- በሁሉ ነገር ላይ እኛ ቤተክርስቲያናችን እናስቀድም ፤ እኛ ከመነቃቀፍ ይልቅ ተከባብረን ፤ ከመራራቅ ይልቅ ተቀራርበን አንድ ሆነን ብንነጋገር የማይፈታ ችግር የለም” አቡነ መርቆርዮስ ለሰላም ኮሚቴው የተናገሩት
- አቡነ መርቆርዮስን ለማውረድ ቅዱስ ሲኖዶስ በተሰበሰበበት ወቅት የተጻፈውን ቃለ ጉባኤ እንዳየሁት “እኔ ከዚህ አልስማማም ፤ የኔ ድምጽ በልዩነት ይያዝልኝ” ያሉ አቡነ በርናናስ ብቻ ነበሩ...... ዲ/ን ዳንኤል ክብረት
- “ትልቁ ነገር ሁለቱም ሲኖዶሶች ተገናኝተው ቤተክርስቲያኒቱን ማዕከል አድርገው የሚነጋሩ ከሆነ የማይፈታ ችግር አይኖርም፡፡” ሊቀ ካህናት ኃ/ሥላሴ
- “ቤተክርስቲያን ያለ ፓትርያርክ የቅርብ አመራር ለብዙ ዘመን የቆየች ቤተክርስቲያን ናት ፤ ያለ አንድነቷ ግን መኖር ከባድ መሆኑን በተለያየ ጊዜ አይተዋለች፡፡” ዲ/ን ዳንኤል ክብረት
- “አሜሪካ ሆነው ስንት ጆሮ በተከፈተበት ፤ ምላስ በበዛበት ፤ የዜና ማሰራጫዎች በበዙበት ቦታ ቁጭ ብለው ምንም አይነት ነገር ባለመናገራቸው በዘመኑ ቋንቋ እጅግ በጣም አድናቂ ነኝ፡፡ የእስከ ዛሬ ዝምታቸው ተገቢ ነው ፤ የአሁኑ ዝምታቸው ግን ይህን ያህል አስፈላጊ ነው ብዬ አላስብም ፡፡” መጋቢ ሀዲስ እሸቱ አለማየሁ
(አንድ አድርገን ህዳር 18 2005 ዓ.ም)፡- የአሜሪካ ድምጽ ሬዲዮ እሁድ 15/03/2004 ዓ.ም ከአዲስ አበባ መጋቢ ሀዲስ እሸቱ አለማየሁ እና ዲያቆን ዳኤል ክብረትን ከአሜሪካ ደግሞ ከሰላምና የእርቅ ኮሚቴ ሊቀ ካህናት ኃ/ሥላሴ አለማየሁ ከዴንቨር እና ጉዳዩ የማይመለከታቸው በቅዱስ ሲኖዶስ ስለ ምፍቅናቸው ተጠይቀው መልስ መስጠት ያልቻሉት አባ ሰረቀ ብርሀንን በማቅረብ አወያይቷል ፡፡ በዚህ ውይይት ቀሲስ ዘበነ ተገኝተው ሃሳባቸውን ይሰጣሉ ተብሎ ቢጠበቅም በውይይቱ ወቅት ሳይመቻቸው በመቅረቱ ውይይቱን ሊካፈሉ አልቻሉም ፡፡






