ወደ አማራ ክልል ሲጓዙ የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናትን ጨምሮ በርካታ ሃይማኖታዊ ቦታዎች ይገኛሉ፡፡ በክልሉ በሚገኘው የዋግኽምራ ዞን ውስጥ ካሉ ጥንታዊ ገዳማትና አብያተ ክርስቲያናት ዘናቆ አቦ ገዳም፣ ዋሻ መድኃኔዓለም፣ ብርብር ጊዮርጊስ፣ ደብረ ፀሐይ ወይብላ ማርያም፣ ደብረ ሎዛ ውቅር ማርያምና አባ ዮሐንስ ይጠቀሳሉ፡፡
በዋግኽምራ ዞን በሚገኘው የሰቆጣ ከተማ ደግሞ ባር ኪዳነ ምሕረት ገዳምና ሌሎችም ተጠቃሽ ናቸው፡፡
ውቅር መስቀለ ክርስቶስ ቤተ
ክርስቲያን ኢትዮጵያን ከ495 እስከ
525 ዓ.ም.
አስተዳድሮ በነበረው አፄ ካሌብ ዘመነ መንግሥት ከአንድ ቋጥኝ ድንጋይ ተፈልፍሎ የተሠራ ቤተ ክርስቲያን መሆኑ ይነገራል፡፡ ቤተ ክርስቲያኑ ከላሊበላ ውቅር
አብያተ ክርስቲያናት 500 ዓመት ቀድሞ እንደተሠራና የላሊበላ ፍልፍል ሕንፃዎች መነሻ ሊሆን እንደሚችል በቤተ
ክርስቲያኑ ያሉ
ሊቃውንት ያምናሉ፡፡
ቤተ ክርስቲያኑ በሰቆጣ ከተማ
ደቡብ ምሥራቅ አቅጣጫ ያሉ ሰንሰለታማ ኮረብታዎች ያዋስነዋል፡፡ ቤተ ክርስቲያኑ ውስጥ
ሰባት ክፍሎች (ቅኔ ማህሌት፣ ቅድስትና መቅደሱን ጨምሮ) እና ጥንታዊ ሥዕሎች ያሉዋቸው አምስት ዐምዶች አሉ፡፡ ወደ ቤተ ክርስቲያኑ የሚያስገቡ አራት በሮችና ዙሪያውን አሥራ አራት መስኮቶች ይገኛሉ፡፡
ቤተ ክርስቲያኑን ልዩ ከሚያደርጉት በዋነኛነት የሚጠቀሰው በውስጡ ያለው ዋሻ ነው፡፡ በጎበኘንበት ወቅት ዋሻው በእንጨት ርብራብ ተከድኖ ነበር፡፡ ዋሻው በሁለት አቅጣጫ (ሰሜንና ደቡብ) የተቦረቦረ ሲሆን፣ ቤተ ክርስቲያኑን ያስጎበኙን የደብሩ አስተዳዳሪ መልአከ ሰላም መርሐጥበብ በየነ
እንደሚሉት፣ አንደኛው በር ወደ ላሊበላ ሌላኛው ደግሞ
ወደ አክሱም ይወስዳሉ፡፡





