ዛሬ ያመቱ፣ የ2004
ዓ.ም. 364ኛ ቀን ነው፡፡ ዓመቱ ሊያበቃ፣ ዘመኑ ሊካተት አሮጌ ኾኖ ሊያልፍና አምና የሚለውን ካባ ለመደረብ 24 ሰዓት ወይም 1,440 ደቂቃ ወይም 86,400 ሰከንድ ቀርቶታል፡፡
ርእሰ ዐውደ ዓመት (የዓመት ዙር ዋና መነሻ) በፀሐይ መስከረም 1 ቀን 2005 ዓ.ም.፣
በፀሐይና ጨረቃ ጥምር ኢትዮጵያዊ አቆጣጠር 2013 ዓመት ሊብት ዘመኑም ሊሞሸር፣ ዓመቱም ሊቀመር በናፍቆት እየተጠበቀ ነው፡፡ በባህላዊውና ዓለማዊው ትውፊት ‹‹እንቁጣጣሽ››፣ በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ትውፊት ‹‹ቅዱስ ዮሐንስ›› እየተባለም ይጠራል፡፡ ቤተ ክርስቲያኒቷ እያንዳንዱን ዓመት ለአራቱ ወንጌላውያን በመስጠቷ ምእመኖቿና ካህኖቿ የተረኛውን ወንጌላዊ ስም በመጥራት መልካም ምኞታቸውን ይገላለጹበታል፡፡