰጥተውናል፡፡ ነገር ግን አቡኑን በምናነጋግርበተ ሰዓት ማንነቱ
ያልለየነው አንድ ሰው ቢሮ ውስጥ ተቀምጦ ጥያቅና መልሱን ይከታተል ነበር፡፡ ለብጹእ አቡነ ሕዝቅኤል የምናቀርብላቸው ጥያቄ እኛን
እየተመለከቱ ምላሽ መስጠት ይገባቸው የነበረ ቢሆንም በእያንዳንዱ አረፍተ ነገር ግለሰቡን እየተመለከቱ ማረጋገጫ እንደሚጠይቅ ሰው አይናቸውን ገጽታው ላይ
ያንከራትቱ ነበር፡፡ ጥያቄያችን ጨርሰን ከቢሮ ልንወጣ ስንልም “አቡኑን ለማስለፍለፍ ሞክራችሁ ነበር እሳቸው ግን ብልጥ በመሆናቸው አንዳች
ነገር አልተናገሩም” ብሎናል፡፡ ለማንኛውን ቃለ ምልልሱን እነሆ፡፡
ላይፍ፡-
የአገር ውስጥ ሲኖዶስ ባወጣው መግለጫ በቀጥታ ስድስተኛውን ፓትርያርክ ወደ መምረጥ እንደሚገባ
አስታውቋል ፡፡ በዚህ ዙሪያ ከግብጽ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን የምትወስዱት ትምህርት ምንድነው ?
አቡነ ሕዝቅኤል፡- እኛ ከግብጽ ኦርቶዶክስ እንለያያለን ፤ ምናልባት ልዩነታችን በቋንቋ
ብቻ አይደለም፡፡ በሐይማኖት በኩል አንድ ነን፡፡ በፓትርያርክ ምርጫ በኩል የራሳችን መንገድ አለን፡፡ ቤተክርስቲያናችን ከግብጽ
ባርነት ወጥታ ራሷን ችላ እየተራመደች በመሆኗ ከእነሱ የምትዋሰው
ነገር የላትም፡፡