·ኮሚቴው ፍጹም ውግዘት የሚገባቸውን የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ እንቅስቃሴ አራማጅ ማኅበራትና ግለሰቦች ለይቷል - ማኅበረ ሰላማ፣ ማኅበረ በኵር፣ የምሥራች አገልግሎት፣ አንቀጸ ብርሃን፣ የቅድስት ልደታ ለማርያም መንፈሳዊ ማኅበር፣ የኢትዮጵያ መንፈሳዊ ተሐድሶ ኅብረት፣ አሸናፊ መኰንን፣ አግዛቸው ተፈራ፣ ጽጌ ስጦታው እና ግርማ በቀለ ይገኙባቸዋል።
·“ሃይማኖቴ እንደ አባቶቼ ነው” ያሉት የአባ ሰረቀ እና “የቅን ልቦና የመንፈሳዊና የፈውስ አገልግሎትን ያቋቋምኹት ልጆቼን የማበላቸው ስለተቸገርኹ ነው” ያሉት የ‹ሊቀ ካህናት› ጌታቸው ዶኒ ጉዳይ ያለውሳኔ ሐሳብ ለምልአተ ጉባኤው ውሳኔ ቀርቧል።
·አባ ጳውሎስ ከጥንተ አብሶ ጋራ በተያያዘ ስለ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ንጽሕና እንዲመሰክሩ ሊጠየቁ ይችላሉ።
·ሊቃውንት ጉባኤው ተደጋጋሚ ጥሪ አድርጎለት ያልቀረበው በጋሻው ደሳለኝ ዛሬ ጠዋት የሊቃውንት ጉባኤውን ሰብሳቢ በእጅጋየሁ በየነ አማላጅነት ሲለማመጥ ታይቷል፤ ሊቃውንት ጉባኤው “በአንድ ወቅት በራስ ቅል ኮረብታ ላይ ኢየሱስና ዲያቢሎስ ቁማር ተጫወቱ . . . ዲያቢሎስም በጨበጣ ገባ” የሚለውና ሌሎቹም ጥንቃቄ የጎደላቸው ንግግሮቹ ፍጹም ውግዘት የሚገባቸው እንደኾኑ አመልክቷል።
·የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን አመራርና መዋቅር ይሻሻላል፤ በጠቅላላ ጉባኤና በቦርድ ይመራል፤ የኮሚሽኑ ሊቀ ጳጳስ የኮሚሽኑ ኮሚሽነር እንደሚኾኑ ተጠቁሟል።
·የማኅበራት መመሪያ ረቂቅ ለውይይት ቀርቧል፤ አሁን ባሉበት አኳኋን ከቀጠሉ “ሌላ ሲኖዶስ ይኾናሉ፤ የፖሊቲካ ዓላማ ማስፈጸሚያ ይኾናሉ፤ በቀኝ ዘመምና ግራ ዘመም አቋም ቤተ ክርስቲያኒቷን ይውጣሉ/ይከፍላሉ” የሚል ስጋት የቀረበባቸው ማኅበራት ንብረት በአጥቢያ አብያተ ክርስቲያን መዋቅር ውስጥ ተጠቃልሎ እንዲተዳደር ሐሳብ ቀርቧል፤ የመመሪያውን ረቂቅ በጥንቃቄ የተመለከቱት የምልአተ ጉባኤው አባላት ጉዳዩ በይደር እንዲታይ አድርገዋል።
(ደጀ ሰላም፤ ግንቦት 9/2004 ዓ.ም፤ May 17/ 2012)፦ የርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ በግንቦት 8 ቀን 2004 ዓ.ም ስድስተኛ ቀን ውሎው በፕሮቴስታንት ድርጅቶች ከፍተኛ ድጋፍ እየተደረገላቸው የቤተ ክርስቲያናችንን ትምህርተ ሃይማኖት ለማፋለስ፣ ሥርዐተ እምነቷን ለመለወጥ፣ አገልጋዩንና ምእመኑን ለመከፋፈል በቡድንና በድርጅት ኾነው በመንቀሳቀስ ላይ ስለሚገኙት የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ኑፋቄ አራማጅ ማኅበራትና ግለሰቦች የተዘጋጀውን ሪፖርት አዳምጧል፡፡