Thursday, December 3, 2015

‹‹እኛ አሁን ቁጭ ያልነው እግዚአብሔርን አምነን ነው ፤ ዝናብ ከቀረ መልቀቅ ነው ፤ መሄድ ነው ፤ መሞት ነው›› የአካባቢው ገበሬ



(አንድ አድርን ህዳር 24 2008 ዓ.ም)፡- በድርቅ በተጎዶ የደቡብ ወሎ ዞኖች ውስጥ ባደረግነው ዳሰሳ በሦስተኛ ቀናችን በአሸዋ መኪና ከአጂባር ተነስተን  ፉርቃቄ ፤ ጎሽ ሜዳ ፤ ዋልካ ሜዳ እና ሰንበሌጤን ተመልክተን ነበር፡፡ መንገዱ የተጎዳ ፒስታ መንገድ ስለሆነ ጉዞው ሰውነትን የሚያንዘፈዝፍ አድካሚ ነበር፡፡ እነዚህ አካባቢ ቆላማ ቦታዎች ሲሆኑ  የዝናብ እጥረት ያጋጠማቸው  አካባቢዎች ነበሩ፡፡በቦታዎቹ በተገኝንበት ወቅት እድሜያቸው ከ60 የሚዘልቁ ሁለት አርሶ አደር ገበሬዎችን በመቅረጸ ድምጽ ፍቃዳቸውን ሳንጠይቅ በውይይት መልክ ከቀረጽነው ውስጥ ለአንባቢ እንዲሆን እንዲህ አዘጋጅተን አቅርበነዋል፡፡


ከመጀመሪያው አርሶ አደር ጋር የተደረገ ውይይት..
መቼ ነው ዝናብ እናንተ ጋር የዘነበው ?
ዝናቡ ሃምሌ 20 አካባቢ ነበር የጀመረው ፤ ትንሽ ጥሎ ሲያበቃ ፤ አድሮ ሲያካፋ አድሮ ሲያካፋ ከአስራ አምስት ቀን በኋላ በዚያው  ቆመ፡፡

ዝናቡ ቆላው ላይ ብቻ ነው ያልጣለው? ሌላ ቦታ ላይ ዝናብ ጥሎላቸዋል ?
እኛ አካባቢ ብቻ ነው ወደ ላይ(ደጋው ክፍል) ይሻላል፡፡

ከአሁን በኋላ ዝናብ የምጠብቁት መቼ ነው ?
መጋቢትን ይዘን ወደ ሚያዚያ…

አካባው የበልግ ዝናብ አለው ?

        የለውም ፤ አያውቅም ፤

Wednesday, December 2, 2015

ሁለተኛ ቀን በድርቅ በተጎዱ አካባቢዎች ፤ በነዋሪ አልባ መንደሮች



‹‹አባ ቦሩና ወርጠጅ›› ነዋሪ አልባ መንደሮች

(አንድ አድርገን ህዳር 22 2008 ዓ.ም)፡- የመጀመሪያ ጉዟችንን ከደሴ ወደ መቅደላ ባደረግንበት ወቅት አባ ቦሩ እና ወር ጠጅ ከተማዎችን በመንገዳችን ላይ አገኝናቸው ፤ በርካታ ቤቶች በግራ እና በቀኝ መስመር ላይ ተሰርተዋል ፤ ጸጥ ረጭ ያሉ አካባቢዎች ፤ ሽው ከሚል ከንፋስ ድምጽ በቀር የሰዎች እና የቤት እንስሳት ድምጽ የማይሰማባቸው ቦታዎች ፤ በመንደሮች ውስጥ ብዙዎቹ ቤቶች የእንጨት አጥር አላቸው  ፤ እነዚህ መንደሮች ውስጥ ሁሉም ቤቶች ተዘግተዋል ፤ የተዘጉት በበር ቁልፍ ሳይሆን መስኮትና በራቸው በውጭ በኩል በተመቱ ተላላፊ እንጨቶች ነው ፤ ለጥቂት እረፍት በቦታዎቹ ላይ በወረድንበት ሰዓት በአካባቢው አንድም የሰውም ሆነ የቤት እንስሳት የሌሉበት ቦታ መሆናቸውን ተገነዝበናል ፤ ሁለት መንገደኞችን አስቁመን ስለ መንደሮቹ ትንሽ እንዲያጫውቱን ጠየቅናቸው እነርሱም እንዲህ አሉን
‹‹ይህ አካባቢ በፊት ሰዎች ይኖሩባቸው ነበሩ ፤ ነዋሪዎቹ ለአቅመ ሄዋን የደረሱ ሴት ልጆቻቸውን  በደሴ ፤ በአዲስ አበባ እና በአረብ ሀገራት ለስራ ያሰማሩ ይገኙባቸዋል ፤ ከዚህ ውጪ ግን እርሻውን እንደምታዩት ፍሬ አይታይበትም አካባቢውም ውሃ ለማግኝት አስቸጋሪ ሆኗል በዚህ ምክንያት ነዋሪው በሩን ዘግቶ ቦታውን ሊለቅ ችሏል ፤ ጥቂቶች ቆላውን መሬት ስላላቸው ወደዚያው አምርተዋል ፤ የተወሰኑ ሰዎች ቆላውን መሬት ስላላቸው ወደዚያው አምርተዋል ፤ ሌሎች ደግሞ ወዴት እንደሄዱ እንኳን አይታወቅም›› የሚል መልስ ሰጥተውናል፡፡

Tuesday, December 1, 2015

በመጀመሪያ ቀን ፡ በድርቅ የተጎዶ አካባቢዎች




(አንድ አድርገን ህዳር 21 2008 ዓ.ም)፡- በአሁኑ ሰዓት ባለሙያዎች እንደሚሉት በአየር ንብረት ለውጥ አማካኝነት ከተጎዱ አካባቢዎች በግንባር ቀደምነት አፋር ክልል የመጀመሪያውን ቦታ ሲይዝ ቀጥሎም ሰሜን ወሎ ፤ የሀረርጌ ወረዳዎች እና ኦሮሚያ በቅደም ተከተል ይቀመጣሉ፡፡ 


እኛ ችግሩን ለማየት ከአዲስ አበባ ከ12 ቀናት በፊት ስንነሳ አንድ አላማን ይዘን ነበር ፤ እርሱም ‹‹ የችግሩ ተጋላጭ አካባቢዎችን በመመልከት ለአንባቢያን ማድረስ›› የሚለው ነበር፡፡ ጉዞው ከአዲስ አበባ በመነሳት ደሴን መዳረሻ በማድረግ ከደሴ እስከ 200 ኪሎ ሜትር ድረስ የሚገኙትን ወረዳዎች ማለትም መቅደላ(ማሻ)  ፤ ሳይንት  ፤ አምባሰል ፤ ለጋምቦ ፤ መግዲ ፤ መካነ ሰላም ፤ ወረ ኢሉ ፤ ወረ ባቦ ወረዳዎችን እና በስራቸው የሚገኙ  ቀበሌዎችን አቅም በፈቀደ መጠን ለመቃኝት ያለመ ነበር፡፡

በወሎ አካባቢ በድርቅ የተጎዱ አካባቢዎችን በቦታው ተገኝነተን እኛ እንዳየናቸው




(አንድ አድርገን ህዳር 21 2008 ዓ.ም )፡- በአሁኑ ሰዓት በመላ ሀገሪቱ የተከሰተውን የድርቅ አደጋ ለመቃኝት አምስት ሰዎችን ያካተተ አንድ ቡድን ወደ ደቡብ ወሎ እና ሰሜን ወሎ ወረዳዎችንና ቀበሌዎች  ቃኝተን ለመምጣት በገባነው ቃል መሰረት ላለፉት ለ12 ቀናት የቆየ ጉብኝት ከደሴ እስከ አምባሰል ፤ ከሳይንት እስከ ወግዲ ፤ ከመካነ ሰላም እስከ ወረ ባቦ ፤ ከሰጎራ እስከ አምባ ማርያም ፤ ከመጓት እስከ አባ መላ ፤ ከኢላላ እስከ ገንቦሬ ፤ ከኩታበር እስከ ደላንታ ፤ ከአቅስታ እስከ መቅደላ ፤ ከማሻ እስከ ወረኢሉ ያሉትን ወረዳ እና ቀበሌዎች በመቃኝት የችግሩ መጠንና ስፋት ምን ያህል አደጋ ሊያደርስ እንደሚችል ለማየት ሞክረናል፡፡ ጉዞው በሕዝብ ማመላለሻ አውቶቡሶች ፤ በድንጋይ ገልባጭ መኪናዎች እና በእግር የተደረገ በጣም አድካሚ እና በፈተናዎች የተሞላ ሲሆን በዘመናችን የመጣውን ችግር እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ ሃላፊነታችንን ለመወጣት በሃላፊነት የአቅማችንን መረጃ ለማድረቅ ከቅን መንፈስ ተነስተን ያደረግነው መሆኑን ለማስገንዘብ እንወዳለን ፡፡ በቦታዎቹ ተገኝተን ያገኝነውን መረጃ በምስል እና በድምጽ ቀርጸን ያስቀረን ሲሆን ለአንባቢያን በሚያመች መልኩ ከዛሬ ጀምሮ የምናቀርብ መሆኑን ለመግለጽ እንወዳለን፡፡ መረጃዎቹ ከ12 ዓመት እረኛ እስከ 90 ዓመት አዛውንት ፤ ከአራስ እናት እሰከ መምህራን ፤ ከቀበሌ ሹማምንቶች እሰከ እርዳታ ማስተባበሪያ ሥራ የሚሰሩ ሰዎች በተሰበሰበ መሆኑን ለመግለጽ እንወዳለን፡፡ በአንኳር ከምንዳስሳቸው ነጥቦች ውስጥ የሚከተሉትን ይገኙበታል

  • መንግሥት በቦታው ፍቃድ የሌላቸው ጋዜጠኞች እንዳይዘልቁ ስለሚያደርገው ጥብቅ ፍተሻ
  • ‹‹አባ ቦሩ እና ወር ጠጅ›› ነዋሪ አልባ መንደሮች
  • ድርቁን ወደ ርሃብ ሊያሸጋግር አቅም ያለው የውሃ ችግር
  • በየጊዜው ስለሚደረጉ የወረዳ ካቢኔዎች ስብሰባ
  • የሕዝቡን ችግር ያልቀረፈው የሴፍቲኔት ፕሮግራም
  • 150 ኪሎ ስንዴ ለ15አባራዎች ፤ 20 ሊትር ዘይት ለ 60 አባዎራዎች ያከፋፈለች ቀበሌ እና ርዳታውን ለመቅረጽ ስለመጡ ጋዜጠኞች
  • ችግሩን ወደ ባሰ ደረጃ ለማሸጋገር የሚጥሩ ነጋዴዎች
  • አንድ እንጀራ 8 ብር የሚሸጥበት ጎጥ
  • በ1977 ዓ.ም የተከሰተው ርሀብ መንግስት ስላደረገው ርዳታ ፤ ስለ ሰፈራ እና ሂደቱ (ሕዝቡ የተሰበሰበበት እና ስለሰፈረበት ቦታ ፤ በ Helicopter እህል የተዘረገፈበት ቦታ )
  • ውሃ ችግሩ ያፋጠጣቸው ቀበሌዎችና በውሃ ችግር ምክንያት ውሃ ወለድ በሽታ ስላጠቃት ጎጥ
  • ውሃ ችግሩ ወደ ፈረቃ እንዲያመሩ ያደረጋቸውና በአራት ቀን አንድ ጄሪካን ብቻ እንዲቀዱ የተገደዱ ቀበሌዎች
  • ለከብቶች አቅርቦት የሚሆን ውሃ ባለመኖሩ ከብቶቻውን ወደ በሽሎ ወንዝ በመውሰድ ችግሩ እስኪቃለል መዋያ ማደሪያቸውን ያደረጉ ቀበሌዎች…
  • በከፍተኛ ድርቅ የተጎዱ ቆላማ አካባቢዎች ፤ድርቁ ማኅበረሰቡ ላይ ስለፈጠረው የስነልቦና ቀውስ
  • …… ሌሎችም እዚህ ላይ ያልጠቀስናቸውን ነጥቦች በማንሳት ለአንባቢያን ያየነውን ፤ የሰማነውን ፤ በምስል ያነሳነውንና በድምጽ የቀረጽነውን መረጃ ለማድረስ እንሞክራለን፡፡
ይጠብቁን